በሮም አቅራቢያ በሚገኝ ቶር ቨርጋታ የተከበረ የወጣቶች ኢዮቤልዩ በዓል በሮም አቅራቢያ በሚገኝ ቶር ቨርጋታ የተከበረ የወጣቶች ኢዮቤልዩ በዓል  (@Vatican Media)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ወጣቶች ከምቾት ሕይወት ወጥተው ለሰላም እንዲሰሩ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ለ40ኛው የዓለም ወጣቶች ቀን ባስተላለፉት መልዕክት፥ ወጣቶች እንደ ክርስቲያን ከሚሰቃዩት ሰዎች ጎን በመቆም የሰላም አርበኞች የመሆን ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ለ40ኛው የዓለም ወጣቶች ቀን ባስተላለፉት መልዕክት፥ ወጣቶች እምነትን ለመከፋፈል የሚጠቀሙ ሰዎችን ሳይከተሉ ይልቁንም የሰላም ገንቢዎች በመሆን ለእርቅ እንዲሠሩ አበረታተዋል።

በደቡብ ኮሪያ መዲና ሴኡል እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2027 ዓ. ም. ለሚደረገው ዓለም አቀፍ ስብሰባ ዝግጅት እንዲሆን በማለት በቤተ ክርስቲያናት በሀገረ ስብከት ደረጃ የሚከበረው ዓመታዊው የዓለም ወጣቶች ቀን ኅዳር 14/2018 ዓ. ም. እንደሆነ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ “ከእኔ ጋር ስለ ነበራችሁ ምስክሮቼ ናችሁ” በሚል መሪ ጭብጥ፥ “የተስፋ ነጋዲያን እንደመሆናችን እና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ደፋር የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክሮች ለመሆን ራሳችንን እናዘጋጃለን” ብለው፥ በሁለት የምስክርነት ገጽታዎች ላይ በማትኮር፥ “ከእግዚአብሔር በስጦታነት የምንቀበለው ከኢየሱስ ጋር ያለን ወዳጅነት እና በኅብረተሰብ ውስጥ የሰላም ፈጣሪዎች ለመሆን ባለን ቁርጠኝነት ላይ ነው” ብለዋል።

ጓደኞቹ በመሆናችን ምስክሮቹም ነን

ክርስቲያናዊ ምስክርነት የሚመነጨው ለተሰቀለው እና ሁሉን ለማዳን ሲሉ ከሞት ከተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ባለን ወዳጅነት መሆኑን ያብራሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ “ይህ ምስክርነት ከርዕዮተ ዓለም ፕሮፓጋንዳ ጋር መምታታት የለበትም፣ ምክንያቱም የውስጥ ለውጥ እና የማኅበራዊ ግንዛቤ ትክክለኛ መርህ ነው” ብለዋል።

“ኢየሱስ ክርስቶስ እኛ ማን እንደሆንን፣ ልባችንን እና ከመድልዎ እና በኢ-ፍትሃዊነት መቆጣታችንን በሚገባ ያውቃል” ብለው፥ “ፍላጎቱ የፖለቲካ ድርጅት አባል ወይም የማኅበረሰብ አንቂዎች እንድንሆን ሳይሆን፥ ከእርሱ ጋር ጓደኛሞች ሆነን ሕይወታችን እንዲታደስ ነው” ብለዋል።

አክለውም፥ “ምሳሌነቱ እውነተኛ ምስክነት ልታይ ባይነት ወይም ተከታዮቻቸውን የራሳቸው ብቻ ማድረግ አለመሆኑን የሚያሳስበን ነው” ብለዋል። “እውነተኛ ምስክሮች ትሑት እና ነፃ፥ ከሁሉም በላይ ከግለኝነት ነፃ በመሆን የትኩረት ማዕከል እና ከማስመሰል ነፃ የሆኑ ናቸው” ሲሉ አስረድተዋል።

በመሆኑም እውነተኛ የክርስቲያን ምስክርነት ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ እርሱ ብቻ የሚያድን መሆኑን ማወቅ እና ወደ እርሱ መመልከት እንደሆነ ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ብዙውን ጊዜ አጥብቀው እንደተናገሩት፥ “ከራሳችን እና ከምቾቶቻችን ካልወጣን፣ ወደ ድሆች እና ከእግዚአብሔር መንግሥት እንደተገለሉ ወደሚሰማቸው ስዎች ዘንድ ካልሄድን ክርስቶስን ልናገኝ እና ስለ እርሱ መመሥከር አንችልም” ማለታቸውንም ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል።

ምስክሮቹ በመሆናችን ሚስዮናውያን ነን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመቀጠልም፥ አብዛኞቹ እኩዮቻቸው ለአመጽ የተጋለጡ፣ የጦር መሣሪያን እንዲታጠቁ የተገደዱ፣ ከሚወዷቸው ተለይተው እንዲሰደዱ የሚገደዱ፣ ብዙዎቹም ትምህርትን እና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች የሌላቸው መሆኑን ወጣቶች ፈጽሞ እንዳይዘነጉ አሳስበዋል።

“ነገር ግን ሁሉም ትርጉም ያለውን ሕይወት የሚፈልጉ ናቸው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “ከዚህም ጋር ተያይዞ የሚመጣ አለመረጋጋት፣ እያደገ የመጣው ማኅበራዊ እና የሥራ ጫና፣ የቤተሰብ ቀውሶችን የመፍታት ችግር፣ የተለያዩ ዕድሎችን ባለማግኘታቸው የሚሰማ አሳማሚ ስሜት እና በሠሩት ስህተት የሚጸጸቱ ናቸው” ብለዋል።

“ከሌሎች ወጣቶች ጎን መቆም፣ ከእነሱ ጋር መጓዝ እና እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ወደ እያንዳንዱ ሰው እንደቀረበ ማሳየት ትችላላችሁ” ሲል ተናግረዋል።

እንዲሁም ወጣት ክርስቲያኖች ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በነበራቸው ሕያው ዝምድና የሕይወትን እውነተኛ ትርጉም እንዲያገኙ የሚያግዙ መጽሐፍ ቅዱስን፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ወዳጆች እና ምስክሮች መፈለጋቸውን እንዲቀጥሉ አደራ ብለዋል።

“በእርግጥ ጥልቅ ጥያቄዎቻችን ትኩረታችንን የሚስብ ነገር ግን አእምሮአችንን እና ልባችንን ባዶ በሚያደርግ መቆሚያ በሌለው ሞባይላችን በኩል ሊደመጥ እና መልስ ሊገኝበት አይችልም” ሲሉ ተናግረው፥ “እውነተኛ ፍላጎቶቻችንን ማሟላት የምንችለው ዘወትር ከራሳችን አልፈን በመሄድ ነው” ብለዋል።

ወንድማማችነት የሰላም መሠረት ነው

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ወጣቶች ግዴለሽነትን እና መንፈሳዊ ስንፍናን በማሸነፍ፣ አዳዲስ የኑሮ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት በጋራ በመሥራት የጓደኝነት እና የወንድማማችነት ትስስርን ለማሳደግ ጥረት እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

“የእምነትን ቃልን ለመከፋፈል ከሚጠቀሙት ጋር አትተባበሩ” ብለው፥ ይልቁንም ልዩነቶችን ለማስወገድ እቅድ እንዲያወጡ እና የተከፋፈሉትን እና የተጨቆኑትን በማስታረቅ እንዲተጉ አደራ ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ “ውድ ወጣቶች እና ወዳጆቼ ሆይ! በውስጣችሁ ያለውን የእግዚአብሔርን ድምጽ በማዳመጥ ራስ ወዳድነትን አሸንፋችሁ ንቁ የሰላም ፈጣሪዎች እንድትሆኑ” በማለት ሐዋርያዊ ምክራቸውን ለግሰዋል።

“የትንሣኤው ጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ የሰላም ስጦታ ሊታይ የሚችለው የእርሱን መንፈስ በልባቸው ውስጥ በመያዝ በዓለም ላይ የጋራ ምስክርነት በሚሰጡት ሰዎች አማካይነት ነው” በማለት መልዕክታቸውን አጠቃልለዋል።

 

08 Oct 2025, 15:54