ንጉሥ ቻርለስ ሦስተኛ እና ንግሥት ካሚላ ንጉሥ ቻርለስ ሦስተኛ እና ንግሥት ካሚላ   (AFP or licensors)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ ለንጉሥ ቻርለስ እና ለንግሥት ካሚላ አቀባበል እንደሚያደርጉላቸው ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ሐሙስ ጥቅምት 13/2018 ዓ. ም. በቫቲካን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ለሚያደርጉት ንጉሥ ቻርለስ ሦስተኛ እና ለንግሥት ካሚላ አቀባበል እንደሚያደርጉላቸው ታውቋል። እንግዶቹ በቫቲካን የሚያደርጉት የሥራ ጉብኝት በቅድስት መንበር እና በባኪንግሃም ቤተ መንግሥት የተረጋገጠው ሲሆን፥ ጉብኝታቸው በአንግሊካን እና በካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት ውስጥ ታሪካዊ ጊዜን ከማመላከት በተጨማሪ በሁለት ዋና ዋና ሃሳቦች ማለትም በክርስቲያን አንድነት እና በአካባቢ ጥበቃ ላይ የሚያተኩር እንደሚሆን ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሮም በሚገኝ የቅዱስ ጳውሎስ ጳጳሳዊ ባዚሊካ ውስጥ በሚከናወን ሥነ-ሥርዓት፥ ባዚሊካው በእንግሊዝ ከሚገኙ የብሪታኒያ የነገሥታት ቤተሰብ እና የቅዱስ ቤነዲክቶስ ገዳም ጋር ያለውን የረጅም ጊዜ ትስስር በማስታወስ ንጉሥ ቻርልስ “የቅዱስ ጳውሎስ ንጉሣዊ ወንድማማችነት” የተሰኘ የክብር ማዕረግ የሚሸለሙ መሆናቸው ታውቋል። 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በዕለቱ እኩለ ቀን ላይ ስለ ፍጥረት እንክብካቤ በሲስቲን ጸሎት ቤት ውስጥ የሚቀርበውን የጸሎት ሥነ-ሥርዓት እንደሚመሩት ታውቋል። በመቀጠልም ከአንዳንድ ታዋቂ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ጋር የአካባቢ ጥበቃን በማስመልከት የተዘጋጀ ስብሰባ እንደሚካሄድ ታውቋል። ከቀትር በኋላ በስምንት ሰዓት ከአርባ አምስት ደቂቃ ንጉሡ እና ንግሥቲቱ በሮም የሚገኘውን የቅዱስ ጳውሎስ ጳጳሳዊ ባዚሊካን የሚጎበኙ ሲሆን፥ በዚህ ሥነ-ሥርዓት ላይ ንጉሥ ቻርልስ “የቅዱስ ጳውሎስ ንጉሣዊ ወንድማማችነት” የተሰኘ የክብር ማዕረግ እንደሚሸለሙ ታውቋል። 

የባኪንግሃም ቤተ መንግሥት ጉብኝቱን “ታሪካዊ” ሲል ገልጾት፥ “የተስፋ ነጋዲያን” ከሚለው የኢዮቤልዩ ዓመት መሪ ቃል ጋር በማዛመድ በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እና በእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን መካከል ላለው የክርስቲያኖች አንድነት ጥረቶች እውቅናን ሰጥቷል።

በአንድነት እና በአካባቢ ጥበቃ ላይ ያተኮረ ጉብኝት

የንጉሣዊ ቤተሰብ ጉብኝት ሁለቱ ማዕከላዊ ጭብጦችን እነርሱም የክርስቲያኖች አንድነት እና ለምድራችን የሚደረግ እንክብካቤን መሠረት ያደረገ መሆኑ ታውቋል። ቅድስት መንበር ጥቅምት 7/2018 ዓ. ም. በሰጠችው ጋዜጣዊ መግለጫ፥ ጉብኝቱ

የክርስቲያኖችን አንድነትን የሚያበረታታ እንደሚሆን በቅድስት መንበር የክርስቲያኖች ሕብረት ማጠናከሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ ፍላቪዮ ፔስ ሲያስረዱ፥ እንዲሁም በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ እህት አሌሳንድራ ስሜሪሊ በበኩላቸው ጉብኝቱ በተጨማሪም ስለ ሥነ-ምህዳር ያለውን ፋይዳ በማስመልከት ተናግረዋል።

ባሕሎችን የሚያገናኝ ዜማ

በክርስቲያኖች አንድነት ላይ የሚያውጠነጥነው የጉብኝቱ ሥነ-ሥርዓት ቅዱስ ዮሐንስ ሄንሪ ኒውማን የተረጎመውን የቅዱስ አምብሮዝ ዜማን እንደሚያካትት ታውቋል።

በአንግሊካን እና በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያናት መካከል ባለው ግንኙነት ቁልፍ ሰው የነበረው ኒውማን የካቶሊክ እምነት ተከታይ ከመሆኑ በፊት በሕይወቱ ለበርካታ ዓመታት የአንግሊካን እምነት ተከታይ እንደ ነበር ይታወሳል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2019 ዓ. ም. ንጉሥ ቻርልስ ራሳቸው በተሳተፉበት ሥነ-ሥርዓት ላይ ቅድስናቸው የታወጀላቸው ዮሐንስ ሄንሪ ኒውማን ከፍተኛ የአንግሊካን ልዑካን በሚገኙበት ከፍተኛ ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በመጭው ኅዳር 1/2025 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛን የቤተ ክርስቲያን ዶክተር ብለው በይፋ እንደሚያውጁ ይጠበቃል።

ለንጉሡ ቻርለስ የተሰጠ ልዩ ክብር

ሐሙስ ጥቅምት 13/2018 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ በቅዱስ ጳውሎስ ጳጳሳዊ ባዚሊካ ውስጥ በሚፈጸም ሥነ-ሥርዓት ላይ ከብሪታንያ ከፍተኛ የክብር ሽልማቶች መካከል አንዱ የሆነው የጋርተር ሠራዊት ምልክት ለንጉሥ ቻርለስ እንደሚሰጣቸው ይጠበቃል።

በዓሉን ምክንያት በማድረግ የቅዱስ ጳውሎስ ንጉሣዊ ወንድማማችነት ሽልማት በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛው ይሁንታ ብፁዕ ካርዲናል ጀምስ ሚካኤል ሃርቪ እና አቡነ ዶናቶ ኦግሊያሪ ለንጉሠ ነገሥት ቻርለስ እንደሚሰጧቸው የሚጠበቅ ሲሆን፥ ሽልማቱ “የክብር እና የመንፈሳዊ ኅብረት ምልክት ነው” ሲሉ ሊቀ ጳጳስ ፔስ ተናግረዋል።

ምድራችንን በጋራ የመንከባከብ ሃላፊነት

ከክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሥነ-ሥርዓት በኋላ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ እና ንጉሥ ቻርልስ ከሌሎች የቤተ ክርስቲያን መሪዎች፣ የውዳሴ ላንተ ይሁን ንቅናቄ ተወካዮች ከንግድ ተቋማት ተወካዮች፣ ከአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች እና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሙያዎች ጋር ስብሰባ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

“ስብሰባው በካቶሊካዊት እና አንግሊካን ቤተ ክርስቲያናት መካከል በሚደረገው የአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ላይ ያለውን ጠንካራ ግንኙነት አጉልቶ ያሳያል” ሲሉ እህት አሌሳንድራ ስሜሪሊ ተናግረዋል። ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ብዙውን ጊዜ ሁሉም ነገር እርስ በርስ የተገናኘ በመሆኑ አካባቢያዊ እና ማኅበራዊ ቀውሶችን በጋራ መፍታት እንደሚገባ ማሳሰባቸውን አስታውሰው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛም ይህ አካሄድ ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ መፈለጋቸውን እህት አሌሳንድራ ስሜሪሊ አስረድተዋል።

እህት አሌሳንድራ ስሜሪሊ፥ ፍጥረትን ከውድመት መከላከልን በማስመልከት ሐምሌ 2/2017 ዓ. ም. የቀረበውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎትን እና  ነሐሴ 30/2017 ዓ. ም. በካስቴል ጋንዶልፎ የሚገኘው “የውዳሴ ላንተ ይሁን” መንደር ምረቃ በዓልን የመሳሰሉ የቅርብ ጊዜ ተነሳሽነቶችን ገልጸዋል። እህት ስሜሪሊ በማከልም የአየር ንብረት ለውጥን እና የብዝሃ ሕይወት መጥፋትን ለመዋጋት የግሉ ሴክተርን የጀመረውን ጥረት አድንቀዋል።

የወደፊት ተስፋ

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፔስ እና እህት አሌሳንድራ ስሜሪሊ፥ የዚህን ጉብኝት የረጅም ጊዜ አስፈላጊነትን በማስመልከት የተናገሩ ሲሆን፥ ሊቀ ጳጳስ ፔስ ጉብኝቱ በአብያተ ክርስቲያናት መካከል የተደረገ የእርቅ ጉዞ ታሪካዊ ወቅት እንደሆነ እና ምን ያህል እንደተጓዝን በመግለጽ ተስፋን የሚሰጥ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

እህት አሌሳንድራ ስሜሪሊ በበኩላቸው ጉብኝቱ የአንድነት ምልክት እና ለአካባቢ ጥበቃ የጋራ ሃላፊነት የሚታይበት መሆኑን በማስታወስ፥ “እነዚህ የጋራ ጥረቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ለወደ ፊት ትውልዶች አስፈላጊ የሆኑ ጭብጦች ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል።

 

18 Oct 2025, 16:32