ር.ሊ.ጳ ሊዮ በቱርክ የሚገኘው ቤተክርስቲያን “በየዋሕነት አመክንዮ” ተስፋ እንድታደርግ ተጠርታለች!
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ወደ ቱርክ እና ሊባኖስ ሐዋርያዊ ጉዞአቸው ሁለተኛ ቀን በኢስታንቡል ከጳጳሳት፣ ከቀሳውስት፣ ከገዳማዊያን/ዊያት እና ከሐዋርያዊ እንክብካቤ መጋቢ ሰራተኞች ጋር በመገናኘት ጀምረዋል።በመንፈስ ቅዱስ ካቴድራል ውስጥ የተሰበሰቡት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በዚህች ምድር የክርስትና ታሪክ ጥልቀት በማመን ጀምረዋል።አብርሃም በታዛዥነት የቆመው እዚህ እንደሆነ፣ ደቀ መዛሙርቱ መጀመሪያ ክርስቲያኖች ተብለው የሚታወቁት እና የቀደሙት አባቶች የእምነትን መሠረት ለመቅረጽ እንደረዱ አስታውሰዋል። ይህ ቅርስ “በቀላሉ የሚታወስ ሳይሆን” ዛሬም የታደሰ ራዕይ እና ቁርጠኝነትን ሊያነሳሳ እንደሚገባ አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።
በትንሽነት የሚገኘው ጥንካሬ
ከዚያም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “የትንሽነት መንገድ” ብለው ስለጠሩት ነገር ተናገሩ። የቤተክርስቲያኒቱ ተልእኮ በቁጥር ወይም በተጽዕኖ ላይ የተመሰረተ እንዳልሆነ በመግለጽ፣ በቦታው የነበሩትን “መንግሥቱን እንድትወርሱ ለእናንተ መስጠት የአባታችሁ ደስታ ነው” በማለት አስታውሰዋል። ይህ አመለካከት ማህበረሰቦች - ትናንሽም እንኳን ቢሆኑም - ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት እንዲመለከቱ ያስችላቸዋል ብለዋል።
ወንጌልን “በደስታ እና በተስፋ ጽናት” መስበካቸውን እንዲቀጥሉ በማበረታታት፣ በቱርክ ውስጥ ቀድሞውኑ ያሉትን የህይወት ምልክቶች ጠቁመዋል፣ ይህም ስለ እምነት ጥያቄዎች የቤተክርስቲያኒቱን በሮች የሚያንኳኩ ወጣቶች ቁጥርን ያካትታል ብለዋል።
ለተልእኮው ቅድሚያ የሚሰጣቸው ነገሮች
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የቤተክርስቲያኒቱ ቁርጠኝነት በተለይ የሚያስፈልግባቸውን በርካታ ዘርፎች ለይተዋል፡- በኅብረት እና በሃይማኖት ተቋማት መካከል የሚደረግ ውይይት፣ ለአካባቢው ሕዝብ እምነትን ማስተላለፍ እና ለስደተኞች እና ለጥገኝነት ጠያቂዎች ሐዋርያዊ እንክብካቤ በማድረግ የእረኝነት አገልግሎት መስጠት እንደ ሆነ የገለጹት ቅዱስነታቸው ብዙ የሐዋርያዊ አገልግሎት የሚሰጡ ሰዎች እራሳቸው ከሌሎች አገሮች የመጡ መሆናቸውን ተገንዝበዋል እና ይህ እውነታ “አካታች ባሕል እንዲኖር ልዩ ቁርጠኝነት” እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፣ ስለዚህም ወንጌል በቱርክ ባህል እና ቋንቋ ውስጥ በሚስማማ መንገድ ይገለፃል ብለዋል።
የስደተኞችንና የጥገኝነት ጠያቂዎች በጉልህ መገኘት እንደ ፈተናም እንደ እድልም እንደሆነ ገልጸው፣ ቤተክርስቲያኗን በኅብረተሰቡ ውስጥ ካሉት “በጣም ተጋላጭ ከሆኑት” ሰዎች ጋር እንድትቀላቀልና እንድትከተል ጋብዘዋል።
የኒቂያ ጉባኤ እና የዛሬው ሥነ-መለኮታዊ ፈተናዎች
የክርስቲያኖች ሕብረት የታየበት የመጀመሪያው የኒቂያ ጉባኤ የተካናወነበት 1700ኛ የመታሰቢያ ዓመት ክብረ በዓልን ሲያከብሩ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ዛሬ ለቤተክርስቲያኗ ጠቃሚ የሆኑ ሦስት ተግዳሮቶችን ለይተው አቅርበዋል።
በመጀመሪያ፣ የሃይማኖት መግለጫው (ጸሎተ ሐይማኖት) ለአንድነትና እርስ በእርስ ለመረዳዳት እንደ “ኮምፓስ” (አቅጣጫ መጠቆሚያ) ሆኖ ማገልገሉን ቀጥሏል በማለት “አዲስ አሪዮሳዊነት” (ክቡራን እና ክቡራት አንባቢዎቻችን "አዲስ አሪዮሳዊነት" የሚለው ቃል የኢየሱስን መለኮታዊነት በማቃለል ወይም በመካድ የአሪዮስን ጥንታዊ መናፍቅነት የሚያስተጋቡ ዘመናዊ የክርስትና ትርጓሜዎችን ያመለክታል። ይህ ደግሞ ኢየሱስን እንደ ታላቅ የሥነ ምግባር አስተማሪ ወይም መለኮታዊ ሰው አድርጎ መመልከት ወይም በቁሳዊ እና በሰብአዊነት መነጽር መተርጎምን የመሳሰሉ የተለያዩ ቅርጾችን ሊወስድ ይችላል። ምንም እንኳን አንድም እንቅስቃሴ ባይሆንም፣ እንደ ይሖዋ ምሥክሮች ያሉ አንዳንድ ቡድኖች ከጥንታዊው አሪዮሳዊ አስተሳሰብ ጋር የሚመሳሰሉ እምነቶችን ይይዛሉ፣ እና የቅርብ ጊዜ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በወንጌላውያን ዘንድ የአሪዮስን መሰል አመለካከቶች መበራከታቸውን ያመለክታሉ) ብሎ ቅዱስነታቸው የጠሩት የአመለካከት ዝንባሌን አደገኛነት አስጠንቅቀዋል። ሁለተኛው ኢየሱስ እንደ ታሪካዊ ሰው የሚደነቅ፣ ነገር ግን እንደ ሕያው የእግዚአብሔር ልጅ የማይታወቅበት “አዲስ አሪዮሳዊነት” ብለው ቅዱስነታቸው ከገለጹት ዝንባሌ መጠበቅ እንደሚገባ አስጠንቅቀዋል። ሦስተኛ፣ ስለ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ እድገት ትንታኔ የሰጡ ሲሆን የቀደሙትን ጉባኤዎች የተፈጥሮአዊ ሕይወት እድገት በማስታወስ እና አስተምህሮው በማይለወጥ እውነት ላይ የተመሠረተ ቢሆንም፣ ግንዛቤው ሲጨምር አገላለፁን እንደሚያስተካክል አረጋግጠዋል።
የታወቀ የአገልግሎት ሞዴል
ንግግራቸውን ወደ ፍጻሜው ሲያደርሱ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ በቱርክ ያሳለፏቸውን ዓመታት በማስታወስ፣ ለአገሪቱ ያላቸውን ፍቅር እና ተልዕኮውን ያከናወነበትን የማያቋርጥ ቁርጠኝነት ትኩረት ሰጥተው ነበር። በመጨረሻም፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ዛሬም በተመሳሳይ ቁርጠኝነት፣ “የእምነትን ደስታ” ሕያው በማድረግ እና በድፍረት በማገልገል እንደሚቀጥሉ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
