ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ “ምጣኔ ሃብት የምርት ማሳደጊያ መንገድ ብቻ ሊሆን አይገባም” ሲሉ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ መልዕክታቸውን የላኩት ከሮም ወጣ ብሎ በሚገኝ ማሪያፖሊ ማዕከል ውስጥ ከኅዳር 19-21/2018 ዓ. ም. በመካሄድ ላይ በሚገኝ ዓለም አቀፍ “የፍራንችስኮስ ኤኮኖሚ” ስብሰባ ላይ ለተሳተፉት ባቀረቡት ግብዣ ላይ ነው።
“በረሃን ማለምለም”
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ኅዳር 17/2018 ዓ. ም. በቫቲካን ተፈርሞ ይፋ በሆነው መልዕክታቸው፥ አዳዲስ ከሚመሠረቱ የሰው ልጅ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ጋር ከወጣቶች የበለጠ ማንም ሰው ግንኙነት እንደሌለው አፅንዖት ሰጥተዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “በፍራንችስኮስ ኢኮኖሚ” አማካኝነት ቤተ ክርስቲያን ኤኮኖሚያዊ አስተሳሰብን እና ተነሳሽነትን የሚያዳብር መንገድ ማሳደግ እንደምትችል እና በዚህም “በረሃን መለምለም” እንደምትችል አስረድተዋል።
ቅዱስነታቸው ለስብሰባው ተሳታፊዎች በላኩት መልዕክት፥ “ቅዱስ ወንጌል የሰውን ሥራ በመለወጥ የተትረፈረፈ ሕይወት ወደ ዓለም እንዲደርስ የሚያደርጉ ለውጦችን ወደ እኛ ያመጣል” ብለዋል።
ከንቱ የኤኮኖሚ ሥርዓት ሊኖር አይገባም
ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ ዕረፍታቸው በብርሃነ ትንሳኤው መታሰቢያ በዓል ወቅት እንደተከሰተ እና ውርሳቸው ለወጣት የምጣኔ ሃብት ጠበብት ጥሪ መሆኑን አስታውሰዋል።
ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአንድ ወቅት ለ “ፍራንችስኮስ ኤኮኖሚ” ልዑካን ያደረጉትን ንግግር በመጥቀስ፥ “አዲስ አብሮ የመኖር ባሕልን እና ኤኮኖሚያዊ ሥርዓት በመካከላችሁ ተወልዶ ቁሳዊ እና መንፈሳዊ ብልጽግናን እንጂ ብክነትን ማምጣት የለበትም” ማለታቸውን አስታውሰዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ምኞት በመድገም ለስብሰባው ተሳታፊዎች ባስተላለፉት መልዕክት፥ “ውድ ጓደኞቼ! ለጥሪያችሁ ታማኞች ከሆናችሁ ሕይወታችሁ ይለመልማል፣ ለልጆቻችሁ እና ለልጅ ልጆቻችሁ የምትነግሯቸው አስደናቂ ታሪኮች ይኖራችኋል” በማለት ድፍረትን ተመኝተውላቸዋል።
አቅጣጫን በመቀየር እንደገና መጀመር
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ “ኤኮኖሚውን እንደገና ማስጀመር” የሚለውን የዘንድሮው ስብሰባ ጭብጥ በማስታወስ፥ ኤኮኖሚውን እንደገና መጀመር ማለት ከምርት ማሳደጊያ መሣሪያነት በላይ የሆኑ የሕይወት ሥርዓቶችን ወደ ነበሩበት በመመለስ ለሰዎች፣ ለማኅበረሰቦች እና ለጋራ መኖሪያ ምድራችን ጥቅም እንዲውሉ ማድረግ ነው” ብለዋል።
ኤኮኖሚውን እንደገና መጀመር ማለት “የኢ-ፍትሃዊነት ሰንሰለት መበጠስ፣ የቆሰለውን መጠገን እና እያንዳንዱ ሰው ክብርን እና ተስፋን የሚተነፍስበትን ቦታ መፍጠር እና አቅጣጫን በመቀየር እና አዳዲስ መንገዶችን መፈለግ ማለት ሊሆን ይችላል” ብለዋል።
የኢኮኖሚ መዛባት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ወጣቶች በሕይወታቸው፣ በሥራቸው እና በምርምራቸው አማካኝነት የሥርዓት አቅም ማጣትን እንዲገልጹ በማበረታት፥ ይህም በሰዎች መካከል የሚታየውን የእኩልነት ማጣት እና ለተናቁት እና ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች እንክብካቤ አለመስጠትን እንደሚያካትት አስረድተዋል።
“አንድ ላይ ሆነን የእግዚአብሔርን ሕልሞች በደስታ መቀበል የራሳችንን እንዴት እንደሚያሰፉ ማየት እንችላለን” ብለው፥ ግድግዳዎች እና ጭፍን ጥላቻዎች ወድቀው ሰላም በሚያድግበት የሕዝብ ጥረት ውስጥ እንድንገባ ማድረግ እንችላለን” ብለዋል።
ሥራ እና ማኅበራዊ እርምጃ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በመጨረሻም፣ የስብሰባው ተካፋዮች ሥራቸው ከማኅበራዊ እርምጃ ጋር አብሮ መሄድ እንዳለበት እና ካለፉት ጎጂ አዝማሚያዎች ጋር የተሳሰረ መሆን እንደሌለበት አሳስበዋል።
ቅዱስነታቸው በማከልም፥ ወንጌልን እና ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትን በማንበብ መንፈሳቸውን በማሳደግ ወደ ልባቸው እንዲመለሱ አደራ ብለው፥ “እነዚህ ቅዱሳት መጻሕፍት እግዚአብሔር አሁንም ድምፁን የሚያሰማበት እና ራእዮቻችንን የሚያነሳሳበት መንገዶች ናቸው” ሲሉ አስረድተዋል።
“መለኮታዊውን ኤኮኖሚ ካወቃችሁ ጥሩ ሥራ ፈጣሪዎች እና ጥሩ የምጣኔ ሃብት ጠበብት ትሆናላችሁ፥ ይህም ከእኛ በፊት የቀረቡ እና አሁንም እየቀረቡ የሚገኙ የብዙ ምስክሮች ምስጢር ነው” ብለው፥ “ወጣቶች ሆይ! በኅብረት ወደፊት እንጓዝ!” በማለት መልዕክታቸውን ደምድመዋል።
