ር.ሊ.ጳ ሊዮ፦ ታማኝነት የተወለደው ከሙታን ከተነሳው ክርስቶስ ጋር ከተገናኘን በኋላ ነው ማለታቸው ተገለጸ!
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሐሙስ ዕለት የኢየሱስ እና የማርያም የገዳማዊያት ማሕበር አባላት እና የቅዱስ ቻርለስ ቦሮሜኦ ሚስዮናውያን እህቶች ማሕበር፣ የስክላብሪኒያውያን አጠቃላይ ጉባኤ ላይ ተሳታፊዎችን ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት ስብሰባዎቻቸውን በጸሎት፣ በማዳመጥ እና ከተነሳው ጌታ ጋር በመገናኘት ላይ የተመሠረተ የእድሳት ጊዜ አድርገው እንዲኖሩ አበረታተዋል።
በግንኙነቱ ወቅት የርዕሰ ሊቀ ጳጳሳቱን እና የአጠቃላይ ጉባኤ ተሳታፊዎች ተወካዮችን ሲቀበሉ፣ ለአገልግሎታቸው ምስጋናቸውን ገልጸዋል እና አዲስ ለተመረጡት የበላይ ዋና አለቃ መልካም ምኞታቸውን አቅርበዋል። የሁለቱ ማሕበራት አጠቃላይ ጉባኤዎች “በተለያዩ ሁኔታዎች የተወለዱ ቢሆንም ለድሆች ተመሳሳይ ፍቅር” እና በጋራ ርህራሄ አንድነት የተሳሰሩ መሆናቸውን አስታውሰዋል።
“ሁሉም የሚጀምረው”
ለተመሳሳይ አጠቃላይ ጉባኤዎች የተመረጡትን ጭብጦች በማሰላሰል - “ኢየሱስ ራሱ ቀርቦ ከእነርሱ ጋር ይሄድ ነበር” (ሉቃ 24:15) እና “በምትሄጅበት እሄዳለሁ" (ሩት 1:16) - ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እነዚህ የእግዚአብሔርን ተነሳሽነት እና የሰውን ምላሽ የሚገልጹ መሆናቸውን ተናግረዋል።
“በቅዱስ ሉቃስ ወንጌል ውስጥ ኢየሱስ ከኤማሁስ ደቀ መዛሙርት ጋር በመንገድ ጉዞዋቸው ላይ ሲቀላቀላቸው እና ከእነርሱ ጋር ሲሄድ እናያለን፣ እንጅራውን በመቁረስ እንዴት እንዲያውቁት እንደመራቸው” የተናገሩት ቅዱስነታቸው ሩትን በተመለከተ ግን “ምንም እንኳን አለማድረግ ብትችልም፣ አማቷን ናኦሚን ወደ ባዕድ አገር ተከትላት እንደምትሄድ እናያለን፣ እስከ መጨረሻው ድረስ አማቷን ለመንከባከብ ወደ ባዕድ አገር አብራት ትሄዳለች” ሲሉ ቅዱስነታቸው ተናግረዋል።
የኢየሱስና የማርያም ገዳማዊያት ማሕበር መስራች የሆኑት ቅድስት ክላውዲን ቴቬኔት እና ቅዱስ ጆቫኒ ባቲስታ ስካላብሪኒ፣ ከብፅዕት አሱንታ ማርቼቲ እና ከስክላብሪኒያን እህቶች መስራቾች ከተከበሩት ጁሴፔ ማርቼቲ ጋር በመሆን፣ ታላቅ የፈተና ጊዜ እንደገጠማቸው አስታውሰዋል።
“የእንደዚህ ዓይነት ታማኝነት ምስጢር፣ ከትንሣኤው ኢየሱስ ጋር ባደረጉት ግንኙነት ውስጥ ይገኛል። ሁሉም ነገር የጀመረው ለእነሱም ሆነ ለእናንተ ከኢየሱስ ጋር በመገናኘታችሁ የተነሣ የሚመነጭ ነው” ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አረጋግጠዋል።
ጸሎት፣ ጸጥታ እና ማዳመጥ
የአጠቃላይ ዋና ስብሰባቸውን አስፈላጊነት በማጉላት፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እህቶችን ኢየሱስ “ከጎናችሁ እንዲሄድ እና ታሪካችሁን በፋሲካ ብርሃን እንደገና እንድታነቡ እንዲረዳችሁ ኢየሱስን ወደ ሕይወታችሁ ልትጋብዙ ይገባል” ሲሉ ተናግረዋል።
“በአንድ አጠቃላይ ዋና ስብሰባ ውስጥ በጣም አስፈላጊዎቹ ግንዛቤዎች የሚገኙት በጉልበታችን ላይ ነው፣ እናም በስብሰባ ክፍሎች ውስጥ የሚበቅለው ነገር በቅዱስ ቁርባን ማስቀመጫ ፊት እና ቃሉን በማዳመጥ ሊዘራ እና ሊፈተሽ ይገባዋል” ሲሉ ቅዱስነታቸው አክለው ገልጸዋል።
ተሳታፊዎቹን “በሥራችሁ ሁሉ ለጸሎት እና በጸጥታ በሚደረግ ጸሎት በቂ ቦታ ስጡ” ሲሉ አሳስበዋል፣ “እርስ በርሳችን በእውነት ማዳመጥ የምንማረው ጌታን በማዳመጥ ብቻ ነው” በማለት አስታውሰዋል።
በሚሰቃዩ ሰዎች ውስጥ የእግዚአብሔርን ፊት መፈለግ
የቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊን በመጥቀስ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እህቶች “በችግር ውስጥ ባሉ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን የእግዚአብሔርን ፊት” እንዲፈልጉ እና በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ “ቃል ኪዳን፣ ተስፋ፣ የመለኮታዊ መገኘት” እንዲመለከቱ ጥሪ አቅርበዋል።
“ይህ ድፍረትን ይጠይቃል” ብለዋል፣ “የራሳችንን ደህንነት ትተን ሳንፈራ መከራ የሚደርስባቸውን ሰዎች ፊት እንድንመለከት እና ጌታ ከጠየቀው ወደ አዲስ መንገዶች እንድንሄድ እንደ ተጠራን ልንገነዘብ ይገባል” ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው ንግግራቸውን ደምድመዋል።
