ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በላቴራን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ዘመን መጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በላቴራን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ዘመን መጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት ላይ   (ANSA)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የላቴራን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ እውነትን እንዲመሰክር አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የ2025-2026 (እ.አ.አ.) የትምህርት ዘመን የሚጀምረውን በሮም የሚገኝ የላቴራን ጳጳሳት ዩኒቨርሲቲን ጎብኝተዋል። ቅዱስነታቸው ዩኒቨርሲቲውን በጎበኙበት ወቅት ባደረጉት ንግግር በልባቸው ውስጥ ለተቋሙ ልዩ ቦታ እንዳለው ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሮም የሚገኘው የላቴራን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ርዕሠ ሊቃነ  ጳጳሳት ዮሐንሳ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደ ጎርጎሮሳያኑ በ 1980 ዓ. ም. ባደረጉት ታሪካዊ ንግግር፥ “የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዩኒቨርሲቲ” ተብሎ የሚታወቅ ሲሆን ዘንድሮ 253ኛውን የትምህርት ዘመን ጀምሯል።

ዓርብ ኅዳር 5/2018 ዓ. ም. ጠዋት የዩኒቨርሲቲው ቻንስለር እና የሮም ሀገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ባልዳዛሬ ሬይና፣ የዩኒቨርሲቲው አስተዳዳሪ ሊቀ ጳጳስ አቡነ አልፎንሶ ቪ. አማራንቴ፣ የአስተባባሪ ምክር ቤቱ አባላት፣ ፕሮፌሰሮች፣ ተማሪዎች፣ የሲቪል እና የሃይማኖት ባለስልጣናት እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በዩኒቨርሲቲው የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ “Dies Academicus” ወይም “የትምህርት ቀን” በሚል ርዕሥ የተዘጋጀውን የትምህርት ዓመት መጀመሪያ አስተንትኖ ላይ ተሳትፈዋል።

በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት አስተምህሮ ላይ የተመሠረተ ተልዕኮ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በአዳራሹ ለተሰበሰቡት እንግዶች ባሰሙት ንግግር፥ “የላቴራን ዩኒቨርሲቲ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ልብ ውስጥ ልዩ ቦታ እንደሚይዝ ገልጸው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ትልቅ ህልም እንዲያልም፣ የነገው ክርስትና ሊገኝ በሚችላቸው ቦታዎች ላይ እንዲያስብ እና ለዚህም በደስታ እንዲሠራ የሚያበረታቱ መሆናቸውን ገልጸው፥ “ሁሉም ኢየሱስ ክርስቶስን እና የሚመኙትን ሙላት በእርሱ በኩል እንዲያገኙ” በማለት ምኞታቸውን ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በንግግራቸው፥ ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲው ከሌሎች ታዋቂ የትምህርት ተቋማት በተለየ መንገድ፣ በሮም ከሚገኙትም በተለየ፥ የምሥረታውን ታሪክ ለመጠበቅ ወይም ለማዳበር ሳይሆን ነገር ግን በልዩ አቅጣጫው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን አስተምህሮን መከተል ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

በሮም የሚገኘው የላቴራን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ በተፈጥሮው እና በተልዕኮው “የዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት የሚዳብርበት፣ የሚወሰድበት፣ የሚብራራበት እና አውድ የሚያወጣበት ልዩ ማዕከል ነው” ሲሉ ተናግረው፥ በዚህ መልኩ፣ የሮም ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ጳጳሳዊ ምክር ቤቶችም በዕለት ተዕለት ሥራቸው ሊያመኩበት የሚችል ተቋም ነው” በማለት አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “ይህ የዩኒቨርሲቲው ተልዕኮ በአውሮፓ፣ በእስያ እና በአሜሪካ በሚገኙ 28 ተዛማጅ ተቋማት ውስጥ እንደሚከናወን አፅንዖት ሰጥተው፥ “ሰፊ የተለያዩ ባህሎች እና ልምዶች ባለጠግነትን የሚገልጽ እና በተመሳሳይም ለቅዱስ ጴጥሮስ ሐዋርያዊ ትምህርት አንድነትን እና ታማኝነትን ይፈልጋል” በማለት ተናግረዋል።

እምነት፣ የእውነት ፍለጋ እና ውይይት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በመቀጠልም፥ “በዛሬው የባሕል ሁኔታዎች እና ፈተናዎች ውስጥ እያደገ የመጣውን ባዶነትን ለመቋቋም እና ግልጽ ለማድረግ በእምነት ላይ ማሰላሰል አስፈላጊ እንደሆነ አፅንዖት ሰጥተው፥ በተለይ የነገረ-መለኮት ፋኩልቲው በዘመናዊ ሁኔታዎች ውስጥ የእምነትን ውበት እና ተዓማኒነት በማጉላት እና ግለሰቦችን እና ማኅበረሰቦችን የመለወጥ ችሎታውን በተጨባጭ እንዲያስይ አሳስበዋል።

የፍልስፍና፣ የሕግ፣ የሰላም ሳይንስ እና የሥነ-ምህዳር ትምህርቶች

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “የፍልስፍና ጥናት በሰው አእምሮ በኩል እውነትን ወደ መፈለግ እንዲያመራ አሳስበው፥ ከባሕል ጋር በተለይም ከክርስቲያን ራዕይ ጋር ለመወያይት ክፍት ሊሆን ይገባል” ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ለብዙ ዘመናት ጉልህ ሚና የተጫወቱት የሕገ ቀኖና እና የሲቪል ሕግ ፋኩልቲዎች በሲቪል የሕግ ሥርዓቶች እና በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መካከል ያለውን ግንኙነት እንዲመረምሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ቅዱስነታቸው በተጨማሪም የሰላም፣ የሥነ-ምህዳር እና የአካባቢ ጥናቶች በሚቀጥሉት ዓመታት ውስጥ ለዲግሪ ፕሮግራሞች ልዩ ትኩረት ሰጥተው በመዋቀር የበለጠ ተቋማዊ ቅርፅ እንደሚይዙ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

“ሰላም በእርግጥ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ስጦታ ነው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ​​ነገር ግን በየቀኑ መገንባትን የሚጠይቅ እንዲሁም ወደ አንድ ወጥ የሥነ-ምህዳር መንገድ የሚያመሩ ብሔራዊ እና ዓለም አቀፍ ሂደቶችን መደገፍን የሚጠይቅ መሆኑን ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ዩኒቨርሲቲው “የክርስትና እምነትን ምስጢር በጋለ ስሜት መመርመርን እንዲቀጥል እና ዘወትርም ከዓለም፣ ከኅብረተሰብ እና ከዛሬዎቹ ጥያቄዎች እና ተግዳሮቶች ጋር መነጋገርን እንዲለማመድ” በማበረታታት ንግግራቸውን አጠናቀዋል።

“ከተቋሙ ዓላማ ውጭ የሆኑ የትምህርት ዘርፎች”

የዩኒቨርሲቲው ቻንስለር እና የሮም ሀገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ባልዳዛሬ ሬይና በአስተንትኖ መግቢያ ባደረጉት የሰላምታ ንግግር፥ በሮም የሚገኘው የላቴራን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ 130 መምህራንን፣ 34 ባለሥልጣናትን እና የአስተዳደር ሠራተኞችን እንዲሁም ከአንድ ሺህ በላይ ተማሪዎችን ያቀፈው መሆኑን በማመላከት ለፈረጀ ብዙ የትምህርት ዘርፎች ጥልቅ ቁርጠኝነት ያለው መሆኑን አስረድተዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ባልዳዛሬ ሬይና ዩኒቨርሲቲው ምንም እንኳን በሥነ-ሕዝብ እና በጥሪ መቀነስ እንዲሁም በተፈጠረው የኢኮኖሚ ቀውስ የተጎዳ ቢሆንም ነገር ግን በምርምር እና በአስተዳደር ዘርፍ አዳዲስ መንገዶችን ለማሰስ እየሞከረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

“ከተቋሙ ዓላማ ውጭ የሆኑ የትምህርት ዘርፎችን እየሞከርን እንገኛለን” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ባልዳዛሬ ሬይና የምርምር እና የማስተማር እንዲሁም ለቅዱስ ጴጥሮስ ሐዋርያዊ አስተምህሮ ምላሽ የሚሰጡ አዳዲስ የትምህርት ዓይነቶችን በመንደፍ እና ከዚህ በፊት በተቋሙ ያልታወቁ ኮርሶችን ለማስተዋወቅ እየሞከርን እንገኛለን” ብለዋል።

 

15 Nov 2025, 19:55