ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ “ሰላምን ለማዳበር ከተፈለገ ፍጥረትን መንከባከብ ይገባል” ሲሉ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በብራዚል ቤሌም ከተማ ለሚካሄደው 30ኛው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP30) ለሚሰበሰቡት የዓለም መሪዎች በላኩት መልዕክት፥ መሪዎቹ ፍጥረትን ለመንከባከብ ደፋር እና ተጨባጭ ቁርጠኝነትን እንዲያሳዩ በማሳሰብ፥ ሰላም እና የአካባቢ ጥበቃ በማይነጣጠል ሁኔታ የተሳሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛን መልዕክት ለጉባኤው ተካፋዮች ያሰሙት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒተሮ ፓሮሊን፥ ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው፥ “ሰላምን ለማዳበር ከተፈለገ ፍጥረትን መንከባከብ ይገባል” ማለታቸውን በማስታወስ፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ መልዕክት የጋራ መኖሪያ ቤታችን የሆነውን ምድራችንን መንከባከብ የሞራል ግዴታ እና ወደ ዘላቂ ሰላም የሚያደርስ መንገድ በመሆኑ ላይ ያላቸውን እምነት የሚገልጽ እንደሆነ አስረድተዋል።
ሰላም እና ፍጥረት እርስ በርስ የተሳሰሩ ናቸው
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ለጉባኤው በላኩት መልዕክት፥ የዓለም ትኩረት ብዙውን ጊዜ በጦርነት እና በግጭቶች ላይ ያተኮረ ቢሆንም፥ ለፍጥረት ተገቢው ክብር ባለመሰጠቱ፣ የተፈጥሮ ሃብቶችን በመዝረፍ እና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የኑሮ ጥራት ቀስ በቀስ በመቀነሱ ምክንያት ሰላም በእጅጉ አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ገልጸዋል።
“እነዚህ ተግዳሮቶች በምድሪቱ ውስጥ ያሉ ፍጥረታትን እና የሰውን ሕይወት በሙሉ አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ ዓለም አቀፍ ትብብር፣ እግዚአብሔር የሰጠውን የእያንዳንዱ ሰው የሕይወት ቅድስናን እና የጋራ ጥቅምን ማዕከል የሚያደርግ የተቀናጀ ሁለገብነት ዕይታ ሊኖር ይገባል” ብለው፥ “የዓለም ሙቀት እየጨመረ ባለበት እና በግጭቶች መካከል የሚደረግ ይህ ጉባኤ የተስፋ ምልክት መሆን አለበት” ሲሉ ቅዱስነታቸው አሳስበዋል።
የሞራል ኃላፊነት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊን ቃላት በማስታወስ ባስተላለፉት መልዕክታቸው፥ ሥነ ምህዳራዊ ቀውስ “በአገሮች መካከል አዲስ የአብሮነት ስሜት የሚጠይቅ የሞራል ጉዳይ” ነው ሲሉ ተናግረው፥ “መንግሥታት ሰላማዊ እና ጤናማ የሆነ የተፈጥሮ አካባቢን እና ማኅበራዊ ሕይትን ለማስተዋወቅ በተጓዳኝ መንገዶች ኃላፊነትን መጋራት አለባቸው” ብለዋል።
ለአየር ንብረት ለውጥ እጅግ ተጋላጭ የሆኑት እና በደን መጨፍጨፍ እና በአካባቢ ብክለት ምክንያት የሚደርሱ አስከፊ ውጤቶችን የሚሸከሙት የመጀመሪያዎቹ ደሆች እንደሆኑ ገልጸው፥ በመሆኑም ለፍጥረት ድኅንነት መጨነቅ የሰብዓዊነት እና የአንድነት መገለጫ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተው፥ “ውይይቶቻችንን እና ሃሳቦቻችንን በኃላፊነት እና በፍትህ ላይ ወደተመሠረቱ ትክክለኛ ምርጫዎች እና ተግባሮች መለወጥ አለብን” ብለዋል።
ከቃላት ወደ ተግባር መሸጋገር
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2015 ዓ. ም. በፓሪስ የተደረሰውን ስምምነት ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “በዚያ ስምምነት ውስጥ የተቀመጡትን ግቦች ለማሳካት የሚወሰደው መንገድ ረጅም እና ውስብስብ መሆኑን ቀጥሏል” ብለው፥ አገራት የፓሪስን ስምምነት እና የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፍ ኮንቬንሽን በድፍረት ተግባራዊ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
ቅዱስነታቸው የነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ውዳሴ ላንተ ይሁን!” ሐዋርያዊ ቃለ-ምዕዳን አሥረኛ ዓመት መታሰቢያን በማስታወስ እንደተናገሩት፥ “የአየር ንብረት ጉዳይ ሁሉን ሰው የሚመለከት የጋራ ጉዳይ እና ሁሉም ሰው እንዲሳተፍበት የሚጠይቅ ነው” ሲሉ አስታውሰዋል።
ሰላሳኛውን ዓለም አቀፍ የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ጉባኤን (COP30) የሚካፈሉት በሙሉ በአየር ንብረት ቀውስ ምክንያት የሚሰቃይ የሰው ልጅን በማሰብ፥ በአስተሳሰባቸው እና በድርጊታቸው የሥነ-ምህዳር ለውጥን በድፍረት እንዲቀበሉት ምኞታቸውን ገልጸዋል።”
አዲስ የፋይናንስ እገዛ ራዕይ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በመቀጠልም፥ ሁሉም አገሮች በተለይም ድሆችን፣ ለአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎች እጅግ የተጋለጡትን እና የዜጎች ክብር መጠበቅን ለማረጋገጥ ሲሉ አዲስ የሰው ልጅን ማዕከል ያደረገ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ዕቅድ በማውጣት አቅማቸውን እንዲያሳኩ ጥሪ አቅርበው፥ እንዲህ ዓይነቱ መዋቅር በሥነ-ምህዳር እና በውጭ ዕዳ መካከል ያለውን ግንኙነት ያገናዘበ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።
ቅዱስነታቸው በተጨማሪም፥ የግል፣ የቤተሰብ እና የፖለቲካ ምርጫዎች የዕለት ተዕለት የሰው ልጅን የወደፊት ዕጣ ፈንታን እንዴት እንደሚቀርጹ ለማወቅ የሚያግዝ የተዋሃደ የሥነ-ምህዳር ትምህርት እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል።
የወደፊት ቁርጠኝነት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በብራዚል-ቤሌም ከተማ ከኅዳር 1-5/2018 ዓ. ም. ለሚካሄው ሰላሳኛ ዓለም አቀፍ የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ጉባኤ (COP30) ያስተላለፉትን መልዕክት ሲያጠቃልሉ፥ የጉባኤው ተሳታፊዎች ሰላማዊ ዓለምን ለመገንባት በእግዚአብሔር የተሰጠንን ፍጥረት እንዲጠብቁ እና እንዲንከባከቡ አሳስበዋል።
ጉባኤውን የሚሳተፉት በሙሉ ለሰው ልጅ የጋራ ጥቅም እና የወደፊት ዕጣ ፈንታ አስፈላጊ ውሳኔዎችን ለማድረግ በጸሎታቸው እንደሚያግዟቸው አረጋግጠው፥ ሥነ-ምህዳራዊ ለውጡ ፍጥረትን እና የሰውን ክብር የሚጠብቅ አዲስ አብሮነትን የሚያነሳሳው ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
