ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ኒቂያ ክርስቲያኖችን በሙሉ ወደ አንድነት እንደምትጋብዛቸው ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቱርክ በማድረግ ላይ ባሉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት በኒቂያ ካገኟቸው የልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ጋር የኅብረት ጸሎታቸውን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ኒቂያ ክርስቲያኖች ከአመፅ እና ከግጭት ይልቅ ወደ አንድነት እንዲያመሩ የምትጋብዝ መሆኗን ተናግረው፥ ክርስቲያኖች በሙሉ የወንድማማችነት፣ የውይይት እና የትብብር መንገድን እንዲከተሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ እንደተጠቀሰው በጥንታዊቷ ኒቂያ የተካሄደውን የመጀመሪያው የክርስቲያኖች የአንድነት ጉባኤ 1,700ኛ ዓመት መታሰቢያን ከ27 ልዩ ልዩ የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ጋር አክብረዋል።

የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች የጋራ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት የተካሄደው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በቱርክ ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረግ በጀመሩ በሁለተኛ ቀን ላይ እንደሆነ ታውቋል።

ቅዱስነታቸው ለአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ባደረጉት ንግግር፥ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ይህን ታሪካዊ የመታሰቢያ በዓልን አብረው እንዲያከብሩ በታላቅ ጥበብ እና አርቆ አስተዋይነት ጥሪ ላቀረቡት ለቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ ለብጹዕ ወቅዱስ ቤርቶሎሜዎስ ቀዳማዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ቅዱስነታቸው በተጨማሪም በመታሰቢያ በዓሉ ላይ የተገኙት የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች እና ዓለም አቀፍ የክርስቲያን ኅብረት ተወካዮች አመስግነዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የኒቂያው ጉባኤ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ325 ዓ. ም. መካሄዱን አስታውሰው፥ ጉባኤው ዛሬም ቢሆን ክርስቲያኖች በሙሉ ኢየሱስ ክርስቶስ ማን እንደሆነ ራሳችንን እንድንጠይቅ የሚጋብዘን መሆኑን ተናግረዋል።

“ይህ ጥያቄ ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ አንድ ዓይነት የተሃድሶ እንቅስቃሴ መሪነት ደረጃ ዝቅ ለሚያደርጉት እና በመጨረሻም የተሳሳተ መልዕክት በማስተላለፍ ወደ ሐዘን እና ግራ መጋባት ለሚመሩት በተለይም ለክርስቲያኖች አስፈላጊ ጥያቄ ነው” ብለዋል።

በወቅቱ ጉባኤው የምስጢረ ሥጋዌን እውነታን ችላ በማለት ኢየሱስ በሙላት መለኮታዊ እንዳልሆነ እና በእግዚአብሔር እና በሰው ልጆች መካከል አስታራቂ ብቻ እንደሆነ በማድረግ ለተናገረው የእስክንድሪያው ካኅን አባ አርዮስ ምላሽ ለመስጠት የተካሄደ እንደ ነበር ይታወሳል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “እግዚአብሔር ሰው ካልሆነ ሟች ፍጥረታት የማይሞተው ሕይወት ተካፋዮች ሊሆኑ እንዴት ይችላሉ?” ሲሉ ጠይቀው፥ “ይህ አስተሳሰብ በኒቂያ ጉባኤ ወቅት ብቻ ሳይሆን ዛሬም ቢሆን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ እኛ ሰው በመሆን የመለኮታዊነት ተካፋዮች በሚያደርገን በእግዚአብሔር ባለን እምነት ላይ አደጋን ደቅኗል” ሲሉ ተናግረዋል።

የኒቂያ ጉባኤ ዛሬ የሐዋርያት ጸሎተ ሐይማኖት ብለን በምንጠራው እና ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት እና ክርስቲያን ማኅበረሰቦች በሚመሰክሩት በኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት ላይ መስማማቱን አስታውሰው፥ “የእምነት ምልክት ክርስቲያኖች ወደ ሙሉ ኅብረት በሚያደርጉት ጉዞ ውስጥ መሠረታዊ ጠቀሜታ አለው” ሲሉ አስረድተዋል።

“እምነት፥ ‘ከዘመናት በፊት ከአብ የተወለ እና ከአብ ጋር አንድ የሆነ፣ የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ (የኒቂያ የሐዋርያት ጸሎተ ሐይማኖት መግለጫ) ነው” ብለው፥ ይህም ክርስቲያኖችን በሙሉ አንድ የሚያደርግ ጥልቅ ትስስር ነው” ብለዋል።

አቡነ አንቶኒ ፖጎ በኒቂያ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት አስፈላጊነት ላይ አስተያየታቸውን ሲሰጡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ክርስቲያኖች በሙሉ አሁን ያለውን የአንድነት ትስስር ተቀብለው በኢየሱስ ክርስቶስ የተገለጠውን የእግዚአብሔር ቃል በመከተል በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በጋራ ፍቅር እና ውይይት እንዲጓዙ አደራ ብለዋል።

“ክርስቲያኖች መከፋፈልን በማሸነፍ እና እርስ በርስ በመታረቅ፥ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እና ለሰው ልጅ በሙሉ ስለተሰጠው የተስፋ አዋጅ የበለጠ ተዓማኒነት ያለውን ምስክርነት መስጠት ይችላሉ” ብለው፥ በዓለማችን ውስጥ የክርስቲያኖች አንድነት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አስታውሰዋል።

“በኢየሱስ ክርስቶስ በሚያምኑት መካከል ሙሉ ኅብረትን የመፍጠር ፍላጎት ዘወትር በሁሉም የሰው ልጆች መካከል የወንድማማችነት ፍለጋን ያካትታል” ሲሉ ተናግረው፥ ዘራቸው፣ ዜግነታቸው፣ ሃይማኖታቸው ወይም የግል አመለካከታቸው ምንም ይሁን ምን የሁሉም ሰዎች መብቶች እና ክብር እውቅና እንዲሰጣቸው ጥሪ አቅርበዋል።

ሃይማኖቶች እውነትን በማገልገል ረገድ ያላቸውን ሚና በመደገፍ ግለሰቦች ውይይትን እና እርስ በርስ የመከባበር መንገድን እንዲፈልጉ አበረታተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በንግግራቸው፥ “ሃይማኖት ጦርነትን፣ ዓመፅን ወይም ማንኛውንም ዓይነት ጽንፈኝነትን እና አክራሪነትን እንዳይደግፍ አጥብቀን መከላከል አለብን” ብለው፥ “በምትኩ የወንድማማችነት፣ የውይይት እና የትብብር መንገዶችን ሊከተል ይገባል” ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በመጨረሻም፥ የኒቂያ ጉባኤ 1,700ኛ ዓመት መታሰቢያ ክብረ በዓል የተትረፈረፈ የእርቅ፣ የአንድነት እና የሰላም  ፍሬዎችን እንዲያስገኝ እግዚአብሔር ይርዳን” በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

በጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ ማጠቃለያ የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች እና የኅብረቱ አባላት ከወልድ የሰረጸ የሚለውን እና ሥነ-መለኮታዊ ክርክር የሚያነሳ የላቲኑን ትርጉም ሳይጠቅሱ የኒቂያ ጉባኤ ጸሎተ ሐይማኖትን በኅብረት አድርሰዋል።

የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሥነ-ሥርዓት፥ ህዳር 19/2018 ዓ. ም.

 

29 Nov 2025, 16:27