ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ ቴክኖሎጂ የክርስትና እምነትን በተጨባጭ መኖርን ሊረዳ እንደሚችል አስገነዘቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በአሜሪካ-ኢንዲያናፖሊስ ከተማ ውስጥ ከተሰበሰቡት ከ15,000 በላይ አዳጊ ወጣቶች ጋር በአውታረ መረብ አማካይነት ተገናኝተዋል። ቅዱስነታቸው ለካቶሊካዊ ወጣቶች ባስተላለፉት መልዕክት፥ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ወዳጅነት እንዲመሠርቱ፣ እምነታቸውን ለማጠናከር ቴክኖሎጂን በጤናማ መንገድ እንዲጠቀሙ እና የፖለቲካ አቋምን መሠረት በማድረግ ስለ ቤተ ክርስቲያን መናገር እንደሌለባቸው አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በአሜሪካ ኢንዲያናፖሊስ ከተማ በተካሄደው ብሔራዊ የካቶሊክ ወጣቶች ጉባኤ (NCYC) ላይ ከተገኙት ከ15,000 በላይ ወጣቶች ጋር ዓርብ ኅዳር 12/2018 ዓ. ም. በቪዲዮ ምስል ተገናኝተዋል።

በኬቲ ፕሬጃን ማክግራዲ በተመራው ዝግጅት ላይ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በቪዲዮ የተገናኙት ስድስት ወጣት ካቶሊካውያን፥ ቅዱሳት ምስጢራትን፣ የአእምሮ ጤናን፣ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን “አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ” እና የቤተ ክርስቲያኗን የወደፊት ሁኔታን በተመለከቱ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ሃሳባቸውን እንዲያካፍሉ ጠይቀዋል።

ቅዱስነታቸው በመክፈቻ ንግግራቸው፥ ጊዜያቸውን ሰጥተው በአካል ለመገናኘት የወደዱትን የአሜሪካ ወጣቶችን አመስግነው፥ ወጣቶቹ በቁምስና ማኅበረሰቦቻቸው መካከል ንቁ አባላት እንዲሆኑ አበረታተዋል።

ጉባኤው ወጣቶቹ በመስዋዕተ ቅዳሴ ላይ እንዲገኙ፣ በቅዱስ ቁርባን ፊት እንዲጸልዩ እና ንስሐን እንዲገቡ ዕድል የሰጣቸው ሲሆን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛም እነዚህ ተግባራት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ለመገናኘት እውነተኛ ዕድሎች እንደሆኑ ተናግረዋል።

በቅዱሳት ምስጢራት ውስጥ የሚገኝ ሕይወት

ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የቀረበላቸው የመጀመሪያው ጥያቄ፥ ወጣቶች ኃጢአትን በሚሠሩበት ጊዜ ወይም ሌሎችን በሚሲያሳዝኑ ጊዜ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረትን ስለመቀበል የሚናገር ሲሆን፥ ሁሉም ሰው ባጠፋ ጊዜ ኑዛዜን በመግባት የእግዚአብሔርን ምሕረት እንደሚጠይቅ እና እርሱም በእውነት ይቅር የሚል መሆኑን ለማመን ጥረት እንደሚያደርግ አስረድተዋል።

“ኃጢአት የመጨረሻ ቃል የለውም” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “ምሕረትን በምንለምንበት ጊዜ እግዚአብሔር ዘወትር ይቅር እንደሚለን ተናግረው፥ ነፍስሔ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ይቅርታን መጠየቅ የሚሰለቸን እኛ እንጂ እግዚአብሔር ይቅር ከማለት ፈጽሞ አይሰለቸንም” ማለታቸውን አስታውሰዋል።

“የእግዚአብሔር ልብ ከእኛ ልብ ፈጽሞ የተለየ ነው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የጠፉትን በጎች ከመፈለግ ፈጽሞ እንደማይሰለች ተናግረው፥ ወጣቶች ኢየሱስ ክርስቶስን በቅዱሳት ምስጢራት ውስጥ እንዲያገኙት ጠይቀው፥ ኃጢአታቸውን በግልጽ በመናዘዝ የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት በካኅን ስርየት እንዲቀበሉ አሳስበዋል።

ከጭንቀት እና ከአእምሮ ሕመም ጋር መታገል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በመቀጠልም፥ ሐዘንን ወይም ጭንቀትን የመሳሰሉ የአእምሮ ጤና ችግሮች በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡ ሲሆን፥ ሁሉም ሰው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ጥልቅ ግንኙነት እንዲመሠርት የጋበዙት ቅዱስነታቸው፥ ወጣቶች ችግሮቻቸውን በጸሎት አማካይነት ለእግዚአብሔር በአደራ እንዲሰጡ አሳስበዋል።

“በጸጥታ መንፈስ በልባችን ውስጥ ስላለው ነገር በሐቀኝነት መናገር እንችላለን” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “በቅዱስ ቁርባን ስግደት ወቅት ኢየሱስን በተባረከው ቅዱስ ቁርባን ውስጥ ማየት እና በፍቅር እንደሚመለከተን ማወቅ እንችላለን” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አክለውም፣ ወጣቶች እግዚአብሔር በወላጆች፣ በመምህራን፣ በካህናት እና በወጣት ሐዋርያዊ አገልጋዮች አማካኝነት ሊያነጋግራቸው ስለሚችል የሚታመኑባቸው ታማኝ አዋቂዎችን ማግኘት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

እንዲሁም ሕይወት ግራ የሚያጋባ ወይም አስቸጋሪ በሚሆንበት ጊዜ ኢየሱስን እንዲፈልጉ ለሚገፋፉ የእውነተኛ ጓደኞች ስጦታን እንዲለምኑ ወጣቶችን ጋብዘዋቸዋል።

“ብዙ ወጣቶች ‘ማንም አይረዳኝም’ ይላሉ” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ነገር ግን ይህ የበለጠ ሊያገልል እንደሚችል አስረድተው፥ “ይህ ሃሳብ በአዕምሮ ውስጥ ከመጣ ‘ጌታ ሆይ! እኔ ራሴን ከምረዳ በላይ አንተ ትረዳኛለህ’ ለማለት መሞከር እና እርሱ ሊመራ እንደሚችል ማመን እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

እምነት እና ቴክኖሎጂ

ቴክኖሎጂ በእምነት ላይ ስላለው ተጽእኖ አስመልክቶ ለሚነሳ ጥያቄ መልስ የሰጡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በሺዎች በሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ከሚገኙ ሰዎች ጋር ለመገናኘት ዘመናዊ መሣሪያዎች የሚሰጡት ጥቅም ገልጸዋል።

“ቴክኖሎጂ ብዙ ነገሮችን እንድናደርግ እና የክርስትና እምነታችንን እንድንኖር በእውነት ሊረዳን ይችላል” ብለው፥ “ለጸሎት፣ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ እና ስለምናምንበት ነገር የበለጠ ለመማር አስደናቂ መንገዶችን ይሰጠናል” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ቴክኖሎጂ እውነተኛ በአካል የሚደረጉ ግንኙነቶችን እና በመስዋዕተ ቅዳሴ ላይ መሳተፍትን ሊተካ በፍጹም የማይችል መሆኑን አስታውሰው፥ ወጣት ካቶሊካውያን በስልካቸው አማካይነት ዓለም አቀፍ ግንኙነት በማድረግ፥ የቴክኖሎጂ አገልጋዮች ከመሆን ይልቅ ቴክኖሎጂን የሕይወታቸው አገልጋይ እንዲያደርጉት ጋብዘዋል።

“ሰው ሠራሽ አስተውሎት ወይም ‘አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ’ የዘመናችን ዋና መለያ ሆኗል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “ደኅንነት የሰው ሠራሽ ‘AI’ ሞዴሎች ዕድገት መቆጣጠር ብቻ ሳይሆን ሰዎች በትምህርት እና በግል ኃላፊነት ጤናማ ውሳኔዎችን እንዲያደርጉ ማስቻልንም ጭምር ያካትታል” ሲሉ ተናግረዋል።

“እያንዳንዱ መሣሪያ የእምነት እና የአዕምሮ ዕድገት ጉዞአችንን መደገፍ አለበት እንጂ እንቅፋት መሆን የለበትም” ብለው፥ በመሆኑም የሰው ሠራሽ አስተውሎት አጠቃቀም እውነተኛ የሰው ልጅ ዕድገትን እንዳይገድብ መጠንቀቅ፣ የነገን ሕይወት የሚጎዳ ቢሆን እንኳ በግል በማሰብ እና ዘዴን በማግኘት እርምጃን መውሰድ በሚቻልበት መንገድ መጠቀም እንደሚገባ አሳስበው፥ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ለዓለም ልዩ ስጦታ መሆናችንን በፍፁም ሊተካ አይችልም” በማለት አስረድተዋል።

የቤተ ክርስቲያን የወደፊት ዕጣ ፈንታ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በመቀጠልም፥ የቤተ ክርስቲያን የወደፊት ዕጣ ፈንታን በማስመልከት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ለጴጥሮስ “የሲኦል በሮች ቤተ ክርስቲያንን አያሸንፉም” ሲል የገባውን ቃል አስታውሰዋል።

“ቤተ ክርስቲያን ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬ እኛን በሚጠይቀን ታማኝ ሆና ወደፊት ለመጓዝ ትዘጋጃለች” ብለው፥ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያንን በሁለት ሺህ ዓመታት ውስጥ በተከሰቱ ችግሮች እና ፈተናዎች መልካከል የመራት መሆኑ አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ “ወጣቶች የቤተ ክርስቲያን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ብቻ ሳይሆኑ የእሷም ጭምር ናቸው” ብለው፥ ወጣቶች በእሁድ ዕለት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ በመሳተፍ እና እምነታቸው ሊያድግ በሚችልባቸው የወጣቶች መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ላይ እንዲሳተፉ አሳስበዋል።

“እግዚአብሔር ለአንድ ልዩ አገልግሎት እየጠራችሁ መሆኑ ከተሰማችሁ ከቁምስና መሪ ካኅን ወይም ከሌላ የቤተ ክርስቲያን መሪ ጋር ተነጋገሩ” ብለው፥ እነርሱ እግዚአብሔር በሚጠይቃችሁ ጉዳይ ላይ እንድታሰላስሉ ሊረዷችሁ ይችላሉ” ብለዋል።

የክርስቶስ ወዳጆች የወንጌል ልኡካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመጨረሻም፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ላሉ ወጣቶች ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ በሚቀጥሉት ዓመታት ውስጥ ወጣቶች ቤተ ክርስቲያንን እንዲያሳድጓት አደራ ብለዋል።ከወጣትነት ፍላጎት የተነሳ ትርጉም ያለውን ነገር ለማድረግ ወጣት ካቶሊካውያን ቤተ ክርስቲያንን ለመገንባት ጊዜያቸውን እና ተሰጥኦአቸውን በልግስና እንዲያቀርቡ ቅዱስነታቸው አሳስበዋል።

እነርሱን ለማግኘት የተፈጠርን በመሆናችን “እውነትን፣ ውበትን እና መልካምነትን በጥልቀት እንናፍቃለን” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ የምንፈልገው ይህ ሃብት ስም ያለው እና በእናንተ ውስጥ መገኘት የሚፈልግ እርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” ብለዋል።

“ወጣቶች የኢየሱስ ክርስቶስ ወዳጆች እና የሰላም ፈጣሪዎች እንዲሆኑ ተጠርተዋል” ብለው፥ የልዩነት ግድግዳን ከመገንባት ይልቅ እርስ በርስ የሚገናኙበትን ድልድይ የሚገነቡ፣ ከመከፋፈል ይልቅ ውይይትን እና አንድነትን የሚያደንቁ ሊሆኑ ይገባል” ብለዋል።

ወጣቶችን “ስለ እምነት መናገር ስትፈልጉ የፖለቲካ አቋማችሁን መሠረት ከማድረግ ተጠንቀቁ” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ቤተ ክርስቲያን የማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል እንዳልሆነች ገልጸው፥ “ይልቁንም በጥበብ እና በፍቅር እንድታስቡና እንድትሠሩ፣ ሕሊናችሁን እንድትገነቡ ትረዳችኋለች” ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው ማጠቃለያ፥ የአሜሪካ ወጣት ካቶሊካውያን በሕይወታቸው ውስጥ የእግዚአብሔርን ጥሪ በማዳመጥ ለጋብቻ፣ ለክኅነት ወይም ለገዳም ሕይወት ባላቸውን ጥሪ ላይ እንዲያስተነትኑ ጋብዘዋቸዋል።

“ሕይወታችሁን ከወንጌል ለበለጠ ለየትኛው ምክንያት መስጠት ትችላላችሁ?” ሲሉ ወጣቶችን ጠይቀው፥ ዓለም የወንጌል ልኡካን እንደሚያስፈልገው እና ከኢየሱስ ክርስቶስ ያገኛችሁትን ብርሃን እና ደስታ እንድታካፍሉት ይፈልጋል” ብለዋል።

 

22 Nov 2025, 16:03