ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ለኢስታንቡል አረጋውያን እናንተ “የሕዝብ ጥበብ” ናችሁ ማለታቸው ተገለጸ።

በቱርክ የሁለተኛ ቀን ሐዋርያዊ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቱርክ በነበራቸው ሁለተኛ ቀን፣ ከማዕከላዊ ኢስታንቡል ውጭ በሚገኘው የድሆች ታናናሽ እህቶች ማሕበር አባላት የሚተዳደሩትን የአረጋውያን የእንክብካቤ መስጫ ተቋም ጎብኝተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ከማዕከላዊ ኢስታንቡል ውጭ በሚገኘው የድሆች ታናናሽ እህቶች ማሕበር አባላት የሚተዳደረው የአረጋዊያን እንክብካቤ መስጫ ተቋም የከተማዋ የተለያዩ አስተዳደግ ላላቸው አረጋውያን መኖሪያ ነው፡ ቱርኮች፣ አርመኖች፣ ከአፍሪካ በርካታ አገሮች የመጡ ስደተኞች እና የኢስታንቡል ታሪካዊ የአይሁድ ሕዝብ አባልም ጭምር።

“ሌላኛው ክርስቶስ ነው” ይላል፣ በኮሪደሩ ግድግዳ ላይ፣ የእያንዳንዱን ነዋሪ የስም ካርድ የሚያሳይ ሰሌዳ አጠገብ የተቀመጠው ጽሑፍ።

የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ በዚህ የአረጋዊያን እንክብካቤ መስጫ ተቋም ቤት ውስጥ የመጀመሪያ ማረፊያ በባንዲራዎችና በአበቦች ያጌጠ ጸሎት ቤት ነበር። እዚያ ወደ 200 የሚጠጉ ሰዎች ቅዱስነታቸውን ለመገናኘት ይጠባበቁ እንደ ነበረ የተዘገበ ሲሆን ሁሉም ነዋሪዎቹ ከፊት ለፊት ተቀምጠው እና ቤቱን በየቀኑ የሚያስተዳድሩት ሰራተኞች ጭምር በስፍራው ተገኝተዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የድሆች ታናናሽ እህቶች ማሕበር ደናግላን ጋር በተገናኙበት ወትት
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የድሆች ታናናሽ እህቶች ማሕበር ደናግላን ጋር በተገናኙበት ወትት   (@Vatican Media)

ሞቅ ያለ አቀባበል

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ወደ መተላለፊያው ሲሄዱ፣ ከኮንጎ፣ ከአንጎላ፣ ከካሜሩን እና ከቡርኪናፋሶ የመጡ ስደተኞችን ያካተተ የሴቶች መዘምራን ቡድን አቬ ማሪያ (ፀጋ የሞላሽ ማርያም ሆይ) እና ላውዴት ዶሚነምን (ጌታን አመስግኑ) የተሰኙ መዝሙሮችን ለቅዱስነታቸው ዘምረዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ብዙ ሰዎችን ተቀብለው፣ ለፎቶግራፍ ቆም ብለው ጥቂት ቃላትን ተለዋወጡ፣ ከዚያም ከቅዱስ ቁርባን ማስቀመጫ ፊት ለፊት ለአጭር ጊዜ በጸሎት ተንበረከኩ።

ከአንድ ወር በፊት ከለንደን የመጡት እህት ማርጋሬት ሴርሰን በድሆች ታናናሽ እህቶች ማሕበር ስም ንግግር አድርገዋል። ለጉብኝታቸው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱን አመስግነዋል፣ ይህም የቤቱን ነዋሪዎች "እግዚአብሔር እጅግ እንደሚወዳቸው" ያሳያል ብለዋል።

ከሌሎች ጋር እና ለሌሎች

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በተራቸው ባደርጉት ንግግር የድሆች ታናናሽ እህቶች ማሕበር እህቶች ላደርጉላቸው አቀባበል  እና ለስራቸው አመስግነዋል። በማሕበሩ መጠሪያ ስያሜ ላይ ጥቂት አስተያየቶችን ሰጥተዋል፣ ይህም "እንድናስብ ያደርገናል" ብለዋል።

"ጌታ ድሆችን ለመርዳት ወይም ለማገዝ ብቻ ሳይሆን እህቶቻቸው እንድትሆኑም ጠርቷችኋል!" ብለዋል። በዚህ መንገድ፣ የታናናሽ እህቶች ማሕበር ስም የክርስቲያን በጎ አድራጎትን ትክክለኛ ትርጉም ፍንጭ ይሰጣል፡- “ለሌሎች ከመሆንዎ በፊት፣ በመጀመሪያ ከሌሎች ጋር በወንድማማችነት ላይ በተመሠረተ ኅብረት ውስጥ መሆን አለብን” ሲሉ ተናግረዋል።

አረጋውያን እንደ ጥበብ ምንጭ

የሊቀ ጳጳሱ ሁለተኛ ምልከታ ለቤቱ አረጋውያን ነዋሪዎች የተነገረ ነበር። በቅልጥፍና እና በቁሳዊ ስኬት በተጠማዘዘ ማህበረሰብ ውስጥ፣ የእርጅና ትክክለኛ ትርጉም የመረሳት አደጋ እንዳለው አስጠንቅቀዋል። ሆኖም፣ የቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ብዙውን ጊዜ እንደሚሉት፣ “አረጋውያን የሰዎች ጥበብ፣ ለልጅ ልጆቻቸው፣ ለቤተሰቦች እና ለኅብረተሰቡ በአጠቃላይ ሀብት ናቸው” ሲሉ የቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የተናገሩትን ቃላት በድጋሚ አስተጋብተዋል።

ጳጳሱ አረጋውያንን “በወንድማማችነት ስም” ስለተቀበሉት ለአረጋዊያን እንክብካቤ መስጫ ተቋሙ “ድርብ ምስጋና” በማቅረብ ንግግራቸውን አጠናቀዋል። አሳቢነት ቀላል እንዳልሆነ እና “ብዙ ትዕግስት እና ጸሎት ይጠይቃል” ሲሉ የተናገሩት ቅዱስነታቸው ከዚያም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ከማህበረሰቡ ጋር ጸለዩ፣ ሐዋርያዊ ቡራኬ እና የመታሰቢያ ስጦታ ቅዱስነታቸው ከሰጡ በኋላ ጉብኝታቸውን አጠናቀዋል።

28 Nov 2025, 16:50