ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ ቤተ ክርስቲያን በችኮላ የማይገነባ ማኅበረሰብ ሥፍራ መሆኗን ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በእግዚአብሔር ታላቅ የግንባታ ሥራ ላይ እንድንተባበር ኢየሱስ ይጠራናል፣ በማዳን ዕቅዱ በጥበብ ይቀርጸናል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ከችግሮቹ በላይ ሮም ውስጥ የሚያድግ ታላቅ መልካም ነገር አለ” ሲሉ ተናግረዋል።
“በራሳችን እና በዙሪያችን ያለውን በመመልከት ከዚያም ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መመልከት እንድንችል እና በዚህም በትህትና እና በትዕግስት መገንባት እንድንችል፣ የቤተ ክርስቲያኗ የሺህ ዓመት ታሪክ እንደሚያስተምረን፣ እውነተኛ የእምነት ማኅበረሰብን፣ የበጎ አድራጎት ተልዕኮን የማስፋፋት፣ የማወጅ፣ የማክበር እና የማገልገል ችሎታ ያለው የቅዱስ ዮሐንስ ዘላተራን ጳጳሳዊ ባሲሊካ የመጀመሪያው መቀመጫ የሆነበትን የሚገልጽ ሐዋርያዊ አስተምህሮን ጠቅሰዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እሁድ ጥቅምት 30/2018 ዓ. ም. በተከበረ የቅዱስ ዮሐንስ ዘላተራን ባዚሊካ በዓል ላይ ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ ቤተ ክርስቲያን እንደ ንቁ የአማኞች ማኅበረሰብ ባላት ተልዕኮ ላይ በማሰላሰል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ወደ 2700 የሚሆኑ ምዕመናን በተገኙበት ሥነ-ሥር ዓት ላይ ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ ለክርስቲያኖች የአምልኮ ነፃነት ከተሰጠ በኋላ በሮማዊ ንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ ትእዛዝ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ313 ዓ. ም. የተገነባውን እና ከጥቂት ዓመታት በኋላ በሲሊቨስተር ቀዳማዊ የተመረቀውን ካቴድራል ጠቃሚ ታሪክ አስታውሰዋል።
ይሁን እንጂ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እናት የሆነው ባዚሊካው ከታሪካዊ መታሰቢያነት ወይም ሐውልትነት በላይ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተው፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በተመረጡ እና በከበሩ ድንጋዮች የተገነባ የሕያው ቤተ ክርስቲያን ምልክት የማዕዘን መሠረት እንደሆነ አስረድተዋል። “እኛም በምድር ላይ ሕያው ድንጋዮች እና እንደ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ የተገነባን መሆናችንን ያስታውሰናል” ሲሉ ገልጸው፥ “የቤተ ክርስቲያን የምእመናን ማህበረሰብ ለቅዱስ ዮሐንስ ዘላቴራን ጳጳሳዊ ባዚሊካ እጅግ ጠንካራ እና አስደናቂ ውጫዊ መዋቅር የሚሰጥ ነው” ሲሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛን ጠቅሰው ገልጸዋል።
“ወንድሞች እና እህቶች፥ ለእግዚአብሔር መንግሥት የምናበረክተው አገልግሎት በችኮላ ሳይሆን ነገር ግን በትጋት ሊሆን ይገባል፤ ብዙውን ጊዜ ፈጣን ውጤት ማየትን የሚፈልግ እና መጠበቅን ችላ በሚሉ ዓለማዊ መመዘኛዎች ሳንደናቀፍ በጥልቀት እንቆፍር” ብለዋል።
ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ጋር በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ የተሳተፉት የሮም ሀገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ እና የቅዱስ ዮሐንስ ዘላተራን ባሲሊካ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ባልዳሳሬ ሬይና እና የካምፒሊ ጳጳስ እና የሮም ሀገረ ስብከት ምክትል ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሬናቶ ታራንቴሊ ሲሆኑ፥ በሥነ-ሥር ዓቱ ላይ በግምት 160 ካህናት እና 10 ጳጳሳት መገኘታቸው ታውቋል።
ቤተ ክርስቲያንን ለመገንባት በቅድሚያ ወደ ክርስቶስ መመልከት አለብን
በቅዱስ ዮሐንስ ዘላተራን ባሲሊካ መሠረቶችን በማስታወስ አስተንትኖአቸውን የጀመሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “የመሠረቶቹ አስፈላጊነት ግልጽ እና በተወሰነ ደረጃ የሚያስጨንቅ ነው” ሲሉ ተናግረው፥ የሮምን ካቴድራሉን የገነቡት ሰዎች በከፍተኛ ጥረት በጥልቀት በመቆፈር ሌላ ማንኛውንም ነገር ለመገንባት የሚያስችል በቂ እና ጠንካራ መሠረት እንደጣሉ ገልጸዋል። በዚህ መንገድ መዋቅሩ በጊዜ ሂደት እንዳይፈርስ ለመከላከል ይህ ጠቃሚ ምስል እንደሆነ አስረድተዋል።
“በሕያው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ ሠራተኞች አስደናቂ መዋቅሮችን ከመገንባታችን በፊት በቅድሚያ እኛ በራሳችን እና በዙሪያችን ያለውን በጥልቀት መመልከት አለብን” ብለዋል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች ከጻፈው የመጀመሪያ መልዕክት የተወሰደውን የዕለቱን ሁለተኛ ንባብ የጠቀሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በዚህ ጥቅስ ውስጥ ማንም ሰው ከተጣለው መሠረት ሌላ መሠረት መጣል አይችልም፤ ያ መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” ብለዋል።
“ይህ ማለት ዘወትር ወደ ኢየሱስ እና ወደ ወንጌሉ መመለስ፣ ለመንፈስ ቅዱስ ተግባር ገር መሆን ማለት ነው። አለበለዚያ መሠረቶቻቸው ደካማ በሆኑ ሕንፃዎች ላይ ከመጠን በላይ የሆነ ክብደት ለአደጋ ያጋልጠናል” ብለዋል።
ቤተ ክርስቲያንን እንደ ግንባታ ቦታ ማየት
በመስዋዕተ ቅዳሴ ወቅት ቅዱስ ሉቃስ ወደጻፈው የወንጌል ክፍል የተመለሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በዚህ ጥቅስ ውስጥ ከኢየሱስ ጋር ለመገናኘት የፈለገው ባለጠጋ እና ኃያል ሰው ዘኬዎስ በሕዝቡ መካከል እሱን ለማየት ዛፍ ላይ መውጣቱ የሚፈልገውን በሙሉ ማግኘት ለሚችል ሰው ያልተለመደ እና ተገቢ ያልሆነ ምልክት እንደሆነ ገልጸው፥ ዘኬዎስ በቅርንጫፎቹ ላይ መውጣቱ የራሱን ውስንነቶች እና ትዕቢቶች ያሸነፈበ ነው” ሲሉ ጠቁመው፥ “ይህም ለእርሱ የአዲስ ሕይወት መጀመሪያ ገጠመኝ ነው” ብለዋል።
ኢየሱስ ክርስቶን በእግዚአብሔር ታላቅ ሥራ ውስጥ እንድንሳተፍ ሲጠራን፣ በመዳን ዕቅዶቹ በብቃት በመቅረጽ ይለውጠናል ያሉት ቅዱስነታቸው፥ በቅርብ ዓመታት ውስጥ፣ የቤተ ክርስቲያናችንን ጉዞ ለመግለጽ “የግንባታ ቦታ” ምስል ብዙ ጊዜ ጥቅም ላይ መዋሉን ተናግረው፥ ስለ ሥራ፣ ስለ ፈጠራ እና ቁርጠኝነት እንዲሁም ስለ ጠንክሮ መሥራት እና አንዳንድ ጊዜ ሊፈቱ ስለሚገቡ ውስብስብ ችግሮች የሚናገር ውብ ምስል ነው” ብለዋል።
በሮም ውስጥ ታላቅ መልካም ነገር እያደገ ነው
“የግንባታ ቦታ ምስሉ ማኅበረሰቦቻችን በየቀኑ የሚያድጉበት እውነተኛ እና ግልጽ ጥረት መኖሩን ያሳያል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራተኛ፥ በሐዋርያዊ አባቶች መሪነት ቸርነትን እንደሚካፈሉ ገልጸው፥ በቅዱስ ዮሐንስ ዘላቴራን ባዚሊካ ታሪክ ውስጥ ወሳኝ ጊዜያት፣ ቆም ያሉበት እና በሂደት ላይ ያሉ ሥራዎች እርማት እንደተደረገበት በማስታወስ፥ “ከእኛ በፊት ለነበሩት ሰዎች ጽናት ምስጋና ይግባቸውና በዚህ አስደናቂ ቦታ መሰብሰብ እንችላለን” ብለዋል።
“ሮም ውስጥ በብዙዎች ጥረት ታላቅ መልካም ነገር እየተደረገ ይገኛል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ድካም ይህን መልካም ነገር እንዳናውቅ እና እንዳናከብር ሊያደርገን አይገባም” ብለው፥ ጉጉታችንን መንከባከብ እና ማደስ እንደሚገባ፥ ከሁሉም በላይ የቤተ ክርስቲያናችን መልክ የሚታደሰው በተግባር በሚደረግ ልግስና እንደ ሆነ፣ ይህም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በባዚሊካው በዓል ቀን ከልጆች ጋር ባደረጉት ውይይት፥ “እናት ቤተ ክርስቲያን የቤተ ክርስቲያናት ሁሉ እናት ናት” ሲሉ ለሁሉም ግልጽ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
የሮም ቤተ ክርስቲያን በአሁኑ ጊዜ “የሲኖዶሳዊነት የተግባር ምዕራፍ” እንዴት እየተመለከተችው እንደሆነ በማሰላሰል እንደተናገሩት፥ ሲኖዶሳዊነትን በማስመልከት ለዓመታት በተሠራ ሥራ እየጎለበተ የመጣው ልምድ መፈተን እና መገምገም እንዳለበት አሳስበው፥ ከባድ ጉዞን የሚያመለክት ቢሆንም ተስፋ መቁረጥ እንደማይገባ፥ “በምትኩ አብረን ለማደግ የምናደርገውን ጥረት በልበ ሙሉነት መቀጠል አለበት” ብለዋል።
የሥርዓተ አምልኮ አስፈላጊነት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በመጨረሻም፥ “የካቴድራል ተልዕኮ አስፈላጊ ገጽታ ማለትም የአምልኮ ሥርዓቱ የቤተ ክርስቲያኗ እንቅስቃሴ የሚመራበት እና ኃይሏ ሁሉ የሚፈስበት ምንጭ መሆኑን ገልጸው፥ በቃለ-ምዕዳናቸው ውስጥ የጠቀሷቸው ጭብጦች በሙሉ በዚህ ውስጥ እንደሚገኙ አስረድተዋል። “እንደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በመንፈስ ውስጥ እንደ መኖሪያ ሥፍራው ሆነን የተገነባን በመሆናችን ኢየሱስ ክርስቶስን በዓለም ውስጥ ለመስበክ ኃይልን እናገኛለን” ብለዋል።
ስለዚህ በተለይም በቅዱስ ጴጥሮስ መንበር ለአምልኮ ሥነ-ሥርዓት ትኩረትን መስጠት ለመላው የእግዚአብሔር ሕዝብ ምሳሌ ሆኖ ሊያገለግል የሚችል መሆን አለበት ብለዋል። ከተቀመጡት ደንቦች ጋር የሚጣጣም፣ ለተሳታፊ ሰዎች የተለያዩ ስሜቶች ትኩረት የሚሰጥ እና በጥበብ ባህል መርህ የሚመራ መሆን አለበት ብለዋል። (መመሪያ ቁ፣ 37-38)። እንደዚሁም ለሮማውያን የተለመደ ባሕል ታማኝ ሆኖ በመቆየት፥ በንቃት ለሚሳተፉት ነፍሳት ብዙ ጥቅም ሊያስገኝ እንደሚችል አስረድተዋል።
ቅዱስ አጎስጢኖስ “ውበት ፍቅር፣ ፍቅርም ሕይወት ነው” ያለውን የጠቀሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኝ፥ “በሥርዓተ አምልኮ ውስጥ ይህ እውነት በታላቅ መንገድ አፅንዖት ተሰጥቶታል” ብለው፥ “በውበት የሚገለጹ የአምልኮ ሥርዓቶች ከኢየሱስ ክርስቶስ አካል ጋር በሚስማማ የአምልኮ ዋጋ እንዲገልጽ ሁሉም ጥንቃቄ መደረግ አለበት” ሲሉ ተስፋቸውን ገልጸው፥ “ወደ መበረ-ታቦት የሚቀርቡት ምዕመናን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ሊያጥለቀልቅ በሚፈልገው ጸጋ ተሞልተው ይሄዳሉ” ሲሉ አስረድተዋል።
