ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በቅዱስ ቻርቤል ማክሎፍ መቃብር ስፍራ ተገኝተው ጸሎት ሲያደርጉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በቅዱስ ቻርቤል ማክሎፍ መቃብር ስፍራ ተገኝተው ጸሎት ሲያደርጉ   (@Vatican Media)

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በቅዱስ ቻርቤል ማክሎፍ መቃብር ስፍራ ተገኝተው ጸሎት ማድረጋቸው ተነገረ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በሊባኖስ እያደረጉት ባለው ሐዋርያዊ ጉብኝት ሁለተኛው ቀን ላይ የቅዱስ ቻርቤልን መቃብር የጎበኙ ሲሆን፥ በዚህም ወቅት ቅዱስ ቻርቤል “ከእግዚአብሔር ውጭ ለሚኖሩ ሰዎች ጸሎትን፣ በጩኸት ውስጥ ለሚኖሩት ዝምታን... ሀብትን ለሚያሳድዱ ሰዎች ድኅነትን” ለማስተማር ያደረጉትን ትጋት በማንሳት ተናግረዋል።

አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ መንፈሳዊ ነጋዲያን፣ ክርስቲያኖች እና እስላሞች በቅዱስ ቻርቤል ማክሎፍ መቃብር ለመጸለይ ወደ ሊባኖስ አናያ ከተማ የሚጓዙ ሲሆን፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ህዳር 22 ቀን 2018 ዓ.ም. ወደ መቃብር ሥፍራው በመጓዝ ከእነዚህ ጎብኝዎች መካከል አንዱ ሆነዋል።

መቃብሩ በሚገኝበት የቅዱስ ማሮን ገዳም ዋና መግቢያ በር ላይ የገዳሙ የበላይ አለቃ እና የሊባኖስ ማሮናዊት ገዳም የበላይ አለቃ እንዲሁም የሊባኖስ ፕሬዝደንት እና ቀዳማዊት እመቤት ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

የማህበሩ በላይ አለቃ የሆኑት አቦት ማሕፉዝ ሃዲ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ከማድረጋቸ ቀደም ብሎ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በጸጥታ ውስጥ ሆነው በቅዱስ ቻርቤል መቃብር ፊት የጸለዩ ሲሆን፥ ብፁዕነታቸው ጸሎት ካቀረቡ በኋላ በፈረንሣይኛ ቋንቋ ባቀረቡት ንግግር “ተደብቀው በዝምታ የኖሩት፥ ነገር ግን ዝናቸው በመላው ዓለም የተስፋፋው” ስለ ቅዱስ ቻርቤል በማንሳት ገለፃ አድርገዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ባደረጉት ንግግር ባህታዊው ቅዱስ ቻርቤል ከእግዚአብሔር ውጭ ለሚኖሩ ጸሎትን፣ በጩኸት ውስጥ ለሚኖሩ ዝምታን፣ ለታይታ ለሚኖሩ ትሕትናን፣ ሀብትን ለሚያሳድዱ ድህነትን ለማስተማር “በመንፈስ ቅዱስ ተቀርፆ ነበር” ብለዋል።

የሰላም ጥሪ
ከ 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በሃገሪቷ የተከሰቱትን የምንዛሪ ውድቀት፣ የተስፋፋ ድህነት፣ የህዝብ አገልግሎት ውድቀት፣ በ 2020 ዓ.ም. በቤሩት ወደብ የደረሰ ከባድ ፍንዳታ እና ሃገሪቷ ከእስራኤል ጋር የገባችበት ግጭትን ጨምሮ በከባድ ቀውስ ውስጥ ለምትገኘው ሊባኖስ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጉብኝት የተስፋ እና የሰላም መልዕክት ማምጣቱ ይገለፃል።

በተለይ ለሊባኖስ እና ለምሥራቁ የሜድተራኒያን ሃገራት (ሌቫንታይኖች) “ሰላም እንዲሰፍን እንጠይቃለን” ያሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ፥ “ቅዱሳኑ እንደሚያስታውሱን መጀመሪያ ልብ ካልተለወጠ ሰላም እንደማይኖር እኛም እናውቃለን” ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የቤተክርስቲያንን፣ የሊባኖስን እና የዓለምን ፍላጎቶች ለቅዱስ ቻርቤል አማላጅነት አደራ ሰጥተዋል።

ጉብኝቱ የሊባኖስ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ አዎን እና ባለቤታቸው በተገኙበት ለቅዱስ ቻርቤል በተደረገው የጸሎት ሥነ ስርዓት እና በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ቡራኬ ተጠናቋል።

ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የተሰጠ ስጦታ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በመጨረሻም ለገዳሙ ከብር እና ነሃስ በእጅ የተሰራ የፋኖስ መብራት ስጦታ ያቀረቡ ሲሆን፥ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር “ይህን ፋኖስ በስጦታ ሳበረክት፥ ሊባኖስ እና ህዝቦቿ ሁል ጊዜ በክርስቶስ ብርሃን ይመላለሱ ዘንድ ለቅዱስ ቻርቤል ጥበቃ አደራ እላለሁ። ስለ ቅዱስ ቻርቤል ስጦታ እግዚአብሔርን እናመስግን! መታሰቢያውንም ስለጠበቅክ እናመሰግናለን፣ በጌታ ብርሃን ተመላለሱ!” በማለት በቡራኬ አጠናቀዋል።

02 Dec 2025, 14:10