በሮም የሚገኝ የጽንሰተ ማርያም ሐውልት በሮም የሚገኝ የጽንሰተ ማርያም ሐውልት 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በሮም የሚገኘውን የጽንሰተ ማርያም ሐውልት እንደሚጎበኙ ተነገረ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የላቲን ሥርዓት የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ ምዕመናን ዘንድ በየዓመቱ የሚከበረውን የጽንሰተ ማርያም ዓመታዊ በዓል በሮም እንደሚያከብሩ ታውቋል። ቅዱስነታቸው ከእርሳቸው ቀደም ብሎ በነበሩት ርዕሣነ ሊቃነ ጳጳሳት ሲደረግ እንደ ነበር ሁሉ፥ ዓመታዊ በዓሉ በሚከበርበት ኅዳር 29/2018 ዓ. ም. “የስፔን ደረጃዎች” ተብሎ በሚጠራ አካባቢ የሚገኘውን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሐውልት እንደሚጎብኙት ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በየዓመቱ ኅዳር 29 የጽንሰተ ማርያም ዓመታዊ በዓልን የማክበር ባሕል ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሚቀርብ ውዳሴ እና ክብር ጋር የተገናኘ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፥ በዓሉ ዕለት የሮም ከተማ ልዩ ልዩ ሃይማኖታው እና የሲቪክ ድርጅቶች ተወካዮች በከተማዋ መሃል በሚገኘው ታዋቂው የጽንሰተ ማርያም ሐውልት ፊት ቀርበው እንደሚጸልዩ እና የአበባ ጉንጉን እንደቀርቡ ይታወቃል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ዘንድሮው በሚከበረው በዓል ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛን እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛን ጨምሮ ከእርሳቸው በፊት የነበሩ ርዕሣነ ሊቃነ ጳጳሳት ፈለግ በመከተል በተለመደው የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደሚሳተፉ ታውቋል።

ባለፈው ዓመት በተከበረው በዓል ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ እመቤታችን ማርያም ምስል ፊት ቀርበው በቀውስ እና በጦርነት ለተፈተነው ዓለም የተስፋ መልዕክት ለሚሆን የኢዮቤልዩ ዓመት የአደራ ጸሎት ማቅረባቸው የሚታወስ ሲሆን፥ የኢዮቤልዩ ቅዱስ ዓመት ሊፈጸም ጥቂት ሳምንታት በቀሩበት በዚህ ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሐውልት ሥር ቀርበው ጸሎት እንደሚያቀርቡ ታውቋል።


የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ጉብኝት

ረቡዕ ኅዳር 24/2018 ዓ. ም. በወጣው የቅድስት መንበር መግለጫ መሠረት፥ የሮም የእሳት አደጋ መከላከያ ቡድን ሰኞ ኅዳር 29/2018 ዓ. ም. ማለዳ በእመቤታችን ማርያም ሐውልት ላይ የአበባ ጉንጉን ካስቀመጡ በኋላ የሮም ሀገረ ስብከት ጳጳስ የሆኑት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ከሰዓት በኋላ በአሥር ሰዓት ወደ ጽንሰተ ማርያም ሐውልት ሲደርሱ በሮም ሀገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ባልዶ ሬይና እና በሮም ከንቲባ ሮቤርቶ ጓልቲየሪ አቀባበል እንደሚደረግላቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው 12 ሜትር ከፍታ ባለው አምድ ላይ በተቀመጠው የጽንሰተ ማርያም ሐውልት ፊት ጸሎታቸውን ካቀረቡ በኋላ የአበባ ጉንጉን እንደሚያስቀምጡ ታውቋል።

ለበዓሉ ዕለት በተዘጋጀው መርሃ ግብር መሠረት የቫቲካን ክብር ዘብ የሙዚቃ ባንድ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ተኩል ላይ የእመቤታችን ማርያም መዝሙር ከዘመረ በኋላ የቅዱስ አንድሪያ ዴሌ ቁምስና፣ የማልታ ሉዓላዊ ማኅበር፣ የሌጂዮ ማርያ፣ የቺርኮሎ ሳን ፒዬትሮ፣ የዶን ኞኪ ፋውንዴሽን፣ ዩኒታሊሲ እና የተለያዩ የትምህርት ተቋማት መዝሙራቸውን እንደሚያቀርቡ ታውቋል።

ከበዓሉ አስቀድሞ ለማርያም የሚቀርብ የዘጠኝ ቀናት ጸሎት

የአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ባዚሊካ አስተዳዳሪ የሆነው የፍራንሲስካውያን ማኅበር በጽንሰተ ማርያም በዓል ዕለት የተለያዩ ዝግጅቶችን የሚያቀርብ ሲሆን በተጨማሪም ከኅዳር 20-28/2018 ዓ. ም. ድረስ ከሰዓት በኋላ ከ 11:45 ጀምሮ የመቁጠሪያ ጸሎትን ጨምሮ ለእመቤታች ቅድስት ድንግል ማርያም የሚቀርቡ የዘጠኝ ቀናት የጸሎት ሥነ-ሥርዓቶችን የሚያስተናግ ሲሆን፥ ከዚያም ከሰዓት በኋላ በ12:30 ላይ የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት እንደሚጀምር ታውቋል።

ለእመቤታች ማርያም በተመደቡ ዘጠኝ የጸሎት ቀናት ውስጥ የሚቀርቡ የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓቶችን ልዩ ልዩ ብጹዓን ካርዲናሎች እንደሚመሩ መሆናቸውን መርሃ ግብሩ ያመለክታል።

 

04 Dec 2025, 13:54