ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ እጅግ ታዋቂውን የኢስታንቡል ሰማያዊ መስጊድን ጎበኙ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በቱርክ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ሦስተኛው ቀን “ሰማያዊ መስጊድ” የሚባለውን የሱልጣን አህመድ መስጊድን ጎብኝተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በውጭ አገር የመጀመሪያ ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረግ የጀመሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በቱርክ ጉብኝታቸው “ሰማያዊ መስጊድ” በመባልም የሚታወቀውን የሱልጣን አህመድ መስጊድ ጎብኝተዋል።

ቅዱስነታቸው ለቦታው እና ለጸሎት ለሚሰበሰቡት ሰዎች ጥልቅ አክብሮት በመስጠት የሱልጣን አህመድ መስጊድን በጽሞና፣ በማስተዋል እና በትኩረት በማዳመጥ መንፈስ የጎበኙት መሆኑን የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል አስታውቋል።

መስጊዱ በጥንታዊ ስሟ ኒቂያ ባሁኑ ኢዝኒክ ተብላ ከምትጠራ ሥፍራ በመጡ በአብዛኛው ሰማያዊ ቀለም ባላቸው ከ21,000 በላይ የሴራሚክ ንጣፎች የተሠራ በመሆኑ “ሰማያዊ መስጊድ” የሚል ስያሜ ማግኘቱ ታውቋል።

በኢስታንቡል ውስጥ ካሉት ተጠቃሽ መስጊዶች መካከል አንዱ የሆነው እና ታላቁ የቁስጥንጥንያ ቤተ መንግሥት በሚገኝበት ሥፍራ የታነጸው መስጊዱ በሱልጣን አህመድ ቀዳማዊ ዘመን ማለትም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1617 ዓ. ም. መጠናቀቁ ይታወሳል። 

ዋና ግቡ መስጊዱ በኦቶማን ዘመነ መንግሥት እጅግ ታዋቂ የአምልኮ ቦታ እንዲሆን ለማድረግ እንደ ነበር ሲነገር፥ አሁን በቶፕካፒ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ተጠብቀው የሚገኙ ስምንት ጥራዞች የመስጊዱን ግንባታ ታሪክ የሚገንጹ መሆናቸው ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ቅዳሜ ኅዳር 20/2018 ዓ. ም. ጠዋት ወደ መስጊዱ ሲደርሱ፥ የአገሪቱ የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር መሕመት ኑሪ ኤርሶይ፣ የኢስታንቡል ክልል ሙፍቲ ኤምሩላህ ቱንሴል እና የሱልጣን አህመድ መስጊድ ኢማም ኩራ ሃፊዝ ፋቲህ ካያ አቀባበል አድርገውላቸዋል። ሙአዚን ሙዛ አሽጊን ቱንካ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በመስጊዱ ያደረጉትን አጭር ጉብኝት መርተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በዕለቱ የተለያዩ ስብሰባዎችን እና ጉብኝቶችን እንደሚያደርጉ የታቀደ ሲሆን፥ ከ “ሰማያዊ መስጊድ” ጉብኝት በኋላ በሶርያ የሞር ኤፍሬም ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ከአካባቢው አብያተ ክርስቲያናት እና የክርስቲያን ማኅበረሰቦች መሪዎች ጋር ስብሰባ አድርገዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ሰማያዊ መስጊድን” የጎበኙ ሦስተኛው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሲሆኑ፥ ይህን መስጊድ በቅርብ ጊዜ ማለትም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2014 ዓ. ም. የጎበኙት ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ፍራንችስኮስ እንደ ነበሩ ይታወሳል። ከእርሳቸው ቀደም ብሎ ማለትም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2006 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ ጎብኝተውት እንደ ነበር ይታወሳል።

በታሪክ ውስጥ አንድ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መስጊድን ሲጎበኙ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ ሁለተኛው ሲሆን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2001 ዓ. ም. በሶርያ ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት በደማሰቆ በሚገኝ የኡማያድ መስጊድ ለመጀመሪያ ጊዜ ታሪካዊ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ቀጥለውም በቅዱስ ጊዮርጊስ ፓትሪያርካዊ ባዚሊካ ውስጥ ከቁንስጥንጥንያው ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ቤርተሎሜዎስ ቀዳማዊ ጋር በምስጋና ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ ተሳትፈዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የኢስታንቡል ሰማያዊ መስጊድ ሲጎበኙ

 

01 Dec 2025, 14:30