ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ “መጭው ጊዜ የተረጋጋ የሚሆነው በሰላማዊ ሰዎች ጥረት ነው” ሲሉ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአራት የአፍሪካ አገራት የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ሰኞ ሚያዝያ 6/2018 ዓ. ም. መጀመራቸው ይታወሳል። ጉብኝታቸውን በጀመሩባት አልጄሪያ ባደረጉት የመጀመሪያ ንግግር፥ እግዚአብሔር ለሁሉም አገራት ሰላምን የሚፈልግ መሆኑን ገልጸው፥ ሰላም የሚገለጸው በፍትህ እና በሰብዓዊ ክብር እንደሆነ በማሳሰብ፥ የአልጄሪያ ሕዝብ በታሪካዊ ቅርሶቻቸው መካከል ለእግዚአብሔር ቀዳሚ ቦታን እንዲሰጡ አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው አልጄሪያ ሲደርሱ በተገኙበት የመጀመሪያ ሕዝባዊ ዝግጅት፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ 1954-1962 ዓ. ም. በአልጄሪያ የነፃነት ትግል ውስጥ ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎችን የሚያስታውስ የሰማዕታት ሐውልት “ማቃም ኢቻሂድ” ጎብኝተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአልጄሪያ የሰማዕታት ሐውልት የጎበኙበት ሥነ-ሥርዓት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአልጄሪያ የሰማዕታት ሐውልት የጎበኙበት ሥነ-ሥርዓት   (@Vatican Media)

በመታሰቢያው ሐውልቱ ሥር የአበባ ጉንጉን ካስቀመጡ በኋላ ባሰሙት የመጀመሪያ ንግግር፥ የቅዱስ አጎስጢኖስ ማኅበር አባል ከሆኑ በኋላ አልጄሪያን ሁለት ጊዜ መጎብኘታቸውን አስታውሰው፥ እንደገና ለመጎብኘት ዕድል በማግኘታቸው እግዚአብሔርን በማመስገን፥ “ከሁሉ በፊት በዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝቴ አማካኝነት ልባችንን የሚያቀራርበውን የፍቅር አንድነት በማደስ ደስተኛ ወንድማችሁ ሆኜ ከጎናችሁ ቆሜአለሁ” ብለዋል።

በመታሰቢያ ሐውልቱ ፊት ለፊት ባለው አደባባይ የተሰበሰቡን ወደ 2,000 የሚደርሱ ሰዎችን በመመልከት፥ ጠንካራ እና ወጣት ሰዎችን እንደሚያዩ እና በአልጄሪያ ሕዝብ ልብ ውስጥ ወዳጅነት፣ መተማመን እና አንድነት መኖሩን ገልጸው፥ እነዚህ አስፈላጊ እሴቶች ለሕይወት ጥንካሬን የሚሰጡ  ናቸው” ሲሉ አስረድተዋል።

እውነተኛ ነፃነት ከይቅርታ ጋር ይመጣል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአደባባዩ ለተሰበሰበው ሕዝብ ንግግር ሲያደርጉ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአደባባዩ ለተሰበሰበው ሕዝብ ንግግር ሲያደርጉ   (@Vatican Media)

የሀገሪቱን ረጅም ታሪክ መለስ ብለው የተለለከቱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ አልጄሪያ በባሕሎች የበለፀገች ብትሆንም ነገር ግን በዓመፅ ጊዜያት ያጋጠማት ሕመሞች ጭምር እንዳላት ገልጸው፥ “የሕዝቡን ጽናት በትክክል በሚገልጸው የመንፈስ ጥንካሬ አማካይነት ፈተናዎችን በሙሉ በድፍረት እና በታማኝነት ማሸነፍ ተችሏል” ብለዋል።

ቅዱስነታቸው የመታሰቢያ ሐውልቱ ለመጎብኘት መወሰናቸው የአልጄሪያን ታሪክ እና ሕዝቡ ለነፃነቱ፣ ለክብሩ እና ለሉዓላዊነቱ ያደረጉትን የተጋድሎ መንፈስ ለማስታወስ የሚያስችል ጊዜ እንደ ነበር ታውቋል። ቅዱስነታቸው ይህን በማሰብ እና እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ አገር ሰላምን እንደሚፈልግ በመናገር፥ ግጭት የሌለበት ብቻ ሳይሆን የፍትህ እና የክብር መግለጫ የሆነውን ሰላም እንዲያስታውሱ አሳስበዋል።

ቅዱስነታቸው ንግግር ሲያደርጉ
ቅዱስነታቸው ንግግር ሲያደርጉ   (@Vatican Media)

“ይህ ዓይነቱ ሰላም ሊመጣ የሚችለው በይቅርታ ብቻ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ይቅርታ ሁሉም ሰው በእርቅ መንፈስ እንዲተባበር የሚያስችል፥ “ለነፃነት የሚደረገው እውነተኛ ትግል በእርግጠኝነት የሚሳካው በልባችን ውስጥ ባለው ሰላም ብቻ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ቅዱስነታቸው “ይቅር ማለት ምን ያህል አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል አምናለሁ” ብለው፥ “ሆኖም በዓለም ዙሪያ በየጊዜው እየጨመረ በሚሄደው ግጭት ውስጥ ሌላ ግጭት እና ቂም መጨመር የለብንም” ብለዋል።

 

14 Apr 2026, 11:04