ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የአፍሪካ ሐዋርያዊ ጉብኝት ሲጀመሩ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የአፍሪካ ሐዋርያዊ ጉብኝት ሲጀመሩ   (@VATICAN MEDIA)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ወደ አልጄሪያ በማምራት ረጅሙን የአፍሪካ ሐዋርያዊ ጉብኝት ጀመሩ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሦስተኛውን እና ረጅሙን ሐዋርያዊ ጉዞቸውን ከሮም ፊውሚቺኖ የአየር ማረፊያ በመነሳት ጀምረዋል። ቅዱስነታቸው በዚህ ጉዞአቸው አራት የአፍሪካ አገራትን ማለትም አልጄሪያን፣ ካሜሩንን፣ አንጎላን እና ኢኳቶሪያል ጊኒን እንደሚጎበኟቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከሮም ፊውሚቺኖ አየር ማረፊያ በአገሩ አቆጣጠር ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ከስድስት ደቂቃ ላይ ጉዞ የጀመሩት ቅዱስነታቸው፥ የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መጀመሪያ አገር ወደ ሆነች አልጀሪያ አምርተዋል።

በአፍሪካ አኅጉር ውስጥ 10 ቀናትን የሚወስድ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን የጀመሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ አልጄሪያ ውስጥ ሁለት ቀናት የሚቆዩ ሲሆን፥ አገሪቱን የጎበኙት የመጀመሪያው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነዋል። ቅዱስነታቸው በአልጄሪያ ቆይታቸው ሰላም፣ ስደት፣ የአካባቢ እንክብካቤ፣ ወጣቶች እና ቤተሰብ የሚሉት ጭብጦችን በመዳሰስ መልዕክቶችን እንደሚያስተላልፉ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአልጄሪያ ጉብኝታቸው ወቅት ከአካባቢው ባለስልጣናት እና ከቅዱስ አጎስጢኖስ ገዳም አባላት ጋር በመገናኘት እንዲሁም የአልጄሪያን ጦርነት (1954-1962 እ.አ.አ) መታሰቢያ ሐውልትን እንደሚጎበኙ ታውቋል።

ቅዱስነታቸው በታናናሽ የድሆች እህቶች የሚተዳደረውን የአረጋውያን መኖሪያ ቤትን ለመጎብኘት ቀጠሮ የተያዘላቸው ሲሆን፥ እንዲሁም በአናባ በሚገኘው የቅዱስ አጎስጢኖስ ባዚሊካ ውስጥ የሚቀርበውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት እንደሚመሩ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአልጄሪያ የሚያደርጉት ይህ ሐዋርያዊ ጉብኝት የግል ትርጉም ያለው ሲሆን፥ ቀደም ሲል ሂፖ በመባል የምትታወቅ አናባ ቅዱስ አጎስጢኖስ እንደ ጎርግሮሳውያኑ ከ395 እስከ 430 ዓ. ም. ድረስ ጳጳስ ሆነው ያገለገሉባት ከተማ በመሆኗ ተብሏል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ አፍሪካን ሲጎበኟት ይህ የመጀመሪያቸው እንዳልሆነ ሲታወቅ፥ የቅዱስ አጎስጢኖስ ማኅበር ጠቅላይ አለቃ ሆነው ባገለገሉባቸው ዓመታት ውስጥ አልጄሪያን፣ ኬንያን እና ታንዛኒያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ አገሮችን የጎበኙ ሲሆን፥ አልጄሪያን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2001 እና በ2013 ዓ. ም. ጎብኝተው እንደ ነበር ይታወሳል።

 

13 Apr 2026, 11:30