ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአናባ የአረጋውያን መንከባከቢያ ማዕከልን ሲጎበኙ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአናባ የአረጋውያን መንከባከቢያ ማዕከልን ሲጎበኙ  (@Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ “የእግዚአብሔር ልብ በጦርነት፣ በዓመፅ እና በፍትሕ መጓደል ክፉኛ ቆስሏል” ሲሉ ተናገሩ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአልጄሪያ በሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው የአናባ የአረጋውያን መንከባከቢያ ማዕከልን ጎብኝተዋል። በማዕከሉ ውስጥ በተዘጋጀው ሥነ-ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፥ “የእግዚአብሔር ልብ ትሑት እና በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ሰላምን ከሚፈልጉ ሰዎችን ጋር ነው” ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአልጄሪያ ሐዋርያዊ ጉብኝት ሁለተኛ ቀን ቅዱስ አጎስጢኖስ ጳጳስ ሆኖ ያገለገለባትን ጥንታዊቷ አናባን ከጎበኟት በኋላ በድሆች ትናንሽ እህቶች ማኅበር የሚመራው የ “ማ ማይሰን” የአረጋውያን ማዕከል ውስጥ እንክብካቤ ከሚደረግላቸው በርካታ አረጋውያን ጋር አጭር ቆይታ አድርገዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለማዕከሉ ነዋሪዎች ባደረጉት አጭር ንግግር፥ “እግዚአብሔር እዚህ ይኖራል” ሲሉ ተናግረው፥ “ፍቅር እና አገልግሎት ባለበት ቦታ ሁሉ እግዚአብሔር ይኖራል” ሲሉ አስረድተዋል።

በአናባ የሚገኝ የአረጋውያን መንከባከቢያ ማዕከል
በአናባ የሚገኝ የአረጋውያን መንከባከቢያ ማዕከል   (@Vatican Media)

የማዕከሉ ተጠሪ ሳላህ ቡኬሜልን ለሰላምታ ንግግራቸው አመስግነው በማዕከሉ ውስጥ የሚኖሩ የአልጄሪያ ሙስሊም አረጋውያን ለእርስ በእርስ እና ለሃይማኖታቸው ያላቸው አክብሮት እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።

ቅዱስነታቸው በምላሹም፥ ሰዎች በወንድማማችነት አብረው ለመኖር በሚጥሩበት ቦታ ያለውን ተስፋ እግዚአብሔር በእርግጠኝነት እንደሚያውቅ ተናግረዋል።

“የእግዚአብሔር ልብ በጦርነት፣ በዓመፅ፣ በኢ-ፍትሃዊነት እና በውሸት እጅግ ቆስሏል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ በሰማያት ያለው አባታችን ልብ ከጨካኞች እና ከትዕቢተኞች ጋር አይደለም” ብለው፥ ይልቁንስ መንግሥቱን በአገልግሎት ከሚገነቡት ጋር እግዚአብሔር አለ” ሲሉ ተናግረዋል።

“እናንተም በዕለት ተዕለት አገልግሎታችሁ፣ በጓደኝነታችሁ እና በሕይወታችሁ አብራችሁ ለመኖር እንደምትጥሩ ሁሉ የእግዚአብሔር ልብ ዘወትር ከሕጻናት እና ከትሑታን ጋር በመሆን የፍቅር እና የሰላም መንግሥቱን ዕለት ዕለት ይገነባል” ብለዋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ2008 እስከ 2021 ዓ. ም. ድረስ የቆስጠንጢኖስ-ሂፖን ጳጳስ ሆነው ያገለገሉት እና አሁን ከድሆች ትናንሽ እህቶች ጋር የሚኖሩት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ዴስፋርጅስ ለቅዱስነታቸው ሰላምታ አቅርበውላቸዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ አቀባበል ሲያደርጉ
ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ አቀባበል ሲያደርጉ   (@Vatican Media)

ሊቀ ጳጳሱ በሰላምታ ንግግራቸው፥ ገዳማውያቱ እና የማዕከሉ ሠራተኞች በእንክብካቤያቸው እና በሃሳባቸው በየቀኑ ተአምራትን እንደሚያደርጉ ገልጸው፥ ከቀላል የእጅ መጨባበጥ ጀምሮ ሰዎችን አንድ ላይ የሚያቀራርቡ ተግባራትን እያከናወኑ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በበኩላቸው፥ ከሊቀ ጳጳስ ዴስፋርጅስ ለተደረገላቸው አቀባበል እና ከአረጋውያኑ ጎን በመሆን ለሚሰጡት ምስክርነት አመስግነው፥ በሉቃ. 10:21 ላይ የተጻፈውን በመጥቀስ፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “የሰማይ እና የምድር ጌታ አባት ሆይ! ይህን ከጥበበኞች እና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግናለሁ” ማለቱን አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በንግግራቸው ማጠቃለያ፥ ከሞተ የተነሳው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምስል በስጦታነት ያቀረቡ ገዳማውያትን እና የማዕከሉ ነዋሪዎችን ለምስክርነታቸው አመስግነዋቸዋል።

በአልባኒያዊው ሠዓሊ ዮሴፍ ድሮቦኒኩ የተሳለው መንፈሳዊ ምስሉ ከጥንታዊው የባይዛንታይን ባሕል ጋር የተያያዘ ሲሆን በግሪክ ቋንቋ፥ “ሂዱና አሕዛብን ሁሉ ደቀ መዛሙርት አድርጉ” የሚል መልዕክት የተጻፈበት እንደሆነ ተመልክቷል።

ከጥበብ ሥራው ጋር ተያይዞ የተሰጠው ጽሑፍም፥ “የእኔ ማንነት፣ በጎነት እና አገልግሎት በሙሉ ከሞት በተነሳው በኢየሱስ ክርስቶስ እንዲበራ፥ የሰው ልብ መጽናናትን እና ተስፋን በሚጠብቅበት ቦታ ሁሉ ምሕረቱ እንዲወርድ” የሚል የግብዣ መልዕክት ያለበት መሆኑ ተመልክቷል።

 

15 Apr 2026, 10:52