ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ከእንግዲህ በኋላ ጦርነት ይብቃ” ሲሉ የዓለም መሪዎችን አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ወደ አልጄሪያ ባደረጉት አጭር በረራ፥ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በ “Truth Social Network” ላይ የጻፉትን አስተያየት በማስመልከት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። “ፕሬዝዳንት ትራምፕ የእኔን ሚና እንደ ፖለቲከኞች ሚና አድርገው አይመለከቱትም” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ፖለቲከኛ አይደለሁም፤ ክርክር ውስጥ መግባትም አልፈልግም” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል።
ከዚህም በላይ “አንዳንዶች እንደሚያደርጉት የወንጌልን መልዕክት አላግባብ መጠቀም ተገቢ ነው ብዬ አላስብም” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “በአገራት መካከል ሰላምን፣ ውይይትን፣ ብዝሃነትን እና ለችግሮች መፍትሄ ለማግኘት እየሞከርኩ ጦርነትን በጥብቅ መቃወሜን እቀጥላለሁ” ብለዋል። “ዛሬ በርካታ ሰዎች በስቃይ ውስጥ በመሆናቸው፥ የብዙ ንፁሃን ሰዎች ሕይወት እየጠፋ በመሆኑ፥ አንድ ሰው ተነስቶ የተሻለ መንገድ እንዳለ መናገር እንዳለበት አምናለሁ” ብለዋል።
ከዚህ በፊት ያቀረቡትን የሰላም ጥሪ በማደስ፥ “የሰላም ጥሪዬን የማስተላልፈው ለፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ብቻ ሳይሆን ሁሉም የዓለም መሪዎች ሰላምን እና እርቅን በማበረታታት ጦርነቶችን እናስቁም” ሲሉ አሳስበዋል።
ቅዱስነታቸው “ለትራምፕ አስተዳደር ሆነ የወንጌልን መልዕክት ጮክ ብዬ የመናገር ፍርሃት የለብኝም” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ በሐዋርያዊ አገልግሎት ላይ የምገኘው እና የቤተ ክርስቲያኒቱ ጥሪም የወንጌልን መልዕክት ማወጅ እንደሆነ አምናለሁ” ሲሉ አስረድተዋል።
“እኛ ፖለቲከኞች አይደለንም” ሲሉ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ “የውጭ ፖሊሲን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሊረዱት በሚችሉት ተመሳሳይ መንገድ ባንረዳም ነገር ግን እንደ ሰላም ፈጣሪ በቅዱስ ወንጌል መልዕክት አምናለሁ” ብለዋል።
ቀጣይነት ያለው የሰላም መልዕክት
በአራቱ የአፍሪካ አገራት ውስጥ በሚያደርጓቸው ሐዋርያዊ ጉብኝቶች ከሚነሱ መሪ ጭብጦች መካከል ሰላም አንዱ ነው። “ይህ ጉዞ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትነት ወቅት የማደርገው የመጀመሪያው ሐዋርያዊ ጉብኝት ከመሆኑ በተጨማሪ በተለያዩ ምክንያቶች የተለየ ነው” ሲሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ገልጸዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በሃይማኖቶች መካከል ለሚደረገው የጋራ ውይይት እጅግ ጠቃሚ ድልድይ የሆነውን የቅዱስ አጎስጢኖስ ምድርን እንደገና ለመጎብኘት በመቻላቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፥ “ቅዱስ አጎስጢኖስ ሰሜን አፍሪካዊ ጳጳስ ሆኖ ወዳገለገለበት ሥፍራ መጓዝ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ለቤተ ክርስቲያኒቱ እና ለዓለምም ጭምር እንዴት ያለ ውድ በረከት ነው” በማለት፥ ሰላምን እና እርቅን የምንገነባበት ድልድይ መፈለግ አለብን” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል።
የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ጠቅላላ ተልዕኮን በማስመልከት ማብራሪያ የሰጡት ቅዱስነታቸው፥ “ተመሳሳይ ድምፅ በማሰማት እና ተመሳሳይ መልዕክት በማስተላለፍ የምንፈልገውን ሰላም፣ እርቅ፣ ሰብዓዊ ክብር እና አሳቢነት በማሳየት ወደፊት መቀጠል እንደሚገባ ለጋዜጠኞች በማሳሰብ ንግግራቸውን በሰላምታ ደምድመዋል።
የአልጄሪያ ተጨባች ሁኔታ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ወደ አልጀርስ ሲደርሱ የአልጄሪያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት አብደልማጂድ ቴቡኔ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
በዝናባማ የአየር ሁኔታ ውስጥ ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ ቅዱስነታቸው በቀጥታ በአየር ማረፊያው ወደሚገኘው የእንግዳ መቀበያ ከታጀቡ በኋላ ከክብር ዘብ ሙዚቃ በፊት ባህላዊ ልብስ የለበሰች ወጣት አበባን ያበረከተችላቸው ሲሆን፥ ከአቀባበል ሥነ-ሥርዓት ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት አብደልማጂድ ቴቡኔ ጋር በግል አጭር ውይይት አድርገዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከፕሬዝደንቱ ካር ካደርጉት የግል ውይይታቸው በኋላ የመጀመሪያ ጉብኝታቸውን ለማድረግ ወደ ማቃም ኤቻሂድ የሰማዕታት መታሰቢያ ሥፍራ ተጉዘዋል።
