“የሰው ልጅ ታላቅነት” የተሰኘው ሐዋርያዊ መልዕክት ዘላቂ ተጽእኖ እንደሚፈጥር ተገለጸ

በዩናይትድ ኪንግደም የዱራም ዩኒቨርሲቲ የሥነ-መለኮት ሊቅ ፕሮፌሰር አና ሮውላንድስ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ “የሰው ልጅ ታላቅነት” የተሰኘ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጠንካራ ሐዋርያዊ መልዕክት፥ የዘመናችንን የሰው ሠራሽ አስተውሎት ጥቅሞች እና አደጋዎች በመዳሰስ በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በዓለም ውስጥ ዘላቂ ተጽእኖ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ፕሮፌሰር አና ሰኞ ግንቦት 17/2018 ዓ. ም. ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ “ስለ እዚህ ጉዳዮች ለማሰብ ቀጠሮ መያዝ አያስፈልግም” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተውታል።

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 13ኛ “አዳዲስ ነገሮች” (Rerum novarum) የሚል ሐዋርያዊ መልዕክት 135ኛ ዓመት መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ዓርብ ግንቦት 7/2018 ዓ. ም. የፈረሙበት ሐዋርያዊ መልዕክትበቫቲካን በሚገኘው የሲኖዶስ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት አዳራሽ ውስጥ ቅዱስነታቸው በተገኙበት ግንቦት 17/2018 ዓ. ም. ይፋ ተደርጓል።

“የሰው ልጅ ታላቅነት” የተሰኘው ሐዋርያዊ መልዕክት ይፋ በተደረገበት ወቅት
“የሰው ልጅ ታላቅነት” የተሰኘው ሐዋርያዊ መልዕክት ይፋ በተደረገበት ወቅት   (@Vatican Media)

ፍጹም ወሳኝነት ያለው አስተዋጽኦ

ፕሮፌሰር አና ሮውላንድስ ከዝግጅቱ ጎን ለጎን ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፥ የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ መልዕክት በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ፍጹም ወሳኝ አስተዋጽኦ እንደሆነ ገልጸው፥ የመጀመሪያው በሠነዱ ውስጥ በተካተቱት ቴክኖሎጂያዊ ጉዳዮች ላይ የሰው ልጅ ከፍተኛ አስቸኳይነት እያጋጠመው እንደሆነ ተናግረዋል።

በመሆኑም በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ለማሰብ ዛሬ ነገ ማለት እንደማይገባ አሳስበው፥ በሥራ ዘርፎችች፣ በስደተኞች፣ በቤተሰብ፣ በፖለቲካ ማኅበረሰብ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚፈጠሩ ግጭቶች ላይ ያላቸው ተጽእኖ ትላንትም፣ ዛሬም፣ ነገም ይቀጥላል” ሲሉ በማስረዳት፥ በተመሳሳይም ብዙ ሰዎች በሰው ሠራሽ አስተውሎት ዙሪያ በሚነሱ ጥያቄዎች ላይ ለመሳተፍ እርግጠኛ ወይም ብቁ አለመሆናቸውን ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሐዋርያዊ መልዕክታቸው ውስጥ፥ “ምናልባት ሌላ ሰው ስለእነዚህ ነገሮች ያስባል የሚል ተስፋ አለ” ማለታቸው በመጥቀስ፥ ነገር ግን ስለ እነዚህ ጉዳዮች አብረን ማሰብ አለብን” ሲሉ ፕሮፌሰር አና አሳስበዋል።

ሁሉም ድምጾች የሚሰሙባቸው መድረኮች አስፈላጊነት

“የሰው ልጅ ታላቅነት” ከተሰኘ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሐዋርያዊ መልዕክት ማዕከላዊ ጉዳዮች መካከል አንዱ፥ እነዚህን ጥያቄዎች በዋነኝነት በትርፍ ላይ በተመሠረቱ የግል መድረኮች ላይ ብቻ እንዳይቀሩ ማረጋገጥ እንደሚገባ ፕሮፌሰር አና ጠቁመዋል።

“በተለይም በማኅበረሰብ ውስጥ በአልጎሪዝም ሥርዓት፣ በዲጂታል አድማስ እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ዓለም እውነታ እጅግ የተጎዱ ሰዎች ድምጾች በቅድሚያ የሚሰሙበት የጋራ መድረኮችን እንዴት እንፈጥራለን?” ሲሉ ፕሮፌሰር አና ጠይቀዋል።

እነዚህ ድምጾች የጋራ ጥቅምን ለማስተዋወቅ ያታለመ ማንኛውም ውይይት ማዕከላዊ መሆን እንዳለበት አጥብቀው የተናገሩት ፕሮፌሰር አና፥ ሐዋርያዊ መልዕክታቸው ራሱ በሰብዓዊነት ዙሪያ ጥልቅ ሞራላዊ እና መንፈሳዊ ጥያቄዎችን በማንሳት በዓለም አቀፍ ደረጃ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ልዩ ድምጽ ማስተጋባቱን ገልጸዋል።

ፕሮፌሰር አና ሮውላንድስ ንግግር ሲያደርጉ
ፕሮፌሰር አና ሮውላንድስ ንግግር ሲያደርጉ   (@Vatican Media)

ቅዱስነታቸው በቁልፍ ጥያቄዎች ላይ ማኅበረሰቡ እንዲያስብበት ጋበዙ

“የሰው ልጅ ሕይወት ምን ይመስለናል? እኛ እንደ ሰው ማን ነን? በሰብዓዊነታችን እና አብረን በምንኖረው ሕይወታችን ውስጥ ምን ራዕይ እና ግብ አለን?” በሚሉት መሠረታዊ ጥያቄዎች ላይ  እንዲያስብበት ማኅበረሰቡን ጋብዘዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሁለት እጅግ ጠንካራ ትችቶች አቅርበውልናል” ሲሉ የቀጠሉት ፕሮፌሰር አና፥ ሰው መሆን ምን ማለት እንደሆነ፥ በተለይም በፖለቲካ፣ በጦርነት፣ በግጭት ወይም በኢኮኖሚ አውድ ውስጥ በሌሎች ላይ ሥልጣንን በመጠውቀም የበላይነት የሚያስቀምጡ የተሳሳቱ ትረካዎች መኖራቸውን ገልጸው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከእነዚያ ትረካዎች በተቃራኒ “የፍቅር ሥልጣኔ ውብ ራዕይ” ሲሉ የገለጹትን ሃሳብ አቅርበዋል።

የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ መልዕክት የሰው ልጅ የጋራ የሞራል አስተሳሰብ እንዲኖር የሚያሳስብ መሆኑን የተናገሩት ፕሮፌሰር አና፥ በተለይም “አንዱ ሌላውን የማየት መንገድ እና የሰው ልጅን ውስጣዊ እሴት የሚያውቅ ዓለም” እንዲኖር ያሳስባል ብለዋል።

ፕሮፌሰር አና በማከልም፥ የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ መልዕክት የሰውን ልጅ ክብር ወደ ቴክኖሎጂ መሣሪያዎች ከማስተላለፍ ወይም ሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ከሰው ልጅ ራሱ የበለጠ ሰብዓዊ ሊሆን እንደሚችል በማሰብ ሰብዓዊነታችንን ይቀንሳል” ብለዋል።

የረጅም ጊዜ ተጽእኖ ለመፍጠር የቀረበ ግብዣ

“የፍቅርን ሥልጣኔ በኅብረት መገንባት ያስፈልጋል” ያሉት ፕሮፌሰር አና፥ “ይህንን የምናደርገው ለፍቅር የተፈጠርን፣ ፍትህን የምንናፍቅ እና ያንን ዓለም መገንባት የምንችለው በተሳትፎ አብረን በምንፈጥረው የጋራ ስሜት ውስጥ ሙሉ በሙሉ በመኖር ብቻ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ፕሮፌሰር አና በሰፊው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ ባሕል ውስጥ በሚገኘው “የሰው ልጅ ታላቅነት” በተሰኘ ሐዋርያዊ መልዕክት ላይ በማሰላሰል፥ ሐዋርያዊ መልዕክቱ የሰው ልጅን የማሰብ ችሎታ የሚመለከት በመሆኑ ገና ለጋ እና አዲስ እንደሆነ አስረድተው፥ “ነገር ግን በኢንዱስትሪ፣ በካፒታሊዝም፣ በሥራ ሁኔታ እና በሰው ልጅ የቴክኖሎጂ ትርጉም ላይ በሚያተኮሩ ሐዋርያዊ መልዕክቶች ረጅም ባሕል ውስጥ ይገኛል” ብለዋል።

ፕሮፌሰር አና በመጨረሻም፥ “የሰው ልጅ ታላቅነት” የተሰኘ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሐዋርያዊ መልዕክት ከአሁኑ ጊዜ በላይ ቀጣይ ትውልዶችንም ጭምር የሚነካ ነው” በማለት ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ደምድመዋል።

“የሰው ልጅ ታላቅነት” የተሰኘው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሐዋርያዊ መልዕክት ይፋ የሆነበት ዝግጅት
“የሰው ልጅ ታላቅነት” የተሰኘው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሐዋርያዊ መልዕክት ይፋ የሆነበት ዝግጅት   (@Vatican Media)

 

 

27 May 2026, 16:52