ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ ሥርዓተ አምልኮ ቤተ ክርስቲያንን የሚደግፍ እና እምነቷን የሚገልጽ መሆኑን አስታወቁ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ረቡዕ ግንቦት 12/2018 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ታዳሚዎች ሳምንታዊውን የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ክፍል አቅርበዋል። ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ቅዱስ የአምልኮ ሥርዓትን በማስመልከት በመጀመሪያ ሠነዱ ላይ ባወጣው ደንብ ላይ በማስተንተን ባቀረቡት አስተምህሮ፥ ሥርዓተ አምልኮ ምእመናንን እንደሚደግፍ እና እያንዳንዱ የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት በጸሎት ላይ ለምትገኝ ቤተ ክርስቲያን እውነተኛ ጥምቀት እንደሚሆን አስረድተዋል።

“በክርስቶስ ለማድረግ የወደደውን የአሳቡን፥ የፈቃዱን ምሥጢር አስታውቆናል፤ በሰማይ እና በምድር ያለውን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል፥ በዘመን ፍጻሜ እንዲሆን እንዳቀደው እንደ ፈቃዱ እና እንደ ምክሩ ሁሉን የሚያከናውን እንደ እርሱ ዓላማ የተወሰንን በክርስቶስ በርስትነት ተቀበለን” (ኤፌ.1:9-11)።

ክቡራት እና ክቡራን ከዚህ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዛሬው ዕለት ለምዕመናኑ ያቀረቡትን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትርጉም ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞች እና እህቶች፥ እንደምን አደራችሁ! እንኳን ደህና መጣችሁ! ዛሬ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ባዘጋጀው በመጀመሪያው ሠነድ ላይ ስለ ትምህርተ ክርስቶስ የገለጻቸውን አዳዲስ ተከታታይ ደንቦችን መመልከት እንጀምራለን። ከደንቦቹ መካከል አንዱ ቅዱስ የአምልኮ ሥርዓትን የሚመለከት ነው (ቅዱስ ጉባኤ ‘Sacrosanctum Concilium)።

የጉባኤው አባቶች ይህንን ደንብ ሲያዘጋጁ በአምልኮ ሥርዓቶች ላይ ማሻሻያ ለማድረግ ብቻ ሳይሆን፥ የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ምስጢር የሆነው፥ ቤተ ክርስቲያንን ስለሚያዋህዳት እና ስለሚያስተሳስራት ሕያው ትስስር እንድታስብ እና እንድታጠናክር ለማድረግ ነው። በእርግጥም የአምልኮ ሥርዓት የዚህ ምስጢር ዋና ልብ ነው። የአምልኮ ሥርዓት ቤተ ክርስቲያን ከኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወትን የምትቀበልበት ቦታ፣ ጊዜ እና አውድ ነው። ምክንያቱም ‘በአምልኮ ሥርዓት ውስጥ የቤዛችን ሥራ ይፈጸማል’ (ቅዱስ  ጉባኤ: 2)። ይህም ‘እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን አስደናቂ ሥራ እንድታውጁ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ እግዚአብሔር ለራሱ ያደረጋችሁ ቅዱስ ሕዝብ ናችሁ’ (1ኛ ጴጥ. 2:9)።

ቤተ ክርስቲያን በሃያኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ ባሳለፈቻቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ፣ የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮአዊ እና ሥርዓተ አምልኮአዊ እድሳት ላይ እንደተገለጸው፥ ጥያቄ ውስጥ ስለ ገባው ምስጢር ግልጽ እውነታን ያመለክታል። ይህም የእግዚአብሔር የማዳን ዕቅድ እንዲፈጸም ነው። ከሁሉ የተደበቀውን እና በኢየሱስ ክርስቶስ የተገለጠውን ምስጢር በማስመልክት ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ማረጋገጫ ይሰጠናል፥ ‘በእርግጥ ስለ እናንተ ሲባል ስለ ተሰጠኝ ስለ እግዚአብሔር ጸጋ መጋቢነት ሰምታችኋል፤ አስቀድሜ በአጭሩ እንደ ጻፍሁ፥ ይህን ምሥጢር በመግለጥ አስታወቀኝ፤ ይህንም ስታነቡ የክርስቶስን ምሥጢር እንዴት እንደማስተውል ልትመለከቱ ትችላላችሁ፤ ይህ ምስጢር አሁን ለቅዱሳኑ ሐዋርያት እና ለነቢያት በመንፈስ እንደተገለጠው ባለፉት ትውልዶች ለነበሩ አልተገለጠም ነበር። ይህ የሆነው አሕዛብ አብረው እንዲወርሱ፥ በአንድ አካልም አብረው እንዲሆኑ፥ በወንጌልም አማካይነት በክርስቶስ ኢየሱስ የሆነውን የተስፋ ቃል አብረው እንዲካፈሉ ነው (ኤፌ. 3:2-6)። እንግዲህ የክርስቲያን ምስጢር ይህ ነው። በምስጢራዊ መንገድ የተገለጠልን የብርሃነ ትንሳኤው ክስተት ማለትም የክርስቶስ ሕማማት፣ ሞቱ፣ ትንሣኤው እና ክብሩ በሥርዓት አምልኮ በኩል በትክክል ቀርቦልናል። ስለዚህም በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በተሰበሰበው ጉባኤ (ማቴ. 18:20) ውስጥ በተሳተፍን ቁጥር በዚህ ምስጢር ውስጥ እንገባለን።

ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ የቤተ ክርስቲያኑ ምስጢር ውስጣዊ ምንጭ ነው። የእግዚአብሔር ቅዱሳን ሕዝቦችም፣ በመስቀል ላይ ከተወጋ ጉኑ የወጡ ናቸው። በቅዱስ አምልኮ ውስጥ በቅዱስ መንፈሱ ኃይል መሥራትን ይቀጥላል። ሙሽራይቱ የሆነች ቤተ ክርስቲያኑን ለአባቱ መስዋዕት አድርጎ ይቀድሳታል፣ አንድ ያደርጋታል። ኢየሱስ ክርስቶስ በሚታወጀው ቅዱስ ቃል፣ በቅዱስ ቁርባን፣ በሚያከብሩት አገልጋዮች፣ በስሙ በሚሰበሰቡት ምዕመናን እና በከፍተኛ ደረጃ በሚቀርብ ቅዱስ ቁርባኑ፥ ፍጹም ልዩ የሆነውን ክኅነቱን ይለማመዳል (ቅዱስ ጉባኤ 7)። ቅዱስ አጎስጢኖስ፥ ‘ቤተ ክርስቲያን መስዋዕተ ቅዳሴን በማቅረብ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ ትቀበላለች፤ ሥጋውም ትሆናለች’ ሲል ገልጿል (ስብከቱ ቁ. 277)። ‘በእርሱም እናንተ ደግሞ ለእግዚአብሔር መኖሪያ ለመሆን በመንፈስ አብራችሁ ትሠራላችሁ’ (ኤፌ. 2:22)። ይህም ከክርስቶስ ጋር የሚያስተካክል እና በኅብረት የሚያንጸን የቤዛችን ሥራ ነው።

በመስዋዕተ ቅዳሴ ውስጥ ይህ አንድነት የሚገኘው በአምልኮ ሥርዓቶች እና በጸሎት ነው (ቅ. ጉ. 48)። የምልኮ ሥርዓት ቤተ ክርስቲያን እምነቷን የምትገልጽበት መንገድ ነው። በተለመደው አገላለጽ ‘የጸሎት ሥርዓት የእምነት ሥርዓት ነው’። እንደዚሁም ይህ ሥርዓት የቤተ ክርስቲያንን ማንነት ይገልፃል። ለምዕመናን የሚሰበክ ቅዱስ ቃል፣ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት፣ በእንቅስቃሴ የሚገጡ ምልክቶችን፣ ጸጥታዎች እና ቦታዎች፥ ይህ ሁሉ በእግዚአብሔር አብ ስም፣ በኢየሱስ ክርስቶስ አካል እና በመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ ውስጥ የተሰበሰቡ ምዕመናንን ይወክላል፣ ቅርፅም ይሰጣል። ስለዚህ እያንዳንዱ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት የቤተ ክርስቲያን እውነተኛ ጸሎት ይሆናል። የር. ሊ. ጳ. ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ 25ኛ መታሰቢያ  ሐዋርያዊ መልዕክት ቁ. 9)።

የአምልኮ ሥነ-ሥርዓቱ የኢየሱስ ክርስቶስን ምስጢር የሚያገለግል ከሆነ፥ ‘የቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴ የሚመራው ኃይሏ ሁሉ ወደሚፈስበት ነው’ ተብሎ ለምን እንደተገለጸ መረዳት ይቻላል (ቅ. ጉ. 10)። የቤተ ክርስቲያን ተግባር በሥርዓተ አምልኮ ብቻ የተወሰነ አለመሆኑ እውነት ነው። ሆኖም ግን እንቅስቃሴዋ ሁሉ፥ ስብከቷ፣ ድሆችን ማገልገሏ፣ የሰው ልጅ እውነታዎችን ማጀቧ ወደዚህ ግብ ይሰበስባል። ሥርዓተ አምልኮ ምዕመናንን በጌታችን ፋሲካ ውስጥ ዘወትር በአዲስ መልክ እንዲገቡ ይደግፋቸዋል። ስለዚህ በቃሉ ምስክርነት፣ በቅዱሳት ምስጢራት አከባበር፣ በጋራ ጸሎት፣ ለእምነት እና ለተልዕኮአቸው ባላቸው ቁርጠኝነት ይታደሳሉ፣ ይበረታታሉ እና ይለወጣሉ። በሌላ አነጋገር በሥርዓተ አምልኮ ተግባር ውስጥ የምዕመናን ተሳትፎ አንዳንድ ጊዜ ውስጣዊ እና ውጫዊ ይሆናል።

ይህ ማለት ደግሞ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ በሚታይ መንገድ፣ በሥነ-ምግባር እና በመንፈሳዊነት እንዲገለጥ መጠራትን የሚገልጽ ሲሆን፥ የሚከበረው ሥርዓተ አምልኮ ወደ ሕይወት እንዲተረጎም እና በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተለማመዱትን ተጨባጭ ለማድረግ የሚያስችል ታማኝ ህልውና እንዲፈልግ ይጠይቃል። ሕይወታችን ሕያው መስዋዕት፣ ቅዱስ እና በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ያለው የሚሆነው እና መንፈሳዊ አምልኮአችንን የሚያሟላው በዚህ መንገድ ነው። ‘እንግዲህ ወንድሞች ሆይ! ሰውነታችሁን ሕያው መስዋዕት፣ ቅዱስና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ አድርጋችሁ እንድታቀርቡ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፤ ይህም መንፈሳዊ አገልግሎታችሁ ነው’ (ሮሜ 12፡1)።

በዚህ መንገድ በየቀኑ የሚቀርበው የአምልኮ ሥርዓት በውስጡ ያሉትን የእግዚአብሔር ቅዱስ ቤተ መቅደስ አድርጎ ይገነባቸል’ (ቅ. ጉ.2)። ሁሉንም በእንግድነት የሚቀበል ግልጽ ማኅበረሰብ ይፈጥራል። በእርግጥም በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ነው። ከኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት ጋር ያስተዋውቀናል። የእርሱ አካል ያደርገናል። በሁሉም መልኩ በክርስቶስ ውስጥ ያለውን የሰው ልጅ የአንድነት ምልክት ይወክላል። ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንዳሉት፥ ‘ዓለም አሁንም አያውቅም እንጂ ሁሉም ወደ በጉ ሠርግ እራት የተጋበዙ ናቸው’ (ራዕ. 19፡9 ፤ ‘እጅግ ተመኝቼ ነበር’ የተሰኘ ሐዋርያዊ መልዕክት ቁ. 5)።

ውድ ወዳጆቼ ሆይ! በሚቀጥሉት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮች ለመዳሰስ ዕድል እንዲሰጠን በአምልኮ ሥርዓቶች፣ በመንፈሳዊ የእንቅስቃሴ ምልክቶች እና ከሁሉም በላይ ደግሞ በመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ውስጥ የኢየሱስ ክርስቶስ ሕያው መገኘት ውስጣችንን እንዲቀርጽ እናድርግ።” 

20 May 2026, 16:31