ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በዮሐንስ ዘላተራን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ዓመት መጀመሪያ ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በዮሐንስ ዘላተራን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ዓመት መጀመሪያ ላይ   (@Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ እውነት ማንነቱን የሚያገኘው በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ ነው” ሲሉ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በላቲን አሜሪካ አገር ቦሊቪያ የሚገኝ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ 60ኛ ዓመት መታሰቢያን በማስመልከት መልዕክት ልከዋል። ቅዱስነታቸው ለተቋሙ ምሁራን በላኩት መልዕክት፥ እውነት ማንነቱን የሚያገኘው በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ እንደሆነ ገልጸው፥ “እውነት በፍቅር” (Veritas in Caritate) የሚለውን ሐዋርያዊ መልዕክት በመጥቀስ፥ “እውቀት በሥነ-ምግባር በመታገዝ የሰውን ልጅ በፍቅር ማገልገል እንዲሁም ለከፍተኛ የትምህርት ተቋም እና ለሐዋርያዊ ተግባር ግንዛቤ መስፈርት ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ፥ “እውነት በፍቅር” ባሉት ሐዋርያዊ መልዕክታቸው፥ “የእውቀት መከፋፈል፣ አንጻራዊነት እና ግንዛቤን መጠቀሚያ በሚያደርግ ባሕል ውስጥ መልዕክታቸው ለከፍተኛ የትምህርት ተቋም እና ለሐዋርያዊ አገልግሎት ማስተዋል መስፈርት እንዲሁም ለወደፊቱ ዓለም ብርሃን እንድትሆኑ ለተጠራችሁበት ዋና መመሪያ ሆኖ ማገልገል ቀጥሏል” ማለታቸውን አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ይህን ያስገነዘቡት፥ በቦሊቪያ የሚገኝ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ “ሳን ፓብሎ” 60ኛ ዓመት መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ ሐሙስ ግንቦት 6/2018 ዓ. ም. በላኩት መልዕክት ሲሆን፥ የመታሰቢያ በዓሉ ለቤተ ክርስቲያን እና ለኅብረተሰብ አገልግሎት ፍሬያማ መንገድ መሆኑን እንደሚያስገነዝብ አስተውለዋል።

“አንድ ዩኒቨርሲቲ በጥልቅ ማንነቱ የቴክኒክ ስልጠና ማዕከል ወይም ጠቃሚ እውቀት ለማግኘት የሚያስችል ቦታ ብቻ ሳይሆን፥ ከሁሉም በላይ ጥብቅ እና ወሳኝ በሆነ መንገድ የሰውን ክብር እና የባሕል ቅርስ ለመጠበቅ እና ለማዳበር የሚያግዝ ምሁራን ማኅበረሰብ የሚገኝበት ቦታ” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል።

እውነተኛ ትምህርት የሰውን ልጅ ስልጠናን ማበረታታት አለበት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ዩኒቨርሲቲዎች የሰው ልጅ ሁሉ አቀፍ ዕውቀትን ለማበረታታት የሚቋቋሙ መሆናቸውን ገልጸው፥ እውነተኛ ትምህርት የሰውን ልጅ የመጨረሻ ግብ እና የማኅበረሰቦችን ጥቅም ለማሳካት ያለመ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

በዚህም መሠረት “የአዕምሮ እና የግብረ-ገብ ችሎታዎች፥ ኃላፊነት የሚሰማው፣ የጋራ ጥቅምን እና ቁርጠኝነትን በማገናኘት የሚዳብሩ፣ በትክክለኛነት፣ በግልጽ ንግግር እና በታማኝነት ለመሥራት የሚችሉ ሰዎችን ይፈጥራሉ” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “እውነት በፍቅር” (Veritas in Caritate) የሚለው የተቋሙ መሪ ጭብጥ ትርጉም እንዳለው ተናግረው፥ ይህ አገላለጽ ከእምነት አንፃር የዩኒቨርሲቲውን ተልዕኮ በሚገባ የሚያንጸባርቅ መሆኑን አስታውሰዋል።

እውነት ማንነቱን የሚያገኘው በኢየሱስ ክርስቶስ ነው

“እውነት ለክርስትና ባሕል አእምሯዊ አስተሳሰብ ወይም ረቂቅ ፅንሰ-ሃሳብ ብቻ ሳይሆን ይልቁንም ማንነቱን የሚያገኘው ራሱን እውነት ባደረገው፣ ሰውን ሙሉ በሙሉ ለራሱ በሚገልጠው እና ጥሪውን በሚያሳየው በኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት ውስጥ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ከዚህ አንፃር በትክክለኛ አእምሮ እና ሳይንሳዊ ታማኝነት የሚፈለግ እውነት፥ ዋና እና የመጨረሻ መስፈርት በሆነው በፍቅር ውስጥ እንደሚገኝ በማስረዳት፥ ለክርስቲያን እውነትን መናገር የሚያንጽ፣ የሚፈውስ እና ወደ ፍጻሜው የሚመራ የፍቅር ተግባር እንደ ሆነም አስረድተዋል።

እውነት የግል እና የግንኙነት ገጽታ እንዳለው መገንዘብ አስፈላጊ እንደሆነ አፅንዖት የሰጡት ቅዱስነታቸው፥ “እንዲህ ዓይነቱ ግንዛቤ እውቀትን የበላይነት፣ የማግለል ወይም ተራ የጥቅም መሣሪያ ከመሆን ይጠብቃል” ሲሉ ተናግረዋል፥ ይልቁንም ወደ ፍትህ አገልግሎት እና ወደ እያንዳንዱ የሰው ልጅ ክብር በተለይም እጅግ ተጋላጭ ወደ ሆኑት ዘንድ ይመራዋል” ብለዋል።

እውቀት ዘወትር የሰውን ልጅ ማገልገል አለበት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “እውነት በፍቅር” የሚለው ሐዋርያዊ መልዕክት እውቀትን እና ሕይወትን፣ አእምሮን እና ሥነ ምግባርን፣ እምነትን እና ምክንያታዊነትን፣ የትምህርት ልቀትን እና የዜግነት ኃላፊነትን አንድ ላይ ለማዋሃድ የሚፈልግ የአካዳሚያዊ ማኅበረሰብ ጥሪን የሚገልጽ መሆኑን አስታውሰዋል።

ምርምር፣ ማስተማር እና ሙያዊ ስልጠና እንደ አገልግሎት እንጂ ራስን መመዘኛ ሊሆን እንደማይገባ አፅንዖት ሰጥተው፥ እውቀት ዘወትር ለሰው ልጅ አገልግሎት የሚሰጥበት የበለጠ ሰብዓዊ፣ ፍትሃዊ እና ነጻ ማኅበረሰብን በመገንባት ላይ ያተኮረ መሆኑን ተናግረዋል።

ቅዱስነታቸው በመጨረሻም፥ በፍቅር ውስጥ የሚገኝ እውነት አስተዋይነትን እንዲመራ በማሳሰብ፥ የትምህርት፣ የአስተሳሰብ እና የማኅበረሰብ ጥረት የጥበብ መቀመጫ ለሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እናታዊ አማላጅነት እንዲሰጥ ዩኒቨርሲቲውን በማበረታታት መልዕክታቸውን ደምድመዋል።

 

14 May 2026, 11:16