ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ በካስቴል ጋንዶልፎ ከጋዜጠኞች ጋር ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ በካስቴል ጋንዶልፎ ከጋዜጠኞች ጋር ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ 

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ የሚሰቃየውን የጋዛ ሕዝብ መርዳት እንደሚገባ እና ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ማክሰኞ ምሽት በካስቴል ጋንዶልፎ ከጋዜጠኞች ጋር ተገናኝተው ባደረጉት ንግግር፥ ለጋዛ ነዋሪዎች ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲደረግላቸው በማሳሰብ፥ ሰብዓዊ መብቶች አንዲከበሩ ጥሪ በማቅረብ አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በዚህ ጥሪያቸው በጦርነት አውድማ ለሰው ልጅ ሕይወት ችላ የሚለው የሰው ሠራሽ አስተውሎት አጠቃቀም በመናገር እና ከሰው ሠራሽ አስተውሎት “AI” አምራች ኩባንያ አንትሮፒክ ጋር የሚደረገውን ውይይት በማስመልከት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ማክሰኞ ምሽት በካስቴል ጋንዶልፎ ለጋዜጠኞች ባደረጉት ንግግር፥ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለጋዛ ሕዝብ ዕርዳታ እንዲያደርግ በድጋሚ ጥሪ በማቅረብ የሁሉም ሰው ሰብዓዊ መብቶች መከበር እንዳለባቸው አጥብቀው ተናግረዋል።

በጋዛ የ “ግሎባል ሱሙድ ፍሎቲላ” ሰልፍ የሚሳተፉ የማኅበረሰብ አንቂዎችን በማስመልከት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፥ አንዳንዶች እጃቸውን በሰንሰለት ታስረው ዓይናቸውን መሸፈናቸው ከተዘገበ በኋላ “የእያንዳንዱ ሰው ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ ያቀረብነውን አቤቱታ ማደስ አለብን” ብለዋል።

በጋዛ ውስጥ በሲቪሎች ላይ እየደረሰ ባለው ተከታታይ ስቃይ ማዘናቸውን ገልጸው፥ “እንደ አለመታደል ሆኖ የጋዛ ሕዝብ አሁንም ሰብዓዊ ዕርዳታ እያገኘ አይደለም” ብለው፥ ይህ ሁኔታ ተቃውሞዎችን እያስነሳ እና በፍሎቲላ ውስጥ የተሳተፉትን ጨምሮ ውስብስብ ችግሮች እንዳሉበት አብራርተዋል።

“ይህን እንደ ግብዣ ብቻ ሳይሆን እንደ ይግባኝ ማደስ እፈልጋለሁ” ሲሉ ተናግረው በመቀጠልም፥ ሁሉም ባለስልጣናት የጋዛን ሕዝብ ለመርዳት እንዲተባበሩ እና መልሶ ግንባታውን እንዲጀምሩ አሳስበው፥ “ሕዝቡ እጅግ በጣም እየተሰቃየ ይገኛል” ሲሉ አስረድተዋል።

“መሣሪያ ያልታጠቁ የሰላም ተሟጋቾችን ማሰቃየት ምን ማለት ነው?” ተብለው የተጠየቁት ቅዱስነታቸው፥ ይህ ተጨማሪ ጥላቻ አደጋን ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቀው፥ አመጽ እየጨመረ የሚሄድ እና ጥላቻን የሚያስነሳ በመሆኑ የትኛውንም ወገን አይረዳም” ብለዋል። በምትኩ ወደ ድርድር ተመልሶ በውይይት ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ በማሳሰብ፥ የሁሉም ሰው ሰብዓዊ መብቶችን ማክበር ዘወትር አስፈላጊ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተዋል።

ሰው ሠራሽ አስተውሎትን “ትጥቅ ማስፈታት”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዘመናዊው ጦርነት ውስጥ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሚና መጨመሩን ተናግረው፥ ከሰው ልጅ ሕይወት ዋጋ የራቀ የቴክኖሎጂዎች ውሳኔ አሰጣጥን አስጠንቅቀዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በመካከለኛው ምሥራቅ ሊባኖስን ጨምሮ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የተከሰቱ ግጭቶችን በመጥቀስ፥ ዛሬ ጦርነት በሰው ሠራሽ አስተውሎት እገዛ እየተካሄደ እንደሚገኝ እና “የተገደሉ ሰዎች የዚህ ሁሉ ሰለባዎች ናቸው” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ይህን በአእምሯቸው ይዘው የሰላም ጥሪያቸውን በማቅረብ፥ የሰው ሠራሽ አስተውሎትን “ትጥቅ ማስፈታት” አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል።

ከ “AI” አምራች ኩባንያ አንትሮፒክ ጋር የተደረገ ውይይት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቅርቡ “የሰው ልጅ ታላቅነት” የተሰኘ ሐዋርያዊ መልዕክት ይፋ ካደረጉ  በኋላ ቫቲካን ከዋና ዋና የሰው ሠራሽ አስተውሎት አምራች ኩባንያዎች ጋር የተጀመረው ውይይት አሁንም መቀጠሉን ገልጸዋል።

ቅዱስነታቸው በማከልም በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት እና አንትሮፒክ በተሰኘ የሰው ሠራሽ አስተውሎት አምራች ኩባንያ መካከል ቀጣይነት ያለው ውይይት እንደሚደረግ እና “ከዚህም በፊት አንድ ዓይነት የጋራ ሥራ ነበረ” ሲሉ አብራርተው፥ በሁለቱም ወገኖች ግብዣቸው ተቀባይነት ማግኘቱን ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመጨረሻም፥ “ሰው ሠራሽ አስተውሎትን ‘ትጥቅ ለማስፈታት’ ውይይቱን መቀጠል እጅግ አስፈላጊ ነው” ሲሉ ቃለ ምልልሳቸውን ደምድመዋል።

 

 

27 May 2026, 16:45