ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ በግጭት በተጎዳ ዓለም ውስጥ ክርስቲያኖች አንድነትን እንዲመሰክሩ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“የክርስቲያኖች ሙሉ አንድነት የሩቅ ግብ ብቻ ሳይሆን አስቸኳይም ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ዓለምን እያስጨነቁት እና በተለይም መካከለኛውን ምሥራቅ እያወደሙት ባሉት ግጭቶች አንፃር አንድነትን ማበረታታት እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ አስገንዝበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የኮፕት እና የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት የወዳጅነት ቀንን ምክንያት በማድረግ ከእስክንድርያው የቅዱስ ማርቆስ መንበር ተተኪ እና በግብጽ የኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ታዋድሮስ ዳግማዊ ጋር ባደረጉት ውይይት እና የጽሑፍ መልዕክት ልውውጥ፥ ቁርጠኛ እና ይበልጥ ጠንካራ የሆነ የክርስቲያኖች አንድነት ማስፈለጉን አረጋግጠዋል።
እንደ ቅድስት መንበር መግለጫ መሠረት፥ የሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ውይይት በእምነት እና በበጎ አድራጎት ላይ በተመሠረቱ ውይይቶች ላይ የሚደርሱ ማናቸውንም እንቅፋቶች ለማሸነፍ በኮፕት እና በካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የወዳጅነት ቀንን ለማክበር በተወሰደ አዲስ ተነሳሽነት ላይ ያተኮረ እንደ ነበር፥ በተጨማሪም በጦርነት እጅግ በተጎዳ የመካከለኛው ምሥራቅ ወንጌልን ለማወጅ፣ ሰላምን እና እርቅን ለማስፈን ባለው የጋራ ኃላፊነት ላይ ያተኮረ እንደ ነበር ገልጿል።
በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተጀመረ ክቡር ባሕል
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የሁለቱ አብያት ክርስቲያናት የወዳጅነት ቀንን መሠረት በማድረግ፥ ለኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ታዋድሮስ ዳግማዊ በላኩት ድጋሚ መልዕክት፥ ሃሳቡ ከፓትርያርኩ እንደመጣ እና በኋላም በነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተቀብለውት ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።
የዚህ ሃሳብ ዋና ዓላማ የሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ እና ብጹዕ ወቅዱስ ሼኑዳ ሳልሳዊ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1973 ዓ. ም. ባደረጉት ታሪካዊ ግንኙነት የኢየሱስ ክርስቶስን ተፈጥሮ፣ ስብዕና እና ተግባራት በማስመልከት በጋራ የፈረሙት ሠነድ አርባ ዓመት መታሰቢያን ለማክበር እንደ ሆነ ታውቋል።
ከአሥር ዓመታት በኋላ ብጹዕ ወቅዱስ ታዋድሮስ ዳግማዊ እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ግንቦት ወር 2023 ዓ. ም. እንደገና መገናኘታቸው ይታወሳል። የመጀመሪያው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የተሰበሰቡትን ምዕመናን በኅብረት ለመባረክ የተገናኙበት ሲሆን፥ ከዚያም በማግሥቱ የቅዱስ ቁርባን ተስፋን እንደገና ለማረጋገጥ እና እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2015 ዓ. ም. በእስላማዊ መንግሥት አሸባሪዎች በሊቢያ የባሕር ዳርቻ የተገደሉትን 21 የኮፕት ክርስቲያኖች ለማስታወስ የተገናኙበት እንደ ነበር ይታወሳል።
እነዚያ 21 ክርስቲያኖች ዛሬ በሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እና በሐዋርያው ቅዱስ ማርቆስ መንበር መካከል የመንፈሳዊ ኅብረት ምልክት በመሆን በሮም ቤተ ክርስቲያን የሰማዕትነት ጥናት ውስጥ ተካትተው እንደሚገኙ ሲታወቅ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በተወደዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተጀመረው የኮፕት እና የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት የወዳጅነት ቀን ክብረ በዓል ለጋራ ጉዞ አዲስ እድገት የሚሰጥ፥ መለያየትን እና አለመግባባቶችን በማስወገድ አዲስ የእርቅ ጉዞ እንዲጀመር ያሳሰቡበት ክቡር ዓላማ እንዲቀጥል አድርገዋል።
“ዓለማችን በብዙ ግጭቶች ውስጥ በወደቀችበት በዚህ ወቅት በተለይም የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ክርስቲያኖች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ለሙሉ አንድነት በመጣር በአንድነት ስለ ሰላም መመስከር አለባቸው” ብለው፥ ይህን በማድረግ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በተሰቃዩት ሥፍር ቁጥር በሌላቸው ሰማዕታት ከፍተኛ ምልጃ እና ምሳሌ ላይ መተማመን እንችላለን” ብለዋል።
የእግዚአብሔርን ቸርነት ለሰው ልጅ መመስከር
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የኮፕት እና የካቶሊክ እምነቶች የወዳጅነት ቀን ምክንያት በማድረግ እሁድ ግንቦት 2/2018 ዓ. ም. በሰሜን ጣሊያን ቬኒስ ከተማ በሚገኘው በቅዱስ ማርቆስ ባዚሊካ ውስጥ መስዋዕተ ቅዳሴን ላቀረቡት የኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ታዋድሮስ ዳግማዊ ወንድማዊ ሰላምታ መላካቸው ይታወሳል።
ሁለቱ የሃይማኖት መሪዎች እስከ ዛሬ በአካል ባይገናኙም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ መሪነት በተመረጡበት ወቅት ብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ታዋድሮስ ዳግማዊ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት ልከው እንደ ነበር የሚታወስ ሲሆን፥ እንዲሁም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ “ከተወዳጇ የኮፕት ቤተ ክርስቲያን ጋር በኅብረት የሚደረግ የወዳጅነት ጉዞ በኢየሱስ ክርስቶስ ዕርዳታ ወደ ፍጹም አንድነት እንዲመራን” በማለት በጸሎት መጠየቃቸው ይታወሳል።
“ወዳጅነት ለእኛ ለክርስቲያኖች የሚያሻማ ስሜት ሳይሆን የሕይወታችን እና የእምነታችን ዋና ማዕከል ነው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ “ወዳጆቼ ሆይ!” ብሎ ይጠራ እንደ ነበር እና “ነፍሱን ለወዳጆቹ አሳልፎ ከመስጠት የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም’ ብሎ እንደሚያስተምረን አስታውሰዋል። “ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ ከእኛ ጋር ባለው ወዳጅነት ላይ በመመሥረት ለሰው ልጆች ሁሉ ስለ መለኮታዊ የበጎ አድራጎት ሥራ አብረን በመመስከር በራሳችን እና በቤተ ክርስቲያኖቻችን መካከል ያለውን ወዳጅነት ማጠናከር እንችላለን!” ብለዋል።
ውይይት እና አንድነት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ2003 ዓ. ም. ጀምሮ እጅግ ፍሬያማ በሆነ ሥነ-መለኮታዊ ውይይት ላይ የተሰማራው የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እና የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ዓለም አቀፍ የጋራ ሥነ-መለኮታዊ ውይይት ኮሚሽን፥ “ሁሉም አንድ እንዲሆኑ” የሚለውን የኢየሱስ ክርስቶስን ጸሎት እውን ለማድረግ በተቻለ ፍጥነት ሥራውን ሊጀምር እንደሚችል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዚሁ መልዕክታቸው፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ጥቅምት ወር 2025 ዓ. ም. በዋዲ ኤል ናትሩን በሚገኘው በቅዱስ ቢሾይ ገዳም “እምነት እና ሥርዓት” በሚል ርዕሥ በተካሄደው ስድስተኛው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ የተሳተፉትን ጨምሮ በርካታ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ልዑካንን በማስተናገዷ የኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን አመስግነዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እንዲሁም፥ የመጀመሪያው የኒቂያ ጉባኤ 1700ኛ ዓመት መታሰቢያ ላይ የተደረጉ አስተንትኖዎች የቤተ ክርስቲያኗን ተጨባጭ አንድነት ለማሳካት ያለንን ፍላጎት እንደገና እንደሚያነሳሳ ያላቸውን እምነት ገልጸው፥ “ይህም በኒቂያው ጸሎተ ሃይማኖት ውስጥ የምናገኘው አንድነት እንዲገኝ ከልብ እጸልያለሁ” ብለዋል።
“የጴንጤቆስጤ በዓልን ለማክበር በምንዘጋጅበት በዚህ ወቅት፥ የኮፕት ኦርቶዶክሶችን እና ካቶሊኮችን ወደ ሙሉ ኅብረት በሚወስደን የጋራ ጉዞ በእውነት እና በፍቅር እንዲመራን” በማለት መንፈስ ቅዱስን ተማጽነዋል።
