ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአልጄሪያ ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአልጄሪያ ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት  (ANSA)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሚቀጥለው ዓመት መስከረም ላይ ፈረንሳይን እንደሚጎበኙ ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ከመስከረም 15-18/2019 ዓ. ም. በፈረንሳይ ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደሚያደርጉ የቅድስት መንበር መግለጫ አስታውቋል። ይህም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በ18 ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደሚሆን ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ማቴዎ ብሩኒ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከመስከረም 15-18/2019 ዓ. ም. በፈረንሳይ ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።

የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2008 ዓ. ም. በፓሪስ እና በሉርድ ሐዋርያዊ ጉብኝት ካደረጉበት ጊዜ ወዲህ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በፈረንሳይ ይፋዊ ጉብኝት ሲያደርጉ የመጀመሪያው እንደሚሆን ተገልጿል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የፈረንሳይ ጉብኝት ይፋ የሆነው፥ የፈረንሳይ ርዕሠ መስተዳድር፣ የፈረንሳይ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ መሪዎች እና በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት “ዩኔስኮ” ዋና ዳይሬክተር ላደረጉላቸው ግብዣ ምላሽ ለመስጠት መሆኑን የቅድስት መንበር መግለጫ አስታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በፈረንሳይ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት “ዩኔስኮ” ዋና መሥሪያ ቤትን እንደሚጎበኙ ታውቋል።

የቫቲካን እና የፈረንሳይ መንግሥታት ግንኙነቶች

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ መንበር ከተመረጡ በኋላ ከፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙት ሚያዝያ 2/2018 ዓ. ም.  እንደ ነበር ይታወሳል።

ሆኖም ይህ የፕሬዚዳንት ማክሮን ጉብኝት የመጀመሪያቸው ሳይሆን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2017 ዓ. ም. ለፕሬዝደንትነት ከተመረጡ በኋላ ቫቲካንን ለበርካታ ጊዜ ጉብኝተው እንደ ነበር እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2018፣ በ2021 እና በ 2022 በቫቲካን ተቀብሎአቸው እንደ ነበር ይታወሳል።

ሁለቱም መሪዎች እንደ ጎርጎሮሳውያኑ መስከረም ወር 2023 ዓ. ም. በማርሴይ ባደረጉት የግል ውይይት፣ በሰኔ 2024 ዓ. ም. በቦርጎ ኢግናዚያ በተካሄደው የ G7 ጉባኤ እና ከዚያም በታኅሳስ 2024 በአጃቺዮ ባደረጉት የግል ውይይት ወቅት እንደገና ተገናኝተው እንደ ነበር ይታወሳል።

 

18 May 2026, 17:45