የሩሲያ ጦር በዩክሬን ላይ ከሚፈጽማቸው ጥቃቶች መካከል አንዱ የሩሲያ ጦር በዩክሬን ላይ ከሚፈጽማቸው ጥቃቶች መካከል አንዱ 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዩክሬን ላይ የሚፈጸሙ የተጠናከሩ ጥቃቶችን አወገዙ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ረቡዕ ግንቦት 19/2018 ዓ. ም. ለታዳሚዎች ሳምንታዊ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ባቀረቡበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፥ የሩሲያ ጦር በዩክሬን ላይ የፈጸመውን የቅርብ ጊዜ ጥቃቶችን ተከትሎ ጦርነት ችግሮችን እንደማይፈታ አፅንዖት በመስጠት የሰላም ጥሪ አቅርበዋል። አክለውም ሚሳኤሎች እና ድሮኖች በሚወድቁበት ሥፍራ ሁሉ የሰላም ተስፋ እንደሚፈርስ፣ የአምልኮ ቦታዎች፣ መኖሪያ ቤቶች እና የንጹሃን ሕይወትም እንደሚፈርስ አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“በቅርቡ በከፍተኛ ደረጃ እየተባባሰ የመጣውን የዩክሬን ጦርነት በጭንቀት እከተላለሁ” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ በሲቪሎች ላይ በተፈጸሙት ጥቃቶች ምክንያት ለሚሰቃዩት በሙሉ ያለኝን ቅርበት መግለጽ እፈልጋለሁ” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ይህንን የማጽናኛ መልዕክት ያስተላልፉት፥ የሩሲያ ጦር በዩክሬን ላይ አዲስ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ ረቡዕ ግንቦት 19/2018 ዓ. ም. ባቀረቡት ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ማጠቃለያ ላይ እንደ ሆነ ታውቋል።

“ጦርነት መከራን እና ጥላቻን ያባብሳል እንጂ ችግሮችን ሊፈታ ወይም ደህንነትን ሊገነባ አይችልም” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ሚሳኤሎች እና ድሮኖች በወደቁበት ሥፍራ ሁሉ ተስፋም ይወድቃል፤ ቤቶች እና የአምልኮ ሥፍራዎች ይወድማሉ፣ የንጹሃን ሕይወትም ይፈርሳል” ሲሉ ተናግረው፥ በጦርነት የተጎዱትን ሁሉ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሰላም ንግሥት ጥበቃ አደራ ሰጥተዋል።

ለሊባኖስ ምዕመናን የተላከ የመጽናኛ እና የእምነት ቃል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በሳምንታዊው የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው ወቅት ለአረብኛ እና ለፈረንሳይኛ ተናጋሪ ምዕመናን ባደረጉት ንግግር፥ በሊባኖስ ውስጥ አዲስ ጥቃት መሰንዘሩን አስታውሰው፥ አስተምህሮአቸውን ሲከታተሉ ለነበሩ የሊባኖስ ምዕመናን መጽናናትን ተመኝተውላቸዋል።

“እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሁልጊዜ ከእኛ ጋር ትገኛለች፣ ትጸልያለች፣ በእናታዊ ፍቅሯ ትንከባከበናለች” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ የእግዚአብሔርን ቡራኬን በመለመን ዘወትር ከክፉ ነገር ሁሉ እንዲጠብቃቸው በመጸለይ የሊባኖስ ምዕመናንን አጽናንተዋል።

እናቶችን በሙሉ አመስግነዋል

በመጨረሻም፥ በፖላንድ ውስጥ ግንቦት 19/2018 ዓ. ም. የሚከበረውን የእናቶች ቀን በማስታወስ፥ አስተምህሮአቸውን ይከታተሉ ለነበሩት የፖላንድ እናቶች ባደርጉት ንግግር፥ ልጆቻቸው እግዚአብሔርን እንዲወዱ ለሚያደርጉት ጥረት እና ለሚሰጡት ትምህርትም አመስግነዋቸዋል።

“የሕይወት ስጦታን ለልጆቻችሁ በልግስና በማስተላለፋቸው፣ እንክብካቤን በማድረጋቸው፣ ለእግዚአብሔር እና ለባልንጀራዎቻቸው ፍቅርን በማስተማራቸው እናቶችን በሙሉ አመሰግናለሁ” ብለዋል።

ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ዘላቂ ግንኙነት እንዲኖር የሚያደርግ ጸጋን ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተማጽነው፥ በእርሷ ዕርዳታ የፖላንድ ሕዝብ በአገሩ ውስጥ ከፅንስ እስከ ተፈጥሯዊ ሞት ድረስ የእያንዳንዱን ሰው ሕይወት እንዲጠብቅ ካሳሰቡ በኋላ ቡራኬያቸውን ሰጥተዋቸዋል።

 

28 May 2026, 10:33