ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ ቤተ ክርስቲያን በቴክኖሎጂ ላይ እምነት በመጣል ሰዎችን ወደ ክርስቶስ መምራት አለባት ሲሉ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ዓርብ ግንቦት 14/2018 ዓ. ም. “የሰውን ፊት እና ድምጽ መጠበቅ” በሚል ርዕሥ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ጉባኤ ላይ ከተሳተፉት እንግዶች ጋር በቫቲካን ተገናኝተዋል።
በቅድስት መንበር የመገናኛ ጽሕፈት ቤት ከባሕል እና የትምህርት ጉዳዮች ምክር ቤት ጋር በኅብረት ባዘጋጁት የአንድ ቀን ጉባኤ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለዘንድሮ የዓለም የመገናኛ ቀን በላኩት መልዕክት ላይ የሚወያዩ፥ በሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI)፣ በትምህርት እና በሥነ-መለኮት ዘርፎች የተሰማሩ ባለሙያዎችን ማሰባሰቡ ታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለጉባኤው ተሳታፊዎች ባደረጉት ንግግር፥ ቤተ ክርስቲያን የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች ዕድገት በመቅረጽ ረገድ ያላትን ተሳትፎ አረጋግጠው፥ እንዲሁም ሰዎች በጥበብ እንዲጠቀሙባቸው በማስተማር እንደምትረዳም አስረድተዋል።
ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ መገናኛ ብዙሃን በማስመልከት ያወጣውን ደንብ በመጥቀስ፥ ቤተ ክርስቲያን በኢየሱስ ክርስቶስ የተመሠረተችው በእጇ ያሉ ዘዴዎችን በመጠቀም በወንጌል አማካኝነት ለሁሉም ሰው የኢየሱስ ክርስቶስን የማዳን ኃይል ማወጅ መሆኑን አስታውሰዋል።
“ይህ በሁሉ ሰው ዘንድ ያለው መዳንን እና እውነትን የማወቅ ፍላጎት ውሳኔዎቻችንን እና ድርጊቶቻችንን ብቻ ሳይሆን የማኅበራዊ መገናኛ፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂ እና የሰው ሠራሽ አስተውሎት አጠቃቀም እና አቅጣጫም ጭምር ማሳወቅ አለበት” ብለዋል።
ሆኖም ሰብዓዊ ክብርን ያጣ ያልተገደበ የቴክኖሎጂ አጥቃቀም፥ የግንኙነት ፍላጎታችንን ወደሚበዘብዙ መሣሪያዎች እንደሚያመራ ገልጸዋል።
ስለዚህ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ሰዎች እግዚአብሔር እንዳቀደው የሰውን ልጅ እውነተኛ ትርጉም እና ግርማ ማግኘት ይችል ዘንድ ቤተ ክርስቲያን እንድትረዳ አሳስበዋል።
ሰብዓዊነትን የሚያጋጥም ፈተና ቴክኖሎጂያዊ ሳይሆን ሰው መሆን ምን ማለት እንደሆነ በሚያስረዳ የሰብዓዊ ጥናት እንቅፋት እንደሆነ አስረድተዋል።
ሥጋ በለበሰው በኢየሱስ ክርስቶስን ላይ በማሰላሰል ባስተላለፉት መልዕክት፥ "ልባችንን ከክርስቶስ ልብ የምንነጥል ከሆነ እራሳችንን በሚገባ ማወቅ አንችልም" ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ቤተ ክርስቲያን እና መሪዎቿ የወጣቶችን የሚዲያ እና የአዕምሮ እውቀት ለማሳደግ ከትምህርት ሥርዓቶች ጋር በኅብረት እንዲሠሩ ጋብዘው፥ “በዚህ ረገድ ወጣቶች በትኩረት ማሰብን ይማራሉ” ሲሉ አስረድተዋል።
ቤተ ክርስቲያን የወጣቶችን መንፈሳዊ ደኅንነት የምትፈልግ በመሆኗ፥ ቴክኖሎጂን በልክ እና በሥነ-ምግባር ረገድ መጠቀምን እንዲማሩ መርዳት አለብን ብለዋል።
“በተለይ ወጣቶች ለዚህ እውነት ክፍት በመሆን የሕይወትን ትርጉም ለማወቅ ይፈልጋሉ” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “ስለዚህ ወጣቶች ሕያው የሆነው ክርስቶስን እንዲያገኙ እና የቴክኖሎጂን አጠቃቀምን በተሟላ ክርስቲያናዊ የአኗኗር ዘይቤ ጋር እንዲያዋህዱ ማስተማር አለብን” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመልዕክታቸው ማጠቃለያ፥ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ዘመን እና ለእርሱ ያለን ምላሽ ለቤተ ክርስቲያን አስፈላጊ ጭብጥ መሆኑን በመጠቆም፥ ሁሉም ሰው ወደ ሙሉ ብስለት እንዲያድግ ለመርዳት የምትጥር መሆኗን አስገንዝበዋል።
“እነዚህ አስተንትኖዎች በእግዚአብሔር የፈጠራ ንድፍ ውስጥ የሰው ልጅ የጥበብ ውጤት በመሆን በቴክኖሎጂ ላይ እንደገና እምነት እንዲኖረን ያደርጉናል” ብለዋል።
