ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ ስቃይ የሚያስወግድ ሥራን እንደገና የሚያስጀምር ምክር ቤት ማቋቋማቸው ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በሳን ጆቫኒ ሮቶንዶ የሚገኘው እና “ካዛ ሶሊዬቮ ዴላ ሶፈሬዛ” (የእፎይታ ቤት) ፋውንዴሽን ተብሎ የሚጠራው የፒየትሬልቺናው ቅዱስ አባ ፒዮ የጤና አጠባበቅ ማዕከል ለሥር ለቀል ተሃድሶ ምዕራፍ መዘጋጀቱ ታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ቅልጥፍናውን፣ ውጤታማነቱን እና የረጅም ጊዜ ዘላቂነቱን ለማጠናከር እንዲቻል የተሻሉ መፍትሄዎችን ለመለየት ስልጣን ያለውን የፋውንዴሽኑ ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዲስ ውል ፈርመዋል።
የምክር ቤቱ አባላትም የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት ምክትል ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፓውሎ ሩዴሊ፣ የሐዋርያዊ መንበር የባለቤትነት አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጆርዳኖ ፒቺኖቲ እና የፎጃ-ቦቪና ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጆርጆ ፌሬቲ እንደሆኑ ታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በተጨማሪም፥ ለቴክኒክ ኮሚቴነት ዶ/ር ቤንጃሚን ኤስቴቬዝ ደ ኮሚንገስን፣ ዶ/ር ጂኖ ጉሚራቶን እና ጠበቃ አሌሳንድሮ ኤላ ኦያናን መርጠው ሾመዋቸዋል።
ውሳኔው የመጣው ሐዋርያዊ መንበር ለበጎ አድራጎት ሥራዎች ካለው ተነሳሽነት እና እንዲሁም ታላላቅ የቤተ ክርስቲያን ተቋማት ለተልዕኮአቸው ታማኝ ሆነው በመቆየት የለውጥ ፈተናዎችን መጋፈጥ እንዲችሉ ከሚለው ግንዛቤ እንደሆነ ታውቋል።
“የዘመኑ የቴክኖሎጂ፣ የሕግ እና የኢኮኖሚ ለውጥ” የሚለው የቅዱስነታቸው ጽሑፍ፥ “የቤተ ክርስቲያኒቱን ተልዕኮ ከተከታታይ የተሃድሶ ፈተና እንደሚያስቀድም በተለይም በጤና አጠባበቅ ዘርፍ ራዕይን፣ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰትን እና ጥንቃቄ የተሞላበት አስተዳደርን እንደሚጠይቅ ገልጿል።
ከእነዚህ ተቋማት መካከል “ሕሙማንን፣ ምዕመናንን እና ቤተሰብን በክብር ተቀብሎ ለማስተናገድ፣ ለመርዳት እና እንክብካቤን ለመስጠት በማሰብ የተመሠረተው የ “እፎይታ ቤትም” ይገኝበታል ሲል አስታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ይህንን ፈተና ለመጋፈጥ እና ለመወጣት የፋውንዴሽኑን የአሁኑን ሁኔታ በመተንተን፣ ለአገልግሎቱ፣ ለተልዕኮው ዘላቂነት እና ለውጤታማነት የሚያግዙ ጥቃሚ መፍትሄዎችን በመለየት እና ለመፍትሄዎችም ተጨባጭ የትግበራ መንገድ በማሳየት የፋውንዴሽኑን የአመራር እና የቁጥጥር ኮሚሽን ለማቋቋም ወስነዋል” ሲል ጽሑፉ ያስረዳል።
ኮሚሽኑ በሁሉም ማለትም በኢኮኖሚያዊ፣ አባታዊ እና ተግባራዊ መስኮች ላይ አዲስ አስተዳደር በማዋቀር አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ሙሉ አቅም እንዳለውም ተገልጿል።
ኮሚሽኑ በተጨማሪም ልዩ ጠቀሜታ ያለውን ማንኛውንም ዓይነት ውሳኔ ከመውሰዱ በፊት፥ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ልዩ ጠቀሜታ ያላቸውን ድርጊቶች ወይም በፋውንዴሽኑ ንብረቶች ላይ ወሳኝ እና ጉልህ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ እንዲሁም ደንቡን ከማሻሻሉ በፊት በቀጥታ ለሊቀ ጳጳሱ ሪፖርት እንደሚያደርግ ተገልጿል።
“ካዛ ሶሊዬቮ ዴላ ሶፈሬዛ” (የእፎይታ ቤት) በመባል የሚታወቀው ፋውንዴሽን የተመሠረተው፥ በሕመም ለሚሰቃይ አካል እንክብካቤን ማድረግ የክርስቲያን ተልዕኮ ዋና አካል እንደሆነ በሚያምነው በቅዱስ አባ ፒዮ ተጨባጭ እምነት እንደ ነበር ታውቋል።
ከአሥርተ ዓመታት በኋላ ዛሬ ያ ግንዛቤ ሳይለወጥ የቀጠለ ሲሆን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በጽሑፋቸው ያጸደቁት የምክር ቤት ምሥረታ ውልም የእንክብካቤ ምልክት እንደሆነ ሲታወቅ፥ ቅዱስ አባ ፒዮ ማንም ሕመምተኛ፣ ነጋዲ ወይም የቤተሰብ አባል መልካም አቀባበል፣ ዕርዳታ እና እንክብካቤ እንዲደረግለት ይፈልግ እንደ ነበር ተገልጿል።
በጣሊያኗ ከተማ ሳን ጆቫኒ ሮቶንዶ የተቋቋመው የሕመም ስቃይ ማስወገጃ ማዕከል ሥራን እንደገና ማስጀመር ለመሥራቹ፣ ለተልዕኮው እና በየቀኑ በበሮቹ ለሚያልፉት ሁሉ የታማኝነት ተግባር ምሳሌ እንደሚሆን ተገልጿል።
