ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በጣሊያን ከጄኖቫ ሀገረ ስብከት ከመጡ አዳጊ ወጣቶች ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በጣሊያን ከጄኖቫ ሀገረ ስብከት ከመጡ አዳጊ ወጣቶች ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ   (@Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ “በምስጢረ ሜሮን የምንቀበለው የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ኢየሱስን ለመከተል ያግዘናል" ሲሉ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ምስጢረ ሜሮን የተቀበሉ በጣሊያን የጄኖቫ ሀገረ ስብከት አዳጊ ወጣቶችን በቫቲካን ተቀብለው መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው ለወጣቶቹ ባስተላለፉት መልዕክት፥ የምስጢረ ሜሮን ጸጋን ከተቀበሉ በኋላ ለኢየሱስ ክርስቶስ ያላቸውን ከፍተኛ ፍላጎት እና ቁርጠኝነት እንዲጠብቁ አበረታተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በሰሜን ጣሊያን ጄኖቫ ሀገረ ስብከት ምስጢረ ሜሮን ከተቀበሉ በኋላ መንፈሳዊ ንግደት በማድረግ ቅዳሜ ግንቦት 8/2018 ዓ. ም. ወደ ሮም ከመጡት አዳጊ ወጣቶች ጋር ተገናኝተው ባስተላለፉት የማበረታቻ መልዕክት፥ ለኢየሱስ ክርስቶስ ያላቸውን ከፍተኛ ፍላጎት እና ቁርጠኝነት እንዲጠብቁ አሳስበዋል።

አዳጊዎቹ ከዚህ በፊት የምስጢረ ሜሮን ጸጋን ለመቀበል ሲዘጋጁ የቆዩ ሲሆን ይህም የምስጢራትን መጀመርያ በማጥናቀቅ ምስጢረ ጥምቀትን የተቀበለ ሰው በመንፈስ ቅዱስ ስጦታ የሚሞላ እንደ ሆነ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለአዳጊ ወጣቶች ባደረጉት ንግግር፥ የምስጢረ ሜሮን ጸጋ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ በመሆኑ እያንዳንዱ ጳጳስ የተሰማውን ታላቅ ደስታ የሚገልጽበት ዕድል እንደሆንም አስረድተዋል።

“ምስጢረ ሜሮንን መቀበል እጅግ ያስደስታል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “ምክንያቱም የመንፈስ ቅዱስ ሙላት ጉጉት፣ ጥንካሬ እና ኢየሱስ ክርስቶስን መከተል ዘወትር ለእግዚአብሔር አዎ! እንድንል እና በድፍረት እርሱን ለመከተል፣ እምነትን በተግባር ለመኖር እና ከኢየሱስ ክርስቶስ ሊያርቀን በሚፈልግ ዓለም ውስጥ ጠንክረን የመኖርን ኃይልን ይሰጠናል” ብለዋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የሚቀጥለው እሁድ ማለትም አሑድ ግንቦት 24/2026 ዓ. ም. የጴራቅሊጦስ በዓል የሚከበርበት መሆኑን የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት የእግዚአብሔርን ፍቅር ማወጅ የጀመሩበትን ቤተ ክርስቲያን የምታስታውስበት ዕለት እንደሆነ አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ለአዳጊ ወጣቶች መልዕክት ሲያስተላልፉ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ለአዳጊ ወጣቶች መልዕክት ሲያስተላልፉ   (@Vatican Media)

ምስጢረ ሜሮንን የተቀበለ እያንዳንዱ የቤተ ክርስቲያን አባል በቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ እንዲሳተፍ የተጠራ እና በእኛ ውስጥ የሚኖረውን መንፈስ ቅዱስ ለጓደኞቹ እና ለቤተሰቦቹ እንዲመሰክር የሚላክ መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።

ምስጢረ ሜሮን ለጳጳሳት ታላቅ ደስታን የሚያጎናጽፍ እንደሆነ ገልጸው፥ ነገር ግን ብዙውን ጊዜ በርካታ ወጣቶች እንደገና ከቁስናቸው እየጠፉ ወደ ቤተ ክርስቲያን አለመመለሳቸው ሐዘንን እንደሚያመጣባቸው አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ስለዚህ ወጣት ካቶሊካውያን ለመንፈስ ቅዱስ የጽናት ስጦታ ልዩ ትኩረት በመስጠት እምነታቸውን በጋራ እንዲኖሩ ጥሪ አቅርበዋል።

“በዚህ ጊዜ ያገኛችሁትን እና ወደ ሮም በመምጣታችሁ የተሰማችሁትን ደስታችሁ በልባችሁ ይዛችሁ ሳትዘነጉ፥ የኢየሱስ ክርስቶስ ታማኝ ደቀ መዛሙርት ሆናችሁ በእምነት ጸንታችሁ ኑሩ” ሲሉ አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ምስጢረ ሜሮን ከተቀበለ በሩቅ ከሚገኝ አዳጊ ጋር በ "ሴልፊ"  ሲነጋገሩ፤
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ምስጢረ ሜሮን ከተቀበለ በሩቅ ከሚገኝ አዳጊ ጋር በ "ሴልፊ" ሲነጋገሩ፤   (@Vatican Media)

ወደ መጡባቸው ቁምስናዎች ሲመለሱም፣ በኅብረት እንዲኖሩ በሚያስችሏቸው በርካታ ተግባራት እና ዕድሎች ላይ እንዲሳተፉ ጋብዘዋቸዋል።

“እምነትን ብቻችንን ሳይሆን አብረን እንኖረዋለን” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ እነዚህ የወዳጅነት እና የማኅበረሰብ ግንኙነት መሠረቶች፥ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንደመሆናችን መጠን በእርሱ ጸንተን የምንኖርባቸው መንገዶች ናቸው” ሲሉ አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመጨረሻም፥ ምስጢረ ሜሮንን የተቀበሉ ከጄኖቫ ሀገረ ስብከት የመጡት አዳጊ ወጣቶች የመንፈስ ቅዱስ የጸጋ ሙላት በሕይወታቸው ሁሉ እንዲጠብቁት እና በዚህ ጊዜ እንዲደሰቱ አበረታተዋቸዋል።

“እያንዳንዳችሁ የእግዚአብሔር ወዳጆች፣ ደቀ መዛሙርቱ እና ሚስዮናውያኑ ሆናችሁ ለመቀጠል መፈለጋችሁ እና በእምነት ጸንታችሁ ለመኖር የገባላችሁት ቃል ኪዳን እጅግ አስፈላጊ ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል።

16 May 2026, 16:46