ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ “እመቤታችን ማርያም ቤተ ክርስቲያን የተጠራችበት ፍጹም አርአያ ናት” ሲሉ ገለጹ
ክቡራት እና ክቡራን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ያደረጉት ንግግር ሙሉ ትርጉም ከማቅረባችን በፊት ለዕለቱ የተመርጠውን የቅዱስ ወንጌል ክፍል እናነብላችኋለን፥
“በገቡም ጊዜ ወደሚኖሩበት ሰገነት ወጡ፥ ጴጥሮስና ዮሐንስም፥ ያዕቆብም፥ እንድርያስም፥ ፊልጶስም፥ ቶማስም፥ በርተሎሜዎስም፥ ማቴዎስም፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብም፥ ቀናተኛ የሚባለው ስምዖንም የያዕቆብ ልጅ ይሁዳም። እነዚህ ሁሉ ከሴቶችና ከኢየሱስ እናት ከማርያም ከወንድሞቹም ጋር በአንድ ልብ ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር” (ሐዋ. 1: 13-14)።
ክቡራት እና ክቡራን ከዚህ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዛሬው ዕለት ለምዕመናኑ ያቀረቡትን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትርጉም ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
"ውድ ወንድሞቼ እና እህቶች ሆይ! እንደምን አረፈዳችሁ! ዛሬ ግንቦት 5 የፋጢማ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መታሰቢያ ቀን ነው። በዚህ ቀን ከአርባ አምስት ዓመታት በፊት ሰዎች በተሰበሰቡት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ላይ የግድያ ሙከራ መደረጉ ይታወሳል። ይህም እመቤታች ቅድስት ድንግል ማርያም በብዙ መንገዶች እንዳረጋገጠችው ለሞት የሚያደርስ አልነበረም። ስለዚህ የዛሬውን አስተምህሮየን ‘ድንግል ማርያም የቤተ ክርስቲያን ሞዴል’ በሚል ጭብጥ፥ “ቶተስ ቱስ” ወይም “አንተ ሁሉ ነህ” የሚል መሪ ቃል ለያዘው የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ መታሰቢያነት ማድረግ እወዳለሁ።
ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ፥ ‘የአሕዛብ ብርሃን’ (Lumen gentium) በሚለው ሐዋርያዊ ደንብ መጨረሻ ምዕራፍ ከቁ. 52-69 ድረስ ቤተ ክርስቲያንን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መስጠት መርጧል። ‘ቤተ ክርስቲያን ቀዳሚ እና በእምነት እና በበጎ አድራጎት ውስጥ እጅግ በጣም ጥሩ ምሳሌ ተደርጋ ትወደሳለች’ (የአሕ. ብ. 53)። እነዚህ ቃላት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የእግዚአብሔር ልጅ ሥጋ ለብሶ እንዲወለድ ያደረገች እመቤታችን ማርያም የቤተ ክርስቲያን ሞዴል፣ ቀዳሚ አባልና እናት መሆኗን እንድንገነዘብ ይጋብዙናል።
ማርያም እራሷን በውስጧ ፍጻሜውን ባገኘችው በጸጋ ሥራ እንድትቀረጽ በመፍቀድ እና የልዑል እግዚአብሔር ስጦታን በእምነት እና በድንግልና ፍቅሯ በመቀበል ቤተ ክርስቲያን የተጠራችበት ፍጹም ሞዴል ናት። የእግዚአብሔር ቃል እና የልጆቹ እናት ቅድስት ድንግል ማርያም በመንፈስ ቅዱስ ተግባር በትሕትና የተወለደች፣ ከዚህም በላይ በእምነትም የላቀ ብቃት ያላት፣ በእግዚአብሔር ቅዱሳን ሕዝቦች ኅብረት ውስጥ ለመለኮታዊ ምስጢር ቅድመ ሁኔታ በሌለው ግልጽነት የተሰጠንባት፣ የቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰብ እጅግ በጣም ጥሩ አባል ነች። በመጨረሻም በእግዚአብሔር ወልድ ውስጥ ልጆችን ስለወለደች፣ በመካከላችን በመጣው ዘላለማዊ ፍቅር የተወደደችው፣ የመላው ቤተ ክርስቲያን እናት ናት። ይህም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በራስ መተማመን፣ በመደመጥ፣ በመጠበቅ እና በመወደድ እርግጠኛነት ወደ እርሷ ሊመለስ ይችላል።
እነዚህ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባህሪያት እንደ ምስጢራዊ ምልክት አድርጓት ሊገልጽ ይችላል። ሴት የሚለው ቃል የመሲሑ እናት የመሆን ያልተለመደ ተሞክሮ እንዲኖራት የተሰጣት የእስራኤል ወጣት ልጅ ታሪካዊ እውነታን ያጎላል። ሞዴል የሚለው አገላለጽ በእርሷ ላይ የመውረድ እና ከእርሷ ውስጥ ወጥቶ የማረግ ሁለትዮሽ እንቅስቃሴ እንደሚፈጸም አፅንዖት ይሰጣል። እግዚአብሔር በእርሷ ውስጥ እና በእርሱ ላይ ያለውን ነጻ የእምነት ፈቃድ ይገልጻል። ስለዚህ እመቤታችን ማርያም የምስጢሩ ሞዴል እና የመለኮታዊ መዳን እቅድ የሆነችው በአንድ ወቅት ተደብቃ የቆየች እና አሁን በኢየሱስ ክርስቶስ ሙሉነት የተገለጠች በመሆኗ ነው።
ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ በቤዛነት ሥራ ውስጥ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስለያዘችው ልዩ ቦታ ግልጽ ትምህርት ሰጥቶናል (የአሕ. ብ. 60-62)። የመዳን ብቸኛው እና መካከለኛ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ያስታውሳል (1ኛ ጢሞቴዎስ 2:5-6)። ‘የኢየሱስ ክርስቶስ እናት ቅድስት ድንግል ማርያም በምንም መንገድ ይህን ሳታደናቅፍ ይልቁንም ምዕመናን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያላቸውን ቀጥተኛ አንድነት ታበረታታለች (የአሕ. ብ. 60)። እንዲሁም ከዘመናት ጀምሮ አስቀድሞ የተወሰነው በመለኮታዊ የአመራር ደንብ ሲሆን፥ ይህም የቃሉ ሥጋዌ የእግዚአብሔር እናት፣ የተባረከች ድንግል እንድትሆን ወስኗል። በዚህ ልዩ መንገድ በአዳኝ ሥራ ውስጥ በታዛዥነት፣ በእምነት፣ በተስፋ እና በሚያቃጥል ፍቅሯ ተባብራ ለነፍሳት በሙሉ ከተፈጥሮ በላይ የሆነ ሕይወት በመስጠት በጸጋ ቅደም ተከተል እናታችን ነች’ (የአሕ. ብ. 61)።
የቤተ ክርስቲያን ምስጢር በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ውስጥ ተንፀባርቋል። በእርሷ ውስጥ የእግዚአብሔር ሕዝብ የመነሻቸውን፣ የሞዴላቸውን እና የትውልድ አገራቸውን ውክልና ያገኛሉ። በኢየሱስ ክርስቶስ እናት ውስጥ ቤተ ክርስቲያን የራሷን ምስጢር ታስባለች። በእርሷ ውስጥ ድንግላዊ እምነት፣ እናታዊ ቸርነት እና የተጠራችበትን የጋብቻ ቃል ኪዳን ሞዴል ስለምታገኝ ብቻ ሳይሆን ከሁሉም በላይ በእርሷ ውስጥ የራሷን አርኪነት እና የተጠራችበትን ፍጹም አምሳያነት ስለምታውቅ ነው።
እንደምናየው በ ‘አሕዛብ ብርሃን’ ሐዋርያዊ ደንብ ውስጥ የተሰበሰቡት የእመቤታችን ማርያም ነጸብራቆች ቤተ ክርስቲያንን እንድንወድ እና በውስጧ የእግዚአብሔርን መንግሥት ፍጻሜ እንድናገለግል ያስተምሩናል። ይህም የሚመጣውን እና ሙሉ በሙሉ በክብር የሚፈጸመውን የእግዚአብሔር መንግሥት ፍጻሜ እንድናገለግል ያደርገናል።
እንግዲህ ድንግል እና እናት በሆነች በእመቤታችን ማርያም የተሰጠን እጅግ የላቀ ሞዴል ምን እንደሆነ እራሳችንን እንጠይቅ። በአማላጅነቷ በኩል ከእኛ የሚጠየቀውን ምላሽ መስጠት እንድንችል እንጠይቃት። የቤተ ክርስቲያንን ተሳትፎ በትህትና እና በእምነት እኖራለሁ? በእርሷ ውስጥ እግዚአብሔር ለዘለዓለም ፍቅሩ ምላሽ እንድሰጥ የሰጠኝን የቃል ኪዳን ማኅበረሰብ እገነዘባለሁን? እግዚአብሔር ለሰጠን ሐዋርያዊ አባቶች በመታዘዝ የቤተ ክርስቲያን ሕያው አካል እንደሆንኩ ይሰማኛል? ማርያምን እንደ ሞዴል፣ እንደ ድንቅ አባል እና የቤተ ክርስቲያን እናት አድርጌ እመለከታታለሁ? የልጇ ታማኝ ደቀ መዝሙር ለመሆን እርዳታዋን እጠይቃታለሁ?
እህቶቼ እና ወንድሞቼ! በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ላይ የወረደው እና በእኛ በኩል በትህትና እና በአደራ የተጠየውቀው መንፈስ ቅዱስ እነዚህን አስደናቂ እውነታዎች ሙሉ በሙሉ ለመኖር የሚያስችል ጸጋ ይስጠን። በሐዋርያዊ ደንብ ላይ በጥልቀት ካሰላሰልን በኋላ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ይህንን ስጦታ ለእኛ እንድታገኝልን እንለምን። የቅድስት እናት ቤተ ክርስቲያን ፍቅር በሁላችን ውስጥ ይደግ። አሜን!” በማለት ሳምንታዊ አስተምህሮአቸውን ደምድመዋል።
