“የሰው ልጅ አስደናቂነት” የተሰኘ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ  ሐዋርያዊ መልዕክት “የሰው ልጅ አስደናቂነት” የተሰኘ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሐዋርያዊ መልዕክት   (AFP or licensors)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “የሰው ልጅ ታላቅነት” የተሰኘ ሐዋርያዊ መልዕክት ይፋ አደረጉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ “የሰው ልጅ ታላቅነት” (Magnifica humanitas) በሚል ርዕሥ የጻፉት የመጀመሪያው ሐዋርያዊ መልዕክት ሰኞ ግንቦት 17/2018 ዓ. ም. ይፋ ሆኗል። ሐዋርያዊ መልዕክታቸው የሰው ሠራሽ አስተውሎት በሰው ልጅ ላይ ጉዳት እንዳያስከትል ከማሳሰቡ በተጨማሪ፥ የሰው ሠራሽ አስተውሎት በሰዎች ላይ ለሚፈጥረው የበላይነት፣ የማግለል እና የጦርነት ተግዳሮቶች ቤተ ክርስቲያን የምትሰጠው ምላሽ የሚገኝበት እንደሆነ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 13ኛ ይፋ ካደረጉት “አዳዲስ ነገሮች” (Rerum novarum) ከተሰኘ ሐዋርያዊ መልዕክት ጋር ተመሳሳይነት ያለው የቅዱስነታቸው መልዕክት፥ የበላይነትን፣ ማግለልን እና ጦርነትን ከሚያበረታቱ ቴክኖሎጂዎች በተቃራኒ፥ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ለሰው ልጅ አገልግሎት እንዲውል ጥሪ አቅርበው፥ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የቴክኖሎጂ ዕድገትን ለሰው ልጅ ጥቅም ሊያውለው እንደሚገባ አሳስበዋል።  

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ቫቲካን ውስጥ በሚገኘው የጠቅላይ ሲኖዶስ አዳራሽ ውስጥ ሰኞ ግንቦት 17/2018 ዓ. ም. ለተገኙት እንግዶች ባደረጉት ንግግር፥ “በኢንዱስትሪ አብዮት ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 13ኛ ከተጋፈጡት ትግዳሮት ጋር በሚመሳሰል የዘመን ለውጥ ላይ እንገኛለን” ሲሉ ተናግረዋል።

“ሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) በሕይወታችን ውስጥ ብዙ ቦታዎችን በመንካት የሰው ልጅ አብሮ የመኖር ውሳኔዎችን የሚቀርጽ እንዲሁም ጦርነት የሚካሄድበትን መንገድ ጭምር በከፍተኛ ሁኔታ እየለወጠው ይገኛል” ሲሉ ተናግረዋል።

“አዳዲስ ነገሮች” የሚታዩበት አዲስ ወቅት

“የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 13ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1891 ዓ. ም. ይፋ ካደረጉት ‘አዳዲስ ነገሮች’ (Rerum novarum) ከተሰኘ ሐዋርያዊ መልዕክት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው” ባሉት መልዕክታቸው፥ “የዛሬዋ ቤተ ክርስቲያንም እንዲሁ የወንጌልን ብርሃን እና የሰው ልጅ ክብርን መሠረት በማድረግ የዘመኑን አዳዲስ ክስተቶችን ለመተርጎም ተጠርታለች” ብለዋል።

“የሰው ልጅ ታላቅነት” የተሰኘው የመጀመሪያው ሐዋርያዊ መልዕክታቸው ለወጣት ትውልድ የወደፊት ሕይወት የሚጨነቁ የሳይንስ ጠበብትን፣ መሐንዲሶችን፣ አስተማሪዎችን፣ የፖለቲካ መሪዎችን እና ቤተሰቦችን በሚገባ በማዳመጥ የጻፉት መሆኑን ቅዱስነታቸው አብራርተዋል። በተመሳሳይም በራስ ገዝ የጦር መሣሪያ ሥርዓቶች፣ ኢ-ፍትሃዊ እና ጭፍን ጥላቻ ባላቸው መረጃዎች ላይ በመመሥረት በጤና አጠባበቅ፣ በሥራ ዕድል ወይም የሰው ልጅ ደህንነትን ያስጠብቃሉ በሚባሉ ስልተ ቀመሮችን ላይ እጅግ የሚያስደነግጡ አስተያየቶችን መቀበላቸውን ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ላይ በጥልቀት ካሰላሰሉ በኋላ ይፋ ባደረጉት የመጀመሪያ ሐዋርያዊ መልዕክታቸው፥ ቴክኖሎጂ ለሰው ልጆች ብልጽግና፣ አብሮነት እና መደጋገፍ የበኩሉን አስተዋጽዖ ማበርከት እንደሚገባ አሳስበው፥ ከጊዜው አሳሳቢ ሁኔታ አኳያ ህሊናን የሚያነቁ እና የሰው ልጅ ወደፊት የሚጓዝባቸውን መንገዶች የሚጠቁሙ ቃላት እንደሚያስፈልጉ ተናግረዋል።

“የሰው ልጅ አስደናቂነት” የተሰኘ የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ መልዕክት ይፋ የሆነበት ዝግጅት
“የሰው ልጅ አስደናቂነት” የተሰኘ የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ መልዕክት ይፋ የሆነበት ዝግጅት   (@Vatican Media)

ቴክኖሎጂ እና የሞራል ኃላፊነት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ቤተ ክርስቲያኗ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ትጥቅ እንዲፈታ ያደረገችውን የረጅም ጊዜ ድጋፍ በማስታወስ፥ እያንዳንዱ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ አቅም ከሥነ-ምግባራዊ ማስተዋል እና ከሕዝብ ተጠያቂነት ጋር መያያዝ እንዳለበት አሳስበዋል።

“ሰው ሠራሽ አስተውሎትም በተመሳሳይ መልኩ፥ ከበላይነት፣ ከማግለል ወይም ሞትን ከሚያስከትል የጦር መሣሪያ አመክንዮዎች ነፃ መሆን አለበት” ብለው፥ ሐዋርያው ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ሰዎች በጻፈው የመጀመሪያ መልዕክቱ ምዕ. 5:6 ላይ፥ “ነቅታችሁ ጠብቁ” ያለውን ምክር በመጥቀስ፥ ቴክኖሎጂ የሰውን ልጅ ወሳኝ የሞራል ንቃት እና ስሜት በሚያዳክምበት ወቅት ሰላም ራሱ አደጋ ላይ እንደሚወድቅ አስጠንቅቀው፥ የሰው ልጅ ተግባር አደገኛ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን መገደብ ብቻ ሳይሆን የበለጠ ፍትሃዊ የወደፊት ሕይወትን በጋራ መገንባት እንደሆነ አፅንዖት ሰጥተዋል።

“ማንም ሰው ብቻውን ሊገነባ አይችልም”

በፔሩ በሚስዮናዊነት ባሳለፏቸው ዓመታት ውስጥ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2017 ዓ. ም. የጣለው ከባድ ዝናብ እና ጎርፍ ከፍተኛ ውድመትን ማስከተሉን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ መልሶ ግንባታ አገልግሎት ሰጭ መዋቅሮችን ከማደስ የሚበልጡ ነገሮችን እንደሚያካትት መማራቸውን፥ እነዚህም አብሮነትን መጠገን፣ መተማመንን ወደ ነበረበት መመለስ እና የወደፊት ተስፋን እንደገና ማንሰራራት እንደሆኑ በመግለጽ፥ “ማንም ሰው ይህን ብቻውን መገንባት አይችልም” ሲሉ አስረድተዋል።

በኦሪት ኪዳን የኢየሩሳሌም ግድግዳዎች እንደገና መገንባታቸውን የሚገልጽ መጽሐፈ ነህምያን የጠቀሱት ቅዱስነታቸው፥ ምስሉን ለዲጂታል ዘመን ሥነ-ምግባራዊ ግንባታ እንደ ሞዴል በማቅረብ፥ የሰው ሠራሽ አስተውሎት በኅብረት መካከል ታሪክ የሚገነባበት ቦታ ሊሆን እንደሚችል እና በዚህም ውስጥ የቴክኖሎጂ ዕድገት የሰውን ሕይወት ማገልገልን እንደሚማር አስረድተዋል።

የሰው ልጅ ማዕከላዊነት

“እውነተኛ ልማት እያንዳንዱን ሰው እና መላውን ኅብረተሰብ ያማከለ ነው” የሚለውን የቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ አስተምህሮን በመጥቀስ፥ ማንም ሰው ከዲጂታል ለውጥ መገለል እንደሌለበት እና በፍፁም ወደ ምርት፣ የእውቀት አፈፃፀም ወይም መረጃነት ደረጃ ሊወርድ እንደማይችል አጥብቀው ተናግረዋል።

“አንደ ሰው በውስጡ ወይም በውስጧ የትኛውም ማሽን ሊተካው ወይም ሊያግደው የማይችለውን ነፃነት፣ ውስጣዊ ማንነት፣ ፍቅር እና የአምልኮ ጥሪ የያዘ ነው” ሲሉ የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በሰው ሠራሽ አስተውሎት አማካይነት የሚመጣ ዕድገት ለጥቂት ሰዎች ብቻ ከመሆን ይልቅ መላውን የሰው ልጅ ቤተሰብ የሚጠቅም መሆኑን ለማረጋገጥ በአገሮች፣ በተቋማት፣ በቴክኖሎጂ ገንቢዎች፣ በቴክኖሎጂ ሥርዓቶች እና እጅግ በተጎዱ አገራት መካከል ትብብር ሊኖር እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

በዝግጅቱ ላይ የተገኙት የሐዋርያዊ መልዕክቱን ጥራዝ ሲቀበሉ
በዝግጅቱ ላይ የተገኙት የሐዋርያዊ መልዕክቱን ጥራዝ ሲቀበሉ   (@Vatican Media)

“የፍቅር ስልጣኔ”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የሰው ሠራሽ አስተውሎትን አስመልክተው ለሚደረጉ ዓለም አቀፍ ውይይቶች ትሕትና እና ግልጽነት ያለበት አስተዋጽኦ ለማበርከት ያላትን ፍላጎት አረጋግጠው፥ ይህም ቴክኒካዊ እውቀትን በማካፈል ሳይሆን፥ ለእግዚአብሔር ባለው ግልጽነት ላይ የተመሠረተ የሰው ልጅ ክብር እና ህሊና በመጠበቅ እንደሆነ አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ሰዎች በሙሉ ተስፋን እንዲያሳድጉ በመጋበዝ፥ አማኞችም ሆኑ የማያምኑት የበለጠ ሰብዓዊ እና ወንድማዊ ማኅበረሰብን እንዲፈጥሩ በማሳሰብ፥ የእግዚአብሔርን ታላቅነት በሚገልጽ ትኅትናዋ፥ ተነሳሽነቱን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በመስጠት፥ “የቀድሞው ርዕሣነ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ እና ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ተስፋ ያደረጉት የፍቅር ስልጣኔ በታሪክ ውስጥ ማደጉን እንዲቀጥል” በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

 

26 May 2026, 12:49