ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ “ስለ ሰላም መጨነቅ ማለት ሕይወትን መንከባከብ ማለት ነው” ሲሉ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ቤተ ክርስቲያን “ውዳሴ ላንተ ይሁን!” ሳምንትን በምታከብርበት ወቅት፥ ሰላም በሁሉም ሰው ልብ ውስጥ እንዲሰፍን ጸሎት አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እሑድ ግንቦት 9/2018 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር ሆነው “የእመቤታችን ማርያም የሰማይ ንግሥት” ጸሎት ባደረሱበት ወቅት፥ “የውዳሴ ላንተ ይሁን!” ሳምንት ከግንቦት 9-16/2018 ዓ. ም. ድረስ የሚከበር መሆኑን አስታውሰዋል።

ዓመታዊ ዝግጅቱ ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ሁሉም ሰው ከተስፋ ወደ ተግባር እንዲሸጋገር የጋበዙትን እና የጋራ መኖሪያ ምድራችንን ስለ መንከባከብ ያስተላለፉትን ሐዋርያዊ መልዕክት መታሰቢያን ለማክበር እንደሆነ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሳምንቱን በማስታወስ ባስተላለፉት መልዕክት፥ የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን!” እንቅስቃሴ አባላት እና ለተቀናጀ ሥነ-ምህዳር የሚሠሩት በሙሉ ቁርጠኝነታቸውን እንዲያድሱ አሳስበዋል።

የአሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮስ ለፍጥረት ያለውን ፍቅር በማስታወስ የሰላም መልዕክቱን የጠቀሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ቤተ ክርስቲያን የቅዱሱን ዕረፍት 800ኛ ዓመት በማክበር ላይ እንደምትገኝ ተናግረዋል።

“በዚህ የአሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮስ የኢዮቤልዩ ዓመት፥ ከእግዚአብሔር ጋር፣ ከወንድሞቻችን እና ከእህቶቻችን ጋር እንዲሁም ከፍጥረታት ሁሉ ጋር ሰላም እንዲኖረን በማለት ያስተላለፈውን መልዕክት እናስታውስ” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በቅርብ ዓመታት ውስጥ በልዩ ልዩ ቦታዎች የሚከሰጡ ጦርነቶች ለፍጥረታት በሚደረገው እንክብካቤ ላይ እንቅፋት መሆናቸውን በሐዘን ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመጨረሻም፥ ለሰላም በሚደረግ እንክብካቤ እና ለሕይወት በሚደረግ እንክብካቤ መካከል ያለውን ትስስር ጠቁመዋል።

“‘የውዳሴ ላንተ ይሁን!’ እንቅስቃሴ አባላት እና ለተቀናጀ ሥነ-ምህዳር የሚሠሩት በሙሉ ቁርጠኝነታቸውን እንዲያድሱ አበረታታለሁ” ብለው፥ “ሰላምን መንከባከብ ማለት ሕይወትን መንከባከብ ማለት ነው” በማለት መልዕክታቸውን ደምድመዋል።

 

18 May 2026, 16:19