ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ቫቲካን ውስጥ በሚገኘው የሉርድ እመቤታችን ማርያም ምስል ፊት ጸሎት በማድረስ ላይ፤ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ቫቲካን ውስጥ በሚገኘው የሉርድ እመቤታችን ማርያም ምስል ፊት ጸሎት በማድረስ ላይ፤   (@Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ ስለ ሰላም የሚቀርብ ዓለም አቀፍ የመቁጠሪያ ጸሎት እንደሚመሩ ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ጦርነት እንዲቆም ዘወትር ከሚያቀርቡት ተከታታይ ጥሪ ጎን ለጎን፥ ግንቦት 22/2018 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ ስለ ሰላም የሚቀርብ ዓለም አቀፍ የመቁጠሪያ ጸሎት እንደሚመሩ ተገልጿል። የመቁጠሪያ ጸሎቱ በየአሥርት ዓመታት ውስጥ በጦርነት ምክንያት የሞት፣ የመቁሰል እና የመበታተን አደጋ የደረሰባቸውን ቤተሰቦችን ጨምሮ የሕክምና ባለሙያዎች እና በጎ ፈቃደኞችን ለማስታወስ እንደሆነ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ መንበር ከተመረጡበት ጊዜ ጀምሮ በዓለም ሰላም ይሰፍን ዘንድ ምዕመናን በጸሎት እንዲተባበሯቸው ተከታታይ ጥሪዎችን በማቅረብ ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል።

በዚህ መሠረት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ቅዳሜ ግንቦት 22/2018 ዓ. ም. ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ በቫቲካን የአትክልት ሥፍራ በሚገኘው የሉርድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሐውልት ፊት የተዘጋጀውን የመቁጠሪያ ጸሎት የሚመሩ ሲሆን፥ በጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ምዕመናን እና ታዋቂ የእመቤታችን ማርያም ቤተ መቅደሶች ቅዱስነታቸውን በጸሎት እንዲተባበሯቸው ተጋብዘዋል።

በዚህ ጸሎት ላይ የሚሳተፉ ታዋቂ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደሶች፥ በዩክሬን (ዛርቫኒትሲያ) የሚገኝ የእግዚአብሔር እናት ቤተ መቅደስ፣ በፊሊፒንስ (አንቲፖሎ) የሚገኝ የሰላም እና የመልካም ጉዞ እመቤታችን ዓለም አቀፍ ቤተ መቅደስ፣ በፖርቱጋል (ፋጢማ) የሚገኝ የመቁጠሪያ እመቤታችን ማርያም ቤተ መቅደስ፣ በቦስኒያ ሄርዞጎቪና (ሜጁጎሪ) የሚገኝ የሰላም ንግሥት እመቤታችን ማርያም ቤተ መቅደስ፣ በፈረንሳይ (ሉርድ) የሚገኝ የእመቤታችን ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ፣ በሊባኖስ (ቢብሎስ) የሚገኝ የቅዱስ ቻርቤል አናያ ቤተ መቅደስ እና በጣሊያን (ሎሬቶ) የሚገኝ የእመቤታችን ማርያም ጳጳሳዊ ቤተ መቅደሶች እንደሆኑ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሚመሩት የመቁጠሪያ ጸሎት ላይ የደስታ ምስጢራትን በመጥቀስ፥ ባለፉት አሥርት ዓመታት ውስጥ በጦርነት እና በዓመፅ የተጎዱትን በልዩ ሁኔታ የሚያስታውሷቸው ሲሆን፥ በጦርነት የተጎዱትን በሙሉ የሰላም ንግሥት ለሆነች እመቤታችን ቅድስት ማርያም አደራ በመስጠት አማላጅነቷን ይለምናሉ።

በመጀመሪያው ምስጢር የጦርነት ሰለባዎችን በተለይም ለአደጋው የተጋለጡትን፣ በሁለተኛው ምስጢር በጦርነት ለተጎዱ ሕዝቦች የተስፋ ቃል እና የእምነት ጽናት የሚሰብኩትን፣ በሦስተኛው ምስጢር ሰብዓዊ ዕርዳታን በየቀኑ የሚያቀርቡትን የሕክምና ባለሙያዎችን እና በጎ ፈቃደኞችን ያስታውሳል።

በአራተኛው ምስጢር ጦርነት በሚቀሰቅሰው ዓመፅ ለሚሰቃዩት፣ ለታሰሩት እና ሰብዓዊ ክብራቸው ተጥሶ ለውርደት የተዳረጉትን ያስታውሳሉ። በአምስተኛው እና የመጨረሻው የደስታ ምስጢር ጦርነት እንዲያበቃ እና በዓለም ላይ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ይጸልያሉ።

የሮም ከተማ ምዕመናን እና በሮም በመንፈሳዊ ንግደት ላይ የሚገኙ የልዩ ልዩ አገራት ምዕመናን በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በተገጠሙት ትላልቅ ስክሪኖች በኩል ጸሎቱን መሳተፍ እንደሚችሉ የተነገረ ሲሆን፥ይህን ዝግጅት ያስተባበረው በዓለም ዙሪያ ወንጌልን የማዳረስ ተልዕኮ ያለው፥ በቅድስት መንበር የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት እንደሆነ ታውቋል።

 

29 May 2026, 09:45