ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን በሚችሉት ሁሉ የሚደግፉትን አመሰገኑ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የቅዱሳን ጴጥሮስ እና ጳውሎስ ዓመታዊ በዓል በተከበረበት ሰኞ ሰኔ 22/2018 ዓ. ም. በጣሊያን መዲና ሮም ለሚኖሩት ሰዎች በሙሉ ሰላምታቸውን አቅርበው፥ በዓለም ዙሪያ በቅዱስ ጴጥሮስ የዕርዳታ ማሰባሰብ መርሃ ግብር ላይ የተሳተፉትን በሙሉ አመስግነዋል።
“ዛሬ የቅዱስ ጴጥሮስ የዕርዳታ ማሰባሰቢያ ቀንን እናከብራለን” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ በመሆን የማበረክተውን አገልግሎት በበጎነት የሚደግፉትን በሙሉ ከልብ አመሰግናለሁ፣ በእምነት እና በኅብረት አብረን የምናደርገውን ጉዞ እንቀጥል” ሲሉ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ባቀረቡበት ወቅት ተናግረዋል።
በየዓመቱ የሚከናወነው ዕርዳታ የማሰባሰብ መርሃ ግብሩ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የበጎ አድራጎት ሥራዎችን ለመደገፍ፣ የአደጋ ጊዜ ዕርዳታን ለማቅረብ እና በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ተጋላጭ ማኅበረሰቦችን ለመደገፍ የሚያስችል እንደሆነ ታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የሮም ከተማ ባልደረባዎች የቅዱሳን ጴጥሮስ እና ጳውሎስ ዓመታዊ በዓል ዕለት በከተማው ለሚኖሩት በሙሉ ሰላምታቸው አቅርበው፥ በተለይም በሕመም እና በብቸኝነት የሚሰቃዩትን እንዲሁም በማረሚያ ቤቶች ውስጥ የሚገኙትን በጸሎት እንደሚያስታውሷቸው ተናግረዋል።
ቅዱስነታቸው በሮም ቁምስናዎች አገልግሎታቸውን በማበርከት ላይ የሚገኙ ካኅናትን፣ ገዳማውያን እና ገዳማውያትን በሙሉ አመሰግነው፥ አለኝነታቸውን በመግለጽ በዕለት ተዕለት አገልግሎታቸው ታላቁን የክርስቲያን ልብ ሕያው እንደሚያደርጉ ገልጸው፥ ይህን አገልግሎት በማስመልከት ሎዘርቫቶሬ ለተሰኘ የቅድስት መንበር ጋዜጣ ጽሑፍ የሚያበረክቱትን አመስግነዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ “‘ከሎሴቫቶሬ ሮማኖ’ ከተሰኘ ዕለታዊ የቅድስት መንበር ጋዜጣ በተጨማሪ ‘ሎሴቫቶሬ ዲ ስትራዳ’ የተሰኘ ጋዜጣን በማከፋፈል የሚተባበሩ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ዙሪያ ለሚኖሩ ቤት አልባ ሰዎች ሰላምታቸውን አቅርበው፥ ጋዜጣው ለዋናው የቫቲካን ጋዜጣ ማሟያ በመሆን በኅብረተሰቡ የተገለሉ እና ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች ታሪኮችን፣ ሃሳቦችን እና አስተያየቶችን በየወሩ የሚያካፍል እንደሆነ ታውቋል።
ሮም የባልደረባዎቿን በዓል ታከብራለች
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በተጨማሪም የቅዱሳን ጴጥሮስ እና ጳውሎስ ዓመታዊ ክብረ በዓል በማስመልከት በከተማው የሚቀርቡ ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን በማስታወስ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በዝግጅቶቹ ላይ ከመላው የጣሊያን ከተሞች የመጡትን እና ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን የሚደግፉ ድርጅቶች ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ የሚወስደውን ረጅሙን መንገድ በሚያማምሩ አበቦች ያስጌጡ በጎ ፈቃደኞችን አመስግነዋል።
በጎ ፈቃደኞቹ በየዓመቱ ሰኔ 29 የአበባ ቅጠሎችን በመጠቀም ውስብስብ የሆኑ ንድፎችን እና ምስሎችን ለዕይታ የሚያቀርቡ ሲሆን፥ ዘንድሮ ለ13ኛ ጊዜ የቀረበው ንድፍ “ኢንፊዮራታ” ወይም “በአበቦች ያጌጠች” የሚል እንደ ነበር ተመልክቷል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በተጨማሪም፥ “የቅዱስ አንጀሎ ቤተ መንግሥት እሽክርክሪት” የተባለውን ዓመታዊ የርችት ዝግጅት በማቅረብ የተባበሩትን አመስግነው፥ ዓመቱ ቅዱስ ፍራንችስኮስ ፍጥረታትን በማስመልከት ያዘጋጀውን የምስጋና መዝሙር የሚያስታውስ እንደሆነም ተገልጿል።
