ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ ቤተ ክርስቲያን በዓለም የተልዕኮ እሑድ እንድትሳተፍ ግብዣ አቀረቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“እያንዳንዱ ካቶሊካዊ ማኅበረሰብ በዓለም የተልዕኮ እሑድ በመሳተፍ ለመጀመሪያው የስብከት የወንጌል አገልግሎት እና ለወጣት ቤተ ክርስቲያናት በሚደረጉ የሚስዮናዊነት ጥረቶች ጸሎት በማቅረብ መንፈሳዊ እና ቁሳዊ መስዋዕቶችን እንዲያቀርብ ተጋብዟል” ሲሉ፥ ሰኞ ግንቦት 24/2018 ዓ. ም. በቫቲካን በተካሄደው ጳጳሳዊ የተልዕኮ ማኅበራት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለተሳተፉት ሰላምታ ባቀረቡበት ወቅት ገልጸዋል።
የማኅበራቱን የቆየ ታሪክ በመቃኘት ለብዙ አሥርት ዓመታት ለቤተ ክርስቲያን እና ለመላው ዓለም ያበረከቱትን አስተዋጽኦ በማስታወስ ንግግራቸውን የጀመሩት ቅዱስነታቸው፥ በያዝነው የጎርጎሮሳውያኑ 2026 ዓ. ም. ማኅበራቱ በርካታ የሚስዮናዊነት በዓላትን የሚያከብሩ መሆኑን አስታውሰው፣ በተለይም የተቋቋመበትን የመቶኛ ዓመት ክብረ በዓል፣ በቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 11ኛ ጥያቄ መሠረት የጥቅምት ወር የዓለም የተልዕኮ እሁድ የሚከበት መሆኑን አስታውቀዋል።
“ይህ ዕለት ላለፉት መቶ ዓመታት ለጸሎት፣ ለአስተንትኖ እና ለቤተ ክርስቲያን የወንጌል ተልዕኮ አገልግሎት አስተዋጽኦን ለማበርከት የተወሰነ፥ በተለይም የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ገና እየተጀመረ ያባሉባቸው ወጣት ቤተ ክርስቲያናት የሚታወስበት ዕለት መሆኑን ቅዱስነታቸው አስገንዝበዋል።
“ከዓለም የተልዕኮ እሑድ አገልግሎቶች መካከል አንዱ በጥንታዊ ቤተ ክርስቲያናት ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ማስታወስ ነው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ አዲስ በተቋቋሙ ቤተ ክርስቲያናት ውስጥ ያሉትም ቢሆን በመላው ቤተ ክርስቲያን የሚስዮናዊነት መንፈስ ውስጥ መሳተፋቸው እጅግ አስፈላጊ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
ልግስና በዓለም ተልዕኮ እሁድ ላይ ያለው ተጽእኖ
በዓለም የተልዕኮ እሑድ በሚሰበሰበው የገንዘብ ድጋፍ፥ በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አማካይነት የመጀመሪያው የወንጌል አገልግሎት ለሚሰጥባቸው እና ከ1,130 በላይ ለሚሆኑ አዳዲስ ቤተ ክርስቲያናት ምሥረታ አስፈላጊ ዕርዳታ ማድረግ እንደሚቻል ገልጸው፥ ይህም የቤተ ክርስቲያን መሠረተ ልማቶችን ለማቋቋም እና ልዩ ልዩ ሚስዮናዊ ተነሳሽነቶችን ለመደገፍ እንደሚረዳ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ገንዘቡ በሮም ውስጥ በቀጣይነት ካኅናትን እያዘጋጁ የሚገኙ አምስት ኮሌጆችን እና ለትምህርት ወደ ሮም የሚመጡን እና ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ ለሚመለሱባቸው የአገራቱ ቤተ ክርስቲያናት ውድ ሃብቶች የሆኑ ካህናትን፣ ገዳማውያንን እና ገዳማውያትን የሚደግፍ መሆኑን አስታውሰዋል።
“በክርስቶስ አንድ በመሆን በተልዕኮ መተባበር”
“በክርስቶስ አንድ በመሆን በተልዕኮ መተባበር” የሚለውን የዘንድሮው የዓለም የተልዕኮ እሑድ ጭብጥ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የምዕመናንን አንድነት የሚያጎላ እና የዚህን ዓለም አቀፍ ክብረ በዓል 100ኛ ዓመት የሚገልጽ መሆኑን አስታውሰዋል።
“ጭብጡ ሁሉም የቤተ ክርስቲያን አባላት በኢየሱስ ክርስቶስ ጠንካራ ኅብረት እንዲኖራቸው እና በመለኮታዊ የፍቅር ተልዕኮው ውስጥ ወደ ሙሉ አንድነት እንዲመጡ የሚጋብዝ እና ኢየሱስ ክርስቶስ ከህማማቱ በፊት ወደ አባቱ ዘንድ ባቀረበው ጸሎቱ ውስጥ የገለጸውን ጥልቅ ፍላጎት የሚያንፀባርቅ ነው” ብለዋል።
በዚህ ዓመት ጭብጥ ውስጥ የተገለጹትን ሃሳቦች የጠቀሱት ቅዱስነታቸው፥ በሚመጡት ዓመታት ውስጥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚስዮናዊነት ተሃድሶ ጥሪ መኖሩን በአእምሯቸው እንዲይዙ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያተኮረ ሚስዮናዊ አንድነት እና ኅብረት እውነተኛ መንፈሳዊነት እንዲኖር እና በምዕመናን መካከል የሚያደርጉ እንቅስቃሴዎችን እንዲያስተዋውቁ አበረታትተዋል።
የተከበረ ፉልተን ሺን የተስፋ፣ የእምነት እና የፍቅር ብርሃን ነበር
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በተጨማሪም፥ በሰሜን አሜሪካ የጳጳሳዊ ተልዕኮ ማኅበራት ታዋቂ ዳይሬክተር የነበሩት ሊቀ ጳጳስ ፋልተን ጄ. ሺን በመስከረም 14/2019 ዓ. ም. በሚዙሪ ግዛት ሴንት ሉዊስ ብጽዕናው የሚታወጅ መሆኑን ተናግረው፥ ሊቀ ጳጳስ ሺን ለአሥርተ ዓመታት በሬዲዮ እና በቴሌቪዥን ሚዲያዎች የሰጡት የወንጌል አገልግሎት የእምነት፣ የተስፋ እና የፍቅር ብርሃን እንደ ነበር አስታውሰው፥ ለአገልግሎታቸውም ምስክር እንደሆኑ ተናግረዋል።
ለቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ እጅግ ጠቃሚ አገልግሎት
ማኅበራቱ በአገራት እና በሕዝቦች መካከል መለያየት፣ ጦርነት እና ግጭት በበዛበት ዓለም ውስጥ፣ለሚሰጡ ልዩ የወንጌል አገልግሎት አፅንዖት ሰጥተው፥ በዚህም ረገድ ጳጳሳዊ የተልዕኮ ማኅበር በተለይም በጥላቻ እና በዓመፅ በተጎዱ አካባቢዎች የእምነት ብርሃን እና ክርስቲያናዊ በጎነትን በዓለም ዙሪያ ላሉ ሕፃናት በማድረስ ለሚያበረክተው ውድ ተልዕኮ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የዚህ ማኅበር ዕርዳታ ተቋዳሽ የልሆኑ በርካታ ቦታዎች መኖራቸውን የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ የዘርዓ ክኅነት ትምህርት ቤት ጀማሪዎች ለሰብዓዊ፣ መንፈሳዊ እና ሐዋርያዊ ዝግጅታቸው የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ እንደማያገኙ አስረድተው፥ በጳጳሳዊ የተልዕኮ ማኅበራት የሚስዮናዊነት ሥራ ላይ የሚሳተፉትን በሙሉ ለእግዚአብሔር እናት፣ የተልዕኮ ንግሥት እና የሚስዮናዊ ቅዱሳን ሁሉ እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት በአደራ በመስጠት ንግግራቸውን ደምድመዋል።
