እህት ስሜሪሊ የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት ጽሕፈት ቤት አዲስ ሃላፊ ሆነው ተሾሙ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት ጽሕፈት ቤት አዲስ መሪዎችን የሾሙ ሲሆን፥ እህት አሌሳንድራ ሰሜሪሊ የጽሕፈት ቤቱ ሃላፊ፣ ካርዲናል ፋቢዮ ባጆ ለ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ከፍተኛ ትምህርት ማዕከል ልዩ ሃላፊነት ጋር የጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ ምክትል ሃላፊ እና አባ ጆዜፍ ባርላሽን ጸሐፊ አድርገው መሾማቸው ታውቋል።
ሦስቱም ሹመቶች በቅድስት መንበር የታወጁት ማክሰኞ 23/2018 ሲሆን ተግባራዊ የሚሆኑትም ከነሐሴ 26/2018 ዓ. ም. ጀምሮ እንደሆነ ታውቋል።
የዶን ቦስኮ ሳሌዥያን እህቶች ማኅበር አባል የሆኑት እህት አሌሳንድራ ስሜሪሊ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ2021 ዓ. ም. ጀምሮ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ጸሐፊ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ 2022 ዓ. ም. ጀምሮ የጽሕፈት ቤት ዋና ሃላፊ የነበሩትን ካርዲናል ሚካኤል ቼርኒን እንደሚተኩ ታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በተጨማሪም የጽሕፈት ቤቱ ምክትል ጸሐፊ ሆነው ያገለገሉትን ካርዲናል ፋቢዮ ባጆን ምክትል ሃላፊ አድርገው ሾመዋቸዋል። ብፁዕ ካርዲናል ባጆ በአዲሱ ሥራቸው ቅድስት መንበር ፍጥረትን በመንከባከብ ሁለንተናዊ ዕድገትን ለማስፋፋት ያላትን ቁርጠኝነት የሚከታትል የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ከፍተኛ የትምህርት ማዕከል ልዩ ኃላፊ ሆነው ያገለግላሉ።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እንደዚሁም እስከ ዛሬ ድረስ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱን በምክትል ጸሐፊነት ያገለገሉትን አባ ጆዜፍ ባርላሽን አዲሱ ዋና ጸሐፊ አድርገው ሰይመዋል።
ሹመቱ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት፥ በፍትህ እና ሰላም፣ በስደት፣ በጤና አጠባበቅ፣ በበጎ አድራጎት፣ በፍጥረት እንክብካቤ እና በዓለም ዙሪያ የሰው ልጅ ክብርን በማስተዋወቅ የቤተ ክርስቲያኗን ተግባር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የሚጥር አዲስ የአመራር ቡድንን ሙሉ ማድረጉ ታውቋል።
