ሊቀ ጳጳስ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በሞስኮ ተገኝተው ጦርነቱ ማብቃት አለበት ማለታቸው ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ማክሰኞ ነሐሴ 19/2018 ዓ.ም በሞስኮ በሚገኘው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካይ ቢሮ በተካሄደው የሁለትዮሽ ስብሰባ ላይ፣ ቅድስት መንበር ከክልሎች እና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር የምታደርገውን ግንኙነት በበላይነት የሚቆጣጠረው ጽ/ቤት ጸሐፊ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ፖል ሪቻርድ ጋላገር እና የሩሲያ ፌዴሬሽን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ በዋና ዋና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ በርካታ አንገብጋቢ ዘርፎችን ለይተው አውጥተዋል፣ በሩሲያ ፌዴሬሽን እና በቅድስት መንበር መካከል የሚደረገውን ቀጣይ ውይይት አስፈላጊነት ላይ ተስማምተዋል።
በሁለቱም ጉዳዮች ላይ የተወያየነው በሩሲያ ውስጥ ስላለው የካቶሊክ ማህበረሰብ እና በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ሰላም ለመፍጠር የታለሙ የሰብአዊ ተነሳሽነቶችን ላይ ነው ሲሉ ሊቀ ጳጳስ ፖል ጋላገር ተናግረዋል።
ድርድሮች እና የሰብአዊ ቁርጠኝነት
በሞስኮ የሚገኘው የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ መንበር ልዑክ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ጆቫኒ ዲአኒሎ በተገኙበት እና ከአንድ ሰዓት በላይ የፈጀው ስብሰባው ሲያበቃ፣ ሊቀ ጳጳስ ጋላገር እና የሩሲያ ውጪ ጉዳይ ሚንስትር ላቭሮቭ ለፕሬስ መግለጫ ሰጥተዋል።
የቅድስት መንበር ከፍተኛ ተወካይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ያለውን ግጭት ለማስቆም እና በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ድጋፍ “እውነተኛ ድርድር” ለመጀመር ያቀረቡትን ጥሪ አስታውሰዋል።
ሊቀ ጳጳስ ጋላገር “የቅድስት መንበር አቋም ግልጽ ነው፣ ግጭቱ በወታደራዊ መንገድ ሊፈታ አይችልም” የሚል ነው ያሉ ሲሆን ስለዚህ፣ “ለፖለቲካዊ እና ለዲፕሎማሲያዊ ሂደት ሁኔታዎችን መፍጠር አስፈላጊ ነው” ብለዋል።
የቫቲካን ባለሥልጣን ሩሲያ እና ዩክሬን ግልጽነት እና በጎ ፈቃድ እንዲያሳዩ እንዲሁም ዓለም አቀፍ እና የሰብአዊነት ሕግን እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርበዋል፣ በተለይም ለሲቪሎች፣ ለመሠረተ ልማት፣ ለቆሰሉ እና ለጦር እስረኞች እንክብካቤ እና ጥበቃ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ጦርነቱ ማብቃት አለበት
“ግልጽ ለመሆን” ሲሉ ሊቀ ጳጳስ ጋላገር በዩክሬን ስላለው ሁኔታ የተናገሩ ሲሆን “ይህ ጦርነት ማብቃት አለበት” ብለዋል።
በሁለቱም ወገኖች የሚደርሰው ጉዳት ቁጥር በጦርነቱ ምክንያት እየጨመረ መምጣቱን ቀጥሏል፣ የሲቪል ህዝብም ስቃይ እንዲሁ ሲሉ የተናገሩት ሊቀ ጳጳስ ፖል ጋላገር “ያለፈውን ስህተት እስረኛ ላለመሆን ጥላቻን ማስቆም እና የወደፊት ግንኙነቶችን ማቀድ አስፈላጊ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
በሩሲያ እና በቅድስት መንበር መካከል ያለውን ትብብር ማጠናከር
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ላቭሮቭ፣ የቅድስት መንበር ከሩሲያ ጋር ለመነጋገር ላሳዩት ግልጽነት እና ለሰላም ላላት ቁርጠኝነት አድናቆታቸውን ገልጸዋል፣ ከቫቲካን አቻቸው ጋር ከግጭቱ ጋር በተያያዙ የሰብአዊ ጉዳዮች ላይ ትብብርን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ ስብሰባውን “በጣም ጠቃሚ” ሲሉ ገልጸውታል
ቅድስት መንበር ለሰላም የሰጠችው ቁርጠኝነት
ቫቲካን ከአገሮች እና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር የምታደርገውን ግንኙነት በበላይነት የሚቆጣጠረው ጽ/ቤት ዋና ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ ፖል ሪቻርድ ጋላገር “በሰብአዊነት መስክ ውስጥ ማንኛውም ተጨባጭ ውጤት፣ መከራን ለማስታገስ እና በግጭቱ ውስጥ ባሉ ወገኖች መካከል ያለውን ዝቅተኛ የመተማመን ደረጃ ወደነበረበት ለመመለስ ይረዳል” ብለዋል። በዚህ ረገድ፣ የካርዲናል ዙፒ ወደ ሩሲያ የሚያደርጉትን ተልዕኮ አስፈላጊነት አስታውሰዋል።
በዚህ ረገድ ቅድስት መንበር ለንግግር ቦታ ለመፍጠር፣ የሰብአዊ ጥረቶችን ለማጠናከር እና የሁለቱም አገሮች“ጥሩ ቢሮዎቻቸው” ሰላምን ለማምጣት አስተዋጽኦ ለማድረግ ያላቸውን ቁርጠኝነት በድጋሚ ሊቀ ጳጳስ ፖል ጋላገር ገልጿል።
አብያተ ክርስቲያናት ሰላምን በመገንባት ረገድ ያላቸው ሚና
ከሩሲያው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ላቭሮቭ ጋር ባደረጉት ስብሰባ፣ ሊቀ ጳጳስ ጋላገር አብያተ ክርስቲያናት እና የአካባቢው የቤተ ክርስቲያን ማህበረሰቦች በጣም ተጋላጭ የሆኑትን ለመርዳት፣ በእርቅ መንፈስ ውስጥ ያላቸውን ጠቃሚ ሚና ለማስታወስ ፈልገው ነበር።
በዚህ አውድ ውስጥ፣ ቫቲካን ከአገሮች እና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር የምታደርገውን ግንኙነት በበላይነት የሚቆጣጠረው ጽ/ቤት ዋና ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በሩሲያ ፌዴሬሽን ውስጥ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን ሁኔታ እና ፍላጎቶች በተለይም የካቶሊክ ምዕመናን የእረኝነት እንክብካቤ፣ በቤተ ክርስቲያን እና በሃይማኖት ማህበረሰቦች የሚከናወኑ የበጎ አድራጎት ተግባራትን በተመለከተ አጉልተው አሳይተዋል።
ከሞስኮ ፓትርያርክ ጋር የተደረገ ውይይት
ማክሰኞ ምሽት ነሐሴ 19/2018 ዓ.ም ቫቲካን ከአገሮች እና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር የምታደርገውን ግንኙነት በበላይነት የሚቆጣጠረው ጽ/ቤት ዋና ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ ፖል ሪቻርድ ጋላገር ከዚያም የሞስኮ ፓትርያርክ የውጭ ቤተክርስቲያን ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ ከሆኑት የቮሎኮላምስክ ሜትሮፖሊታን አንቶኒ ጋር መገናኘታቸው ተገልጿል።
በአሁኑ ክልላዊ ሁኔታ ላይ በመመስረት የጋራ ጥቅም ያላቸውን ጉዳዮች ተወያይተዋል። ሜትሮፖሊታን አንቶኒ በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት እና በቅድስት መንበር መካከል ባለው ቀጣይነት ባለው እና ወዳጃዊ ግንኙነት እርካታቸውን ገልጿል።
