ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ “እንደ ጴጥሮስ ግራ ስንጋባ ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር ይገባል” ሲሉ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እሑድ ነሐሴ 24/2018 ዓ. ም. በካስቴል ጋንዶልፎ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር ሆነው የመልአከ እግዚብሔር ጸሎት አድርሰዋል። ቅዱስነታቸው በቦታው ለተገኙት ምዕመናኑ ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ ቅዱስ ጴጥሮስ ሰው እንደ መሆኑ ግራ መጋባቱን አስታውሰው፥ ልባችንም ግራ ቢጋባም እውነተኛ ስሜቶቻችንን ለኢየሱስ ክርስቶስ በትህትና መንገር አለብን” ሲሉ አሳስበዋል።

ክቡራት እና ክቡራን፥ ከዚህ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዕለቱ ለምዕመናን ያሰሙትን ቃለ-ምዕዳን ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እህቶቼ፥ መልካም ዕለተ ሰንበት ይሁንላችሁ! የዛሬው ቅዱስ ወንጌል ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የሚመጣውን የመከራውን ምስጢር እንዴት እንደገለጠላቸው ይነግረናል። ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም መሄድ እንዳለበት በሽማግሌዎች፣ በካኅናት አለቆች እና በጻፎች እጅ ብዙ መከራን መቀበል እንዳለበት፣ መገደል እና በሦስተኛውም ቀን ከሞት መነሳት እንደሚገባ ተናግሯል” (ማቴ 16፡21)።

እርሱ የነገራቸውም ድል አድራጊ እና ኃያል ከሆነው መሲሕ ከሚጠብቁት እጅግ የራቀ ነው። እርሱ የሚያስጨንቋቸውን ጠላቶች ድል አድርጎ እንደሚረግጣቸው ነገራቸው። (መዝ 108፡13)። አስቀድመው ከእርሱ ጋር ባሳለፉት ጊዜያት በብዙ ተግባሮቹ እና ቃሎቹ ተደንቀው ነበር። ሆኖም ይህ የመጨረሻው መልዕክት በእርግጥ ከሚጠበቀው በላይ ነው። በተለይም ጴጥሮስ ገለል አድርጎ ወስዶት እንዲህ አለው፥ ‘ጌታ ሆይ! ይህ ከቶ አይድረስብህ’ ብሎ ይገስጸው ጀመር (ማቴ 16፡22)።

ከጥቂት ጊዜያት በፊት ጴጥሮስ፥ “ኢየሱስ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ መሲሕ” መሆኑን አውቆት ነበር (16:16)። አሁን ግን በሰማው ነገር በመገረም እና ምናልባትም ተስፋ በመቁረጥ ኢየሱስን ገሰጸው። ይህም አሁን ካሳየው ድንቅ የእምነት መግለጫ ጋር የሚቃረን ነው። ‘አዎ አንተ መሲህ እንደሆንክ በእርግጥ አምናለሁ፤ ነገር ግን ዓለም የሚድነው በዚህ መንገድ አይደለም’ ሲል መለሰ። የጴጥሮስ ንግግር ቅንዓት የተሞላበት እና በእርግጠኝነት በቅን ልቦና በመነሳሳት ያለው ነው። ሆኖም ግን አንድ ነገር እንድንገነዘብ ያደርገናል።

እንደ እውነቱ ከሆነ የእግዚአብሔርን መንገዶች መረዳት እና መቀበል ለእኛም ቢሆን ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። በተለይም እኛ ከምናስበው እጅግ የራቁ ሲሆኑ ነው። በእምነታችን ውስጥ ፈተና የሚመጣው እግዚአብሔር እንደሚሳሳት፣ እንደማያዳምጠን ወይም ደግሞ ለእኛ እንደማይጨነቅልን ስናስብ ነው። በዚህ እርግጠኛ ባልሆነበት ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ሁለት አስፈላጊ ነገሮችን ያስተምረናል።

የመጀመሪያው በእንደዚህ ዓይነት ጊዜያት ውስጥም ቢሆን ከእግዚአብሔር ጋር የምናደርገውን ውይይት በፍጹም አለማቋረጥ። በምትኩ ከእኛ ምን እንደሚፈልግ በማወቅ ችግሮቻችንን በሙሉ በልበ ሙሉነት ልንነግረው ይገባል።

ሁለተኛው በእግዚአብሔር ሥራ ላይ ፈጽሞ አለመፍረድ። ሥራዎቹ እኛ ከምንጠብቃቸው ነገሮች ጋር የማይጣጣሙ እንኳ ቢሆኑ እርሱ የሚገልጽልንን ነገር በትህትና እና በጸሎት ማዳመጥ ያስፈልጋል። በዚህም የሐዋርያቱ የመጀመሪያው ታላቅነት በግልጽ ይታያል።

ኢየሱስ ግን ዞሮ ጴጥሮስን፥ ‘ወደ ኋላዬ ሂድ፤ አንተ ሰይጣን!’ ሲል መለሰ (ማቴ. 16:23)። ጴጥሮስ እና ሌሎች ደቀ መዛሙርት የእርሱን ፈለግ ለመከተል ራሳቸውን መካድ፣ መስቀላቸውን ተሸክመው መከተል እንዳለባቸው አስረዳቸው (ማቴ. 16:24)። ጴጥሮስም ኢየሱስን ካዳመጠው በኋላ ፈተናውን በመቀበል እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ ቤዛው አድርጎ ለቆጠረው ለኢየሱስ ክርስቶስ ቃል እስከ ሰማዕትነት ድረስም ታማኝ ሆኖ ቆየ።

ስለዚህ እኛም ልባችን ግራ ቢጋባም በእምነት እና በጸሎት ሕይወት ውስጥ የሚሰማንን በሙሉ ልክ እንደ ጴጥሮስ በቅንነት ለኢየሱስ ክርስቶስ በትህትና እንነግረው። እንደዚሁም ኢየሱስ ክርስቶስ ከሚጠበቅብን በላይ የሚጠይቀንን በመቀበል የጴጥሮስን ገርነት በውስጣችን እናዳብር።

በልጇ በኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ሥር ሆና ለእግዚአብሔር እቅድ ታዛዥ የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትርዳን።” በማለት ቃለ-ምዕዳናቸውን አጠቃልለዋል።

31 Aug 2026, 15:48