ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቫቲካን ከላቲን አሜሪካ የጳጳሳት ኮሚሽን  ጋር በተገናኙበት ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቫቲካን ከላቲን አሜሪካ የጳጳሳት ኮሚሽን ጋር በተገናኙበት ወቅት  (@VATICAN MEDIA)

ር.ሊ.ጳ ሊዮ ቤተ ክርስቲያን የተጎዱ ቤተሰቦችን ከአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኝነት እንዲፈወሱ መርዳት አለባት አሉ!

ከላቲን አሜሪካ የጳጳሳት ኮሚሽን ጋር ባደረጉት ስብሰባ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በላቲን አሜሪካ የምትገኘው ቤተ ክርስቲያን በአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኝነት፣ በዓመፅ ወይም በድህነት ህመም የሚሰቃዩ ቤተሰቦችን እንድትንከባከብ አበረታተዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሐሙስ ዕለት ነሐሴ 21/2018 ዓ.ም በ"በላቲን አሜሪካ የአደንዛዥ ዕፅ ሱስ" በሚል ርዕስ ላይ ባተኮረው ስብሰባ ላይ ከተሳታፊዎች ጋር ተገናኝተዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በንግግራቸው፣ በሃይማኖት ላይ ከተመሰረቱ ማዕከላት የተውጣጡ በርካታ ሰዎችን ተቀብለው በአደንዛዥ ዕፅ  የተጎዱ ወጣቶችን መንከባከብ እና ማጀብ፣ መከላከል፣ የማገገሚያ ሥፍራ ማዘጋጀት እና ውህደት ላይ የተቀናጀ ተግባር እንዲያከናውኑ ቅዱስነታቸው ጋብዘዋል።

የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኝነት ተጽእኖን በማጤን፣ ከእስያ፣ ከአፍሪካ፣ ከአውሮፓ እና ከአሜሪካ የመጡ ተሳታፊዎች “ስቃይ እና ተስፋ ድንበር የላቸውም” በሚል ጭብጥ ዙሪያ ላይ እየተወያዩ እንደሚገኙ ተገልጿል።

በስብሰባው ላይ የተገኙት አራት የትብብር መንገዶችን የሚወክሉ አራት “ድልድዮች” ጠቁመዋል።

በመጀመሪያ፣ ቤተ ክርስቲያኗ የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኝነትን ለመዋጋት ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በቅርበት ትሰራለች።

ኮሚሽኑ ከአሜሪካ መንግስታት ድርጅት (OAS) እና ከላቲን አሜሪካ እና ካሪቢያን የጳጳሳት ምክር ቤት (CELAM) ጋር በመተባበር ሰዎችን በእምነት ላይ ለተመሰረቱ የማህበረሰብ ድርጅቶች ለማሰልጠን እንደሚረዱ ተናግረዋል።

ሁለተኛ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሳይንስ እና እምነት ሌላ ድልድይ እንደሚፈጥሩ ተናግረዋል፣ ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን ከነርቭ ሥርዓት እና የአንጎል ሳይንሳዊ ጥናት፣ የአእምሮ ሕክምና ወይም ከህዝብ ጤና ጋር መወዳደር አትፈልግም ብለዋል። "ይልቁንስ፣ የወንጌልን ብርሃን በሰው ልጅ ላይ ባለው ጥልቅ ግንዛቤ ለማብራት ትፈልጋለች" ብለዋል።

ሦስተኛ፣ ቤተክርስቲያን የጋራ ግቦች ያሏቸው ሰዎች "ስቃያቸውን፣ ተስፋቸውን እና የእረኝነት ጉጉታቸውን ለመጋራት" በሚሰበሰቡበት ጊዜ በሁሉም አህጉራት መካከል እንደ ድልድይ ሆና ታገለግላለች ሲሉ ቅዱስነታቸው ተናግረዋል።

አራተኛ፣ ቤተ ክርስቲያን እና ሌሎች የቤተ ክርስቲያን ማህበረሰቦች እምነትን እንደ የጋራ ቋንቋ አድርገው የሚጠቀሙበት ሲሆን በሱስ ለሚሰቃዩ ሰዎች ተጨባጭ ፍቅርን ማሳየት ይኖርብናል ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የቤተሰብን ማዕከላዊነት አጉልተው በመግለጽ "የቤት ውስጥ ቤተ ክርስቲያን" በማለት ሱሰኝነትን ለመዋጋት በሚደረጉ ጥረቶች ሁሉ ውስጥ የቤተሰብ ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።

ቤተሰብ "ሕይወት የሚንከባከቡበት፣ ፍቅር የሚለግሱበት እና መመሪያ የሚሰጥበት ቦታ ነው። ከጥሩ ቤተሰብ የተሻለ ከአደንዛዥ ዕፅ ሱስ የሚከላከል ቦታ የለም" ሲሉ ቅዱስነታቸው ተናግረዋል።

የቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንዳሉት ከሆነ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ “የሰውን ስቃይ ለመጋራት፣ የሌሎችን ስቃይ ለመረዳት ትፈልጋለች” ብለዋል።

“ዛሬ” ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ሐዘናቸውን በመግለጽ ፣ “በዕፅ አጠቃቀም፣ በዓመፅ፣ ልጆችን ለወንጀል መቅጠር፣ በድህነት ወይም ሰዎችን ወደ ዳር በሚገፋፉ እድሎች ምክንያት የብዙ ቤተሰቦችን ስቃይ እናያለን” ሲሉ ቅዱስነታቸው ሐዘናቸውን ገልጸዋል።

በማጠቃለያ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የላቲን አሜሪካ የጳጳሳት ኮሚሽን እና በሱስ ዘርፍ የሚሰሩትን ሁሉ በዚህ ሥራ እንዲቀጥሉ አበረታተዋል።

“ቤተ ክርስቲያኒቱ በመንገድ ዳር የተተው ሁሉ ቤተሰብ ትሁን” ብለዋል። “የምትቆም፣ የምትቀርብ፣ በርኅራኄ የምትንቀሳቀስ፣ ቁስልን የምትቀባ፣ ምግብ የምትሰጥ እና ቤት የምትሆን ቤተ ክርስቲያን እንገንባ” ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው ንግግራቸውን አጠናቀዋል።

28 Aug 2026, 15:31