በቫቲካን በሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ መስዋዕተ ቅዳሴ በመቅረብ ላይ  በቫቲካን በሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ መስዋዕተ ቅዳሴ በመቅረብ ላይ   (@Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ ሊዮ 14ኛ፥ “የፍቅር ደስታ” ሐዋርያዊ ምክር 10ኛ ዓመት በመስዋዕተ ቅዳሴ እንደሚያከብሩት ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሚቀጥሉት ወራት ውስጥ በመስዋዕተ ቅዳሴ የሚያከብሯቸውን የመንፈሳዊ በዓላት የጊዜ ሠሌዳ መርሃ ግብር ቫቲካን ይፋ አድርጓል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቤተሰብ ውስጥ ያለውን ፍቅር በማስመልከት፥ “Amoris Laetitia” (የፍቅር ደስታ) በሚል ርዕሥ የታተመበት አሥረኛ ዓመት የመታሰቢያ መስዋዕተ ቅዳሴን ረቡዕ ጥቅምት 4/2019 ዓ. ም. እንደሚያከብሩት ይጠበቃል።

“የፍቅር ደስታ” የተሰኘ ሐዋርያዊ ምክር ከአሥር ዓመት በፊት የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዘመናዊው ዓለም ቤተሰቦችን በሚያጋጥሟቸው ችግሮች ላይ ለመወያየት የጠሩትን የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ማጠናቀቂያን እና ዓመታዊው የቅዱስ ዮሴፍ በዓልን ተከትሎ በመጋቢት 10/2008 ዓ. ም. መታተሙ ይታወሳል።

ይህ ሐዋርያዊ ምክር ከታተመ ከአሥር ዓመታት በኋላ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥  በ “የፍቅር ደስታ” ሐዋርያዊ ትምህርቶች እና ወንጌልን ለቤተሰቦች ማወጅ በሚቻልበት መንገድ ላይ ለመወያየት በዓለም  ዙሪያ የሚገኙ የጳጳሳት ጉባኤዎች ፕሬዝደንቶችን ወደ ሮም ጠርተዋል።


በቀጣይ ጊዜያት የሚፈጸሙ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓቶች

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሚቀጥሉት ጊዜያት ውስጥ ከሚፈጸሟቸው ልዩ ልዩ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓቶች መካከል አንዱ ከሮም ወጥ ብላ በምትገኝ በጄናዛኖ የመልካም ምክር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚያቀርቡት መስዋዕተ ቅዳሴ እንደሆነ ታውቋል።

ቅዱስነታቸው ለርዕሠ ሊቃነ ጵጵስና በተመረጡበት በሁለተኛው ቀን ማለትም ግንቦት 2/2017 ዓ. ም. ቤተ ክርስቲያኑን ጎብኝተው እንደ ነበር ይታወሳል።

ቤተ ክርስቲያኑ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ አባል በሆኑበት በቅዱስ አጎስጢኖስ ማኅበር እንደሚተዳደር ታውቋል።

በመጭው መስከረም ወር መጨረሻ ላይ ርዕሥ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በፈረንሳይ ሐዋርያዊ ጉዞ የሚያደርጉ ሲሆን፥ ይህም በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ዋና መሥሪያ ቤት የሚያደርጉትን ጉብኝት ያካትታል።


ቅዱስነታቸው በፈረንሳይ ከመስከረም 15-18/2019 ዓ. ም. በሚያደርጉት የአራት ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት በፓሪስ፣ በሉርድ እና በሜትዝ ውስጥ በርካታ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓቶችን እንደሚፈጽሙ ይጠበቃል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመጨረሻም መስከረም 28/2019 ዓ. ም. የጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት ዓመት መጀመሪያን ምክንያት በማድረግ መስዋዕተ ቅዳሴን እንደሚያቀርቡ የቫቲካን መግለጫ አስታውቋል።

 

29 Aug 2026, 15:24