የፍልስጤም እና የእስራኤል ጦርነት የፍልስጤም እና የእስራኤል ጦርነት  (AFP or licensors) ርዕሰ አንቀጽ

“የፍልስጤም ሕዝብን ያገለለ ‘አዲሱ የመካከለኛው ምሥራቅ’ እቅድ”

የቅድስት መንበር መገናኛዎች ርዕሠ አንቀጽ ዝግጅት ክፍል ሃላፊ አቶ አንድሬያ ቶርኔሊ ፍልስጤማውያንን በግዳጅ ከመሬታቸው ለማፈናቀል በወጣው ‘አዲስ የመካከለኛው ምሥራቅ’ እቅድ ላይ በማሰላሰል፥ ሰላማዊ ዜጎችን የመጠበቅ ግዴታ እንዲከበር በማለት የሚከተለውን ርዕሠ አንቀጽ አዘጋጅቷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“የእስራኤል እና የፍልስጤም ግጭት የክርክር እና ያለመግባባት ምንጭ ሆኖ ቆይቷል። አሁን በጋዛ እየተካሄደ ያለው ጦርነት እና በዙሪያው ያሉ ውዝግቦች ክስተት የበለጠ ጽንፍ እንዲደርስ አድርጎታል።አንዳንዴም ጠንከር ያሉ እና ወደ ጫፍ የደረሱ ልዩነቶች በብዙ የዓለም ሀገራት እና ማኅበረሰብ ውስጥ ይከሰታሉ።

እንደዚህ ባለ ውስብስብ አውድ ውስጥ ለስህተት እና ለጉዳት የሚያጋጡ ምክንያቶች አይጠፉም። ይህ የሚሆነው እጅግ ስሜታዊ የሆነ አቀራረብ እና ቋንቋን በሚጠቀሙበት ጊዜ እና ሌላውን ለማዳመጥ ካለመሞከር ሊሆን ይችላል።

ከሁለት ዓመታት በፊት ሃማስ የፈፀመው የሽብር ተግባር ያለ ምንም ጥርጥር የሚወገዝ ነው። ለተፈጸመው አስደንጋጭ ጥቃት ከእስራኤል በኩል የተሰጠው ምላሽ የተጠበቀ ነበር።

ከእስራኤል በኩል የተሰጠው ይህ ምላሽ በብዙ ዓለም አቀፍ ባለስልጣናት ብቻ ሳይሆን በእስራኤል በራሷ፣ በአይሁድ ማኅበረሰብ እና በሰፊው በሚታወቁት ዘንድም ተቀባይነት የሌለው፣ ከማንኛውም የሥነ-ምግባር ገደብ በላይ የሆነ እና ያልተመጣጠነ ምላሽ ነው።

በቀሪው የፍልስጤም አካባቢ በአንድ ወቅት ዌስት ባንክ ይባል የነበረውን ግምት ውስጥ በማስገባት በጋዛ የተከፈተውን ጦርነት ብንመረምረው በመስከረም 26/2016 ዓ. ም. ለደረሰው እልቂት ምላሽ ከመስጠት ባለፈ ሌሎች ዓላማዎችም እንዳሉት ማሰብ እንችላለን።

የሠፈራ መስፋፋት፣ በሠፋሪዎች ላይ የሚደርሱ ቀጣይነት ያላቸው ጥቃቶች፣ የፍልስጤም አስተዳደር መጨረሻ እንደሚሆን ተስፋ የሚያደርጉ አንዳንድ የእስራኤል መንግሥት ሚኒስትሮች የሚሰጡት መግለጫዎች፣ ሁሉንም ግዛቶች በመጠቅለል ፍልስጤማውያንን የማፈናቀል ዓላማ፥ አንድ ሰው ይህ ተግባር ሃማስን ከማስወገድ ወይም ለእስራኤል መንግሥት ደኅንነት ዋስትና ከመስጠት የዘለለ ነው ብሎ እንዲያስብ ያደርገዋል።

በቅርብ ቀናት ውስጥ በ “E1” አካባቢ አዲስ የሠፈራ ፕሮግራም ጸድቋል። ይህም ግዛቱን በተጨባጭ ለሁለት የሚከፍል ነው። በተመሳሳይ መልኩ “C” የተባለውን የፍልስጤም ግዛት ለመጠቅለል ንግግር እየተደረገ ይገኛል። ከዚህም በተጨማሪ አካባቢው በእስራኤል ሙሉ ቁጥጥር ስር ያለ ሲሆን ይህም በይፋ አልተካተተም።

በዚህ ከጊዜ ወደ ጊዜ ውጥረቱ በበዛበት አውድ ውስጥ “የአዲሱ መካከለኛው ምሥራቅ ዕቅዶች” አንድ በአንድ እየታተሙ ይገኛል። ይህ አዲስ ሥርዓት በመጀመሪያ በጸጥታ እየተከናወነ የነበረ ቢሆንም የፍልስጤም ሕዝብ ቦታ የሌለው መሆኑ አሁን ይበልጥ ግልጽ እየሆነ የመጣ ይመስላል።

ከእነዚህ ዕቅዶች መካከል የቅርብ ጊዜው ለወደፊት የጋዛ ልማት እየተነጋገሩ ያሉበት ሁኔታ ነው። ዕቅዱ ጋዛ ውስጥ አዲስ ከተሞችን እና ቅንጡ ሪዞርቶችን መገንባት ያመላክታል።

በተለምዶ የሚታወቀው “ፍልስጤማውያንን በፍቃደኝነት ማፈናቀል” የሚል ሲሆን፥ ይህም በፈቃደኝነት ፍልስጤማውያኑ ከፈለጉ ከዕለታት አንድ ቀን ሊመለሱ እንደሚችሉ ይፈቅዳል። በፈቃደኝነት መውጣት ለማይፈልጉ ደግሞ “ልዩ ዞኖች” እየተነደፉ ሲሆን፥ ይህም በራሱ የተለየ እቅድ መኖሩን የሚናገር ነው። አንድ ሰው ይህ የሳይንሳዊ ልበ ወለድ ሥራ ወይም የቅዠት ፊልም ሴራ ነው ብሎ አስቦ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ይምሰል እንጂ በሚያሳዝን ሁኔታ ይህ ፍልስጤማውያንን የማፈናቀል እውነተኛ ሴራ ነው።

የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ እና የባለብዙ ወገን አካላት ድክመት ይህንን ጉዞ ማስቆም ባለመቻሉ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ሆን ብሎ ችላ ማለታቸው ደንቦችን ማክበር እና የሞራል ሥነ-ምግባርን ማባባሱ የሚያሳዝን ነው። የቀረው ብቸኛው ቋንቋ አስቀድሞ በቃላት ከዚያም ወታደራዊ የሃይል እርምጃ መውሰድ ነው።

ቤተ ክርስቲያን የጦር መሣሪያ እና ማንኛውንም ነገር የመጫን አቅም የላትም። የእርሷ ብቸኛው መሣሪያ ጸሎት እና የወንጌል ጥንካሬ ነው። ነገር ግን ስለ ሰው ልጅ ስብዕና እና ስለ ዓለም ሕይወት ግልጽ የሆነ የእውነት ቃል እንድንናገር ያስገድደናል።

በሰው ሕይወት ላይ ባለ ንቀት ወይም በሰዎች ዘንድ የተከበረ እና አስተማማኝ ሕልውና ለማግኘት ያለውን ምኞት በመቃወም ወደፊት በኃይል ሊገነባ የሚችል ነገር የለም።

ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ፍራንችስኮስ እና ከዚያም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ጥሪ እንዳቀረቡት ሁሉ አሁንም በድጋሚ በጋዛ ዋሻዎች ውስጥ የታሰሩት ሁሉም የእስራኤል ታጋቾች በአስቸኳይ እንዲፈቱ እንመኛለን።

ለፍልስጤማውያንም ተመሳሳይ ሁኔታን በመመኘት ታጋቾቻቸው በአክብሮት እና በሰብዓዊነት እንዲያዙ፥ ጋዛ ውስጥም ፍልስጤማውያን በክብር እና ሰብአዊ በሆነ መንገድ እንዲስተናገዱ እንጠይቃለን።

በመላው የጋዛ  ሰርጥ አቅመ ደካሞች እና ሲቪሎች መጠጊያን የሚያገኙባቸው፣ ደህንነታቸው የተጠበቀ እና በዓለም አቀፍ ጥበቃ ሥር የሚገኙ ዞኖች እንደሚመሠረቱ ተስፋ እናደርጋለን።

“በፈቃደኝነት ማፈናቀል” ሲባል በግዳጅ ማፈናቀል፣ ጠቅላላ ውድመት ማስከተል፣ ማብቂያ የሌለው ሞት፣ ሆስፒታሎችን በጦር መሣሪያ መምታት፣ ለእንጀራ ፍለጋ የሚሰለፉትን በየዕለቱ መግደል፣ ለፍልስጤም ሕዝብ ክብር እና መኖሪያ ቤትን የሚሰጥ ማንኛውንም የፖለቲካ አድማስ መከልከል፣ እነዚህ በሙሉ የመካከለኛው ምሥራቅ የወደፊት ሚዛንን በጭራሽ አይገነቡም።

በሚያሳዝን ሁኔታ እየሆነ ያለው በጥላቻ የተሞላ ቀጣይ ሕዝብ ለመፍጠር የታሰበ እና ወደፊት ለሌላ የኃይል ማዕበል ግምጃ ቤት የመሆን ስጋት ነው።

በፍልስጤማውያን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ የሚጫኑት አንዳንድ የልማት እቅዶች ሌላ ሳይሆን ነገር ግን በዓይነ ስውርነት በእነሱ ላይ የሚፈጸሙ የእብሪተኝነት ተጨማሪ ማረጋገጫዎች ናቸው። የፍልስጤማውያን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው ከእነርሱ ጋር አብሮ መሆን አለበት።

ቤተ ክርስቲያን ሁሌም እንደምታደርገው የሁሉንም ቁስል ለመጠገን የምታደርገውን ሙከራ ትቀጥላለች።

ለሕይወት ምቹ እና አማራጭ ሁኔታዎችን ለመፍጠር አብረው ለመሥራት ከሚፈልጉት ሁሉ ጋር ለመተባበር እጇን ትዘረጋለች። ለጥላቻ እና ለጦርነት አመክንዮ እጅ ለመስጠት ላልፈለጉ እና ተግባራዊ የሰላም መንገዶችን ለሚሹት በሙሉ በሮቿ ዘወትር ክፍት ሆነው ይቆያሉ።

ቅድስት መንበር ለብዙ ዓመታት ለፍልስጤም ግዛት በይፋ እውቅና ሰጥታለች። እየሆነ ያለውን ነገር እያየን ዝም ማለት አንችልም።

አሁንም በድጋሚ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛን ቃል የራሳችን በማድረግ፥ አረመኔያዊ ጦርነት እንዲቆም፣ ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሄ እንዲገኝ፣ የሰብዓዊነት ሕግ እና የሲቪል ሕዝብ ድኅንነት የመጠበቅ ግዴታ እንዲከበር፣ በሕዝብ ላይ የሚፈጸም የጋራ ቅጣት፣ የኃይል አጠቃቀም እና ሕዝብን በግዳጅ ማፈናቀል እንዲቆም እንጠይቃለን።”

 

03 Sep 2025, 16:39