አቶ ማክሲሚኖ ካባሌሮ ሌዶ፥ አቶ ማክሲሚኖ ካባሌሮ ሌዶ፥  

አቶ ማክሲሚኖ ካባሌሮ፥ የቅድስት መንበር ፋይናንስ አወንታዊ ምልክቶችን ማሳየቱን ገለጹ

የቫቲካን የኢኮኖሚ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ማክሲሚኖ ካባሌሮ በቅድስት መንበር የ2024 ዓ. ም. (እ.አ.አ) የፋይናንስ ሪፖርት ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል። አቶ ማክሲሚኖ በማብራሪያቸው “የቅድስት መንበር ኢኮኖሚን በማጠናከር ረገድ ጉልህ ዕድገት ታይቷል” ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቅድስት መንበር የኢኮኖሚ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ማክሲሚኖ ካባሌሮ ሌዶ፥ በቅድስት መንበር ፋይናንስ ላይ አዎንታዊ እና አበረታች ምልክቶች መታየታቸውን ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል።

የቫቲካን የኢኮኖሚ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት የቅድስት መንበርን የ2024 ዓ. ም. (እ.አ.አ) ዓመታዊ የፋይናንስ ሪፖርት ረቡዕ ኅዳር 17/2018 ዓ. ም. ይፋ አድርጓል።

አቶ ማክሲሚኖ ካባሌሮ በቃለ ምልልሳቸው የታዩትን ለውጦች በማብራራት፥ ምቹ ሁኔታዎችን የፈጠሩ ጉልህ እርምጃዎችን ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ በማጥናከር ቀጣይነት እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

“የበጀት ሚዛንን መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ቅድስት መንበር እያንዳንዱን መዋጮ በተቻለ መጠን በአግባቡ የመጠቀም ችሎታዋን ማጠናከር አለባት” ሲሉ አፅንዖት የሰጡት አቶ ማክሲሚኖ ካባሌሮ፥ “ይህም ዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን የምትሰጠውን የወንጌል ተልዕኮ አገልግሎት ይበልጥ ጠንካራ እና ዘላቂ ለማድረግ ነው” ብለዋል።


እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2024 ዓ. ም. የተመዘገበው የመዋቅር ጉድለት መሻሻል ከ83.5 ወደ 44.4 ሚሊዮን ዩሮ በመቀነሱ የቅድስት መንበርን የኢኮኖሚ ሁኔታ በማጠናከር ረገድ ጉልህ ዕድገትን እንዳሳየ እና ይህ ውጤት ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በጠቅላላ ገቢ ላይ ወደ 79 ሚሊዮን ዩሮ የሚጠጋ ጭማሪ ማሳየቱን አቶ ማክሲሚኖ ካባሌሮ አስረድተዋል።

“ጭማሪው በልገሳዎች እድገት፣ በሆስፒታሎች አገልግሎት አወንታዊ ውጤቶች፣ በንብረት እና በንግድ አስተዳደር ውስጥ በተመዘገበው ዕድገት የተገኘው ነው” ብለዋል።

እነዚህ ምቹ ሁኔታዎች በወጪዎች ላይ ጥንቃቄ የተሞላበት ቁጥጥር እንዲደረግ እና የአሠራር ቅልጥፍናን ለማሻሻል የማያቋርጥ ጥረት በማድረግ ጉድለትን በከፍተኛ ሁኔታ ለመቆጣጠር አበረታች አቅጣጫን ለማመልከት ማስቻሉን አስረድተዋል።

“ምንም እንኳን ከፍተኛ መሻሻል ቢታይም የ44.4 ሚሊዮን ዩሮ ጉድለት አሁንም አለ” ያሉት አቶ ማክሲሚኖ ካባሌሮ፥ ይህንን ፈተና ወደ ሙሉ የፋይናንስ ዘላቂነት በመቀየር ቀጣይነትን፣ እውነታዊነትን እና ዲሲፕሊንን ለመጋፈጥ በሚስዮናዊ ቁርጠኝነት እና ኃላፊነት በተሞላበት የሃብት አስተዳደር መካከል ያለውን ሚዛን ለመጠበቅ ወደ ሙሉ ዘላቂ ፋይናንስ በሚወስደው መንገድ ላይ ቁርጠኝነትን ማሳየት እንደሚገባ አሳስበዋል።

“የ2024 ዓ. ም. (እ.አ.አ) የምጽዋዕት አሰባሰብ አበረታች ነበር” ያሉት አቶ ማክሲሚኖ ካባሌሮ፥ “ለዓመታት ከቀነሱ በኋላ ምጽዋዕት መጨመራቸው ምዕመናን እና የአገራት ቤተ ክርስቲያናት በቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ተልዕኮ ውስጥ እንደገና በመሳተፋቸው ተስፋን ይሰጣል” ብለዋል።

“ይህ አዎንታዊ እውነታ ሲሆን እነዚህ ሁኔታዎች በጊዜ ሂደት ሊለያዩ እንደሚችሉ እና ሁልጊዜም በትርጉማቸው ውስጥ ጥንቃቄ እና እውነታዊነት እንደሚያስፈልጋቸው በማወቅ የበለጠ እምነት የሚጣልበት ሁኔታ መኖሩን ይጠቁማል” ብለዋል።

የወጪ ትንተና እንደሚያረጋግጠው፥ ለዓመታት የነበሩ አብዛኛዎቹ ሃብቶች በቀጥታ ለሐዋርያዊ ተግባራት የተመደቡ መሆናቸውን እንደሚያረጋግጥ አስረድተው፥ ይህ የበጀት አወቃቀር በጊዜ ሂደት የተረጋጋ፣ በተልእኮው ቅድሚያ የሚሰጥባቸውን ነገሮች እና እውን ለማድረግ በሚያስችሉት ኢኮኖሚያዊ ምርጫዎች መካከል ያለውን ወጥነት እንደሚያንጸባርቅ፣ የሐዋርያዊ አገልግሎት ተነሳሽነቶችን እንደሚያሻሽል እና አቅመ ደካማ የሆኑ የቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰቦችን የሚደግፍ መሆኑን አስረድተዋል።

ይህ በእውነት አዎንታዊ እና በእጃችን ላይ የሚገኙ ሃብቶችን በጥንቃቄ ቀጣይነት ባለው መንገድ እና በሚዛናዊነት ማስተዳደር መቀጠልን ያበረታታል ብለዋል።

በ2024 ዓ. ም. (እ.አ.አ) የተከናወኑ የፋይናንስ እንቅስቃሴዎች ውጤት አጠቃላይ የኢኮኖሚ ሁኔታን ለማሻሻል ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን የገለጹት አቶ ማክሲሚኖ ካባሌሮ፥ ይህም ዓመቱ በትርፍ እንዲጠናቀቅ ማስቻሉን ገልጸው፥ ከፍተኛ ጫናዎች ያሉበትን ሁኔታ ለመጋፈጥ እና ከቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ተልዕኮ ጋር ለተያያዙ ተግባራት ተጨባጭ ድጋፍ የሰጠ ጠቃሚ ድጋፍ እንደ ነበር አስረድተዋል።

“እነዚህ ውጤቶች በአዲሱ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ እና በኢንቨስትመንት ኮሚቴ መመሪያዎች መሠረት ከልምድ መረጃ ዝውውር ጋር በተያያዙ ያልተለመዱ ሥራዎች የተገኘ መሆኑ መታወስ አለበት” ብለዋል።

“ይህ አስተዳደር ከተቀመጡት መመዘኛዎች ጋር የበለጠ ወጥነት እንዲኖረው ለማድረግ አስፈላጊ እርምጃ ቢሆንም ነገር ግን በዚህ ደረጃ የተገኘው የካፒታል ትርፍ በቀጣዮቹ ዓመታት በተመሳሳይ ጥንካሬ ሊደገም እና የፋይናንስ እንቅስቃሴን ተፈጥሯዊ ተለዋዋጭነት ሊያንፀባርቅ አይችልም” ሲሉ አስረድተዋል።

በዚህ ምክንያት ወጪዎችን በማስተዳደር ረገድ የተደረገውን ጥንቃቄን ጨምሮ በገቢ በኩል መሥራት አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተው፥ ከልገሳ እስከ ገንዘብ ማሰባሰብ፣ ከሃብት ማጎልበት እስከ ኢንቨስትመንት አስተዳደር ከተቀመጡ መስፈርቶች ጋር በሚስማማ መልኩ መከናወን እንዳለበት አሳስበዋል።

ግቡ ሁለቱን ገጽታዎች እርስ በእርስ ማጣመር ሳይሆን የተገኘውን ዕድገት ማጠናከር እና ቀስ በቀስ የበለጠ የተረጋጋ የኢኮኖሚ መሠረትን ማዋቅር እንደሆነ ተናግረው፥ ይህም ቀጣይነት እና እውነታዊነትን የሚፈልግ ሂደት ስለሆነ የሚገኙ ሃብቶች የቅድስት መንበርን ተግባራት በብቃት እና በኃላፊነት መደገፍ እንደሚችሉ አስረድተዋል።

1.6 ሚሊዮን ዩሮ ጠቅላላ ትርፍ የታየበት የ2024 ዓ. ም. ውጤት ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነጻጸር እንዲህ ያለ ጉልህ ዕድገት በእርግጥ እጅግ አዎንታዊ ምልክት እንደሆነ ገልጸው፥ የተወሰደው አቅጣጫ አበረታች መሆኑን እንደሚያሳይ እና በተለይም መዋቅራዊ የአሠራር ጉድለት በመቀነሱ መሆኑን ያመላክታል ብለዋል።

አሁን የታየውን ዕድገት በጊዜ ሂደት ማጠናከር እንደሚገባ የተናገሩት አቶ ማክሲሚኖ ካባሌሮ፥ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው የዚህ መሻሻል አካል ተደጋጋሚ ያልሆኑ ምክንያቶች መሆናቸውን አስረድተዋል።

ከዚህም በላይ የፋይናንስ ዘላቂነት ሊከሰት የሚችል ብቻ ሳይሆን የቅድስት መንበር ተልዕኮ ቀጣይነትን ለማረጋገጥ አስፈላጊ ሁኔታን እንደሚያመቻች ተናግረው፥ ሐዋርያዊ ሥራ በተፈጥሮው ሰፊ በመሆኑ የተረጋጋ ኢኮኖሚያዊ መሠረትን እንደሚፈልግ አስረድተዋል።

“በዚህ ምክንያት በጥንቃቄ እና ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ሃብቶችን እንደገና በማከፋፈል ላይ መሥራታችንን መቀጠል አለብን” ብለው፥ ይህም ሚስዮናዊ አገልግሎት የበለጠ ውጤታማ በሆነ መንገድ መከናወኑን ያረጋግጣል” ብለዋል።

የበጀት ሚዛንን መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ቅድስት መንበር የተገኘውን እያንዳንዱን አስተዋጽኦ በተቻለ መጠን በአግባቡ የመጠቀም አቅሟን ማጠናከር እና ይህም የዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የበለጠ ጠንካራ እና ዘላቂ የሚያደርግ መሆኑን በቅድስት መንበር የኢኮኖሚ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ማክሲሚኖ ካባሌሮ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አስረድተዋል።

 

27 Nov 2025, 19:23