ምዕመናን በቅዱስ ቪንሴንት ማኅበር ገዳማውያን የኢዮቤልዩ በዓል ላይ ምዕመናን በቅዱስ ቪንሴንት ማኅበር ገዳማውያን የኢዮቤልዩ በዓል ላይ  (Jeffrey Ortega)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የመረጡት የመጭው አውሮፓውያኑ ዓመት ዓለም አቀፍ የተልዕኮ እሑድ ጭብጥ ይፋ ሆነ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2026 ዓ. ም. ለሚከበረው የዓለም የተልዕኮ እሑድ የመረጡትን እና “በክርስቶስ አንድ በመሆን በተልዕኮ መተባበር” የሚለው መሪ ጭብጥን ቫቲካን ይፋ አድርጓል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2026 ዓ. ም. የሚከበረው ዓለም አቀፍ የተልዕኮ ቀኑ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮ 11ኛ የተጀመረበትን 100ኛ ዓመትንም እንደሚያከብር ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በሚቀጥለው የጎርጎሮሳውያኑ 2026 ዓ. ም. ለሚከበረው ዓለም አቀፍ የተልዕኮ እሑድ የመረጡት መሪ ጭብጥ፥ “በክርስቶስ አንድ በመሆን በተልዕኮ መተባበር” የሚል ሲሆን፥ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮ 11ኛ የተቋቋመበትን 100ኛ ዓመት ያከብራል።

በተለምዶ ከወሩ መጨረሻ እሑድ ቀደም ብሎ ባለው እሑድ ለሚከበረው የተልዕኮ ቀን በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የመረጡት መሪ ጭብጥ ይፋ የተደረገ ሲሆን፥ ዓመታዊ ክብረ በዓሉ የሚከበረው ከጥቅምት ወር የመጨረሻ እሁድ ቀደም ብሎ በሚውለው እሑድ ወይም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ጥቅምት 18 2026 ዓ. ም. እንደሚሆን ታውቋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጥሪ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የዘንድሮውን ዓለም አቀፍ የተልዕኮ እሑድን በማስመልከት ባቀረቡት ጥሪ፥ መላዋ ቤተ ክርስቲያን ለሚስዮናውያን እና ለሐዋርያዊ ሥራዎቻቸው ፍሬያማነት ምዕመናንን በጸሎት ለመሳተፍ ልዩ አጋጣሚ እንደሆነ አፅንዖት ሰጥተው፥ በላቲን አሜሪካ አገር ፔሩ ውስጥ ሚስዮናዊ ካኅን ሆነው በኋላም በጳጳስነት ባገለገሉባቸው ዓመታት ያገኙትን የግል ልምድ በማስታወስ፥ “በዓለም ዓቀፍ የተልዕኮ እሁድ የሚታየው የምዕመናን እምነት፣ ጸሎት እና ልግስና መላውን ማኅበረሰቦች መለወጥ የሚችል መሆኑን በገዛ ራሴ አይቻለሁ” ብለዋል።

የተነሳሽነቶች ሁሉ መሪ

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2026 ዓ. ም. የሚከበረው ዓለም አቀፍ የተልዕኮ እሁድ ዋና ጭብጥ የመጀመሪያው ክፍል፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ለሐዋርያዊ መሪነት እንዲሆን የመረጡትን መሪ ቃል፥ “በአንዱ ክርስቶስ ሁላችንም አንድ ነን” የሚለውን የሚያስታውስ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ከአብ ጋር ባለው አንድነት ላይ የተመሠረተውን የአማኞች የእምነት አንድነትን እና በዚህም የወንጌል ስርጭትን የጋራ ተልዕኮ የሚያጎላ እንደሆነ ታውቋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2026 ዓ. ም. ለሚከበረው ዓለም አቀፍ የተልዕኮ ቀን ዝግጅት ቀጣዩ እርምጃ በዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ወራት ውስጥ የቅዱስነታቸውን መልዕክት ይፋ ማድረግ ሲሆን፥ ይህም በዚህ አስፈላጊ ዓመት ውስጥ በሁሉም ምእመናን መካከል የሚስዮናዊነት መንፈስን እና ኃላፊነትን ለማጎልበት ለታለሙ በርካታ ተነሳሽነቶች መሪ ጭብጥ ሆኖ እንደሚያገለግል ታውቋል።

መላዋ ቤተ ክርስቲያን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2026 ዓ. ም. የምታከብረው “ጳጳሳዊ የሚስዮናዊነት ኅብረት” ምሥረታ 110ኛ ዓመት፥ ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ “ሌሎች ጳጳሳዊ የሚስዮናዊነት ሥራዎች በማለት የእምነት ማስፋፊያ ማኅበር፣ የቅዱስ ልጅነት ማኅበር እና የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ማኅበር በዓል እንደምታከብር ታውቋል።

እነዚህ አራት ማኅበራት እያንዳንዳቸው የራሳቸው ተልዕኮ ያላቸው ሲሆን፥ አገልግሎታቸውም በተጠመቁት መካከል የሚስዮናዊነት ኃላፊነትን ለማስተዋወቅ እና አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናትን ለመደገፍ በጋራ የሚሠሩበት እንደሆነ ታውቋል።

 

03 Nov 2025, 17:16