በቫቲካን የሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ በቫቲካን የሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ  (ANSA)

ቫቲካን የቅድስት መንበር የአስተዳደር እና የዳኝነት ሥርዓት አዳዲስ ደንቦችን ይፋ አደረገ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ “ወንጌልን ስበኩ” በተሰኘው ሐዋርያዊ ድንጋጌ ውስጥ የተቀመጡ ደንቦች ተግባራዊነት የሚያረጋግጡ አዳዲስ የአስተዳደር እና የዳኝነት ሥርዓት ደንቦችን አጽድቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቅድስት መንበር የአስተዳደር እና የዳኝነት ሥርዓት እንዲሁም የተቋማቱ ሠራተኞች ደንቦች የታተሙ ሲሆን በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ፊርማ የጸደቁት የክርስቶስ ንጉሥ በዓል በተከበረበት ሰኞ ኅዳር 15/2018 ዓ. ም. እንደሆነ ታውቋል።

የቅድስት መንበር ደንብ የሚመለከተው ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶችን የሚያዋቅሩ ተቋማትን እና ቢሮዎችን ማለትም የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤትን፣ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶችን፣ የዳኝነት እና የኢኮኖሚ አካላትን እንደሆነ ታውቋል።

አዲስ የወጣው የሠራተኞች ደንብ በጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ውስጥ የሚያገለግሉ ሠራተኞች የሥራ ግንኙነትን በተመለከተ የድርጅት፣ የዲሲፕሊን እና የኢኮኖሚ ባህሪን፣ የቅድስት መንበር የአስተዳደር ጽሕፈት ቤቶችን የሚያዋቅሩ አካላትን እና ቢሮዎችን እንዲሁም ከቅድስት መንበር ጋር የተገናኙ ተቋማትን እንደሚመለከት ታውቋል።

አዲሶቹ ደንቦች በቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ሚያዝያ 15/1999 ዓ. ም. ጸድቆ በተመሳሳይ ዓመት ሐምሌ 1/1999 ዓ. ም. በሥራ ላይ የዋለውን  ደንብ የሚተካ መሆኑ ታውቋል።

አዲሶቹ ደንቦች ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ወንጌልን ስበኩ” በሚል እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በመጋቢት 19/2022 ዓ. ም. ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ ደንብ ውስጥ የጠቀሷቸውን ማሻሻያዎች፣ አዳዲስ ሃሳቦች እና አመላካቾች ያካተቱ እና ተግባራዊ የሚያደርጉ መሆናቸው ታውቋል።

 

25 Nov 2025, 15:30