ቪቪያን ሱተር ከአንዳንድ ሥራዎቿ ጋር ቪቪያን ሱተር ከአንዳንድ ሥራዎቿ ጋር   (© Francesco Gili, courtesy Dicastero per la Cultura e l'Educazione e l'artista)

ታዋቂዋ የጥበብ ሰው ቪቪያን ሱተር እና ከተፈጥሮ ጋር ያላት የማይነጣጠል ትስስር

ታዋቂዋ የጥበብ ሰው ቪቪያን ሱተር ሮም በሚገኘው የእጽዋት እና አትክልት ማዕከል ውስጥ የሥዕል ሥራዎቿን ያቀረበች ሲሆን፥ በዚህ ዝግጅት ላይ ተገኝተው መርሃ ግብሩን ያስጀመሩት የቅድስት መንበር የባህል እና የትምህርት ጽህፈት ቤት ሃላፊ ብፁዕ ካርዲናል ሆሴ ቶለንቲኖ ዴ ሜንዶንሳ “የቪቪያን ሱተር ጠንካራ ጥበባዊ እይታ በቀላሉ አመለካከታችንን ይለውጣል” ማለታቸው ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

“ሥራዎቿ ከተፈጥሮ ጋር ያለን ትስስር የማይነጣጠል መሆኑን ያስታውሰናል” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ሆሴ፥ በዓለም ውስጥ የመኖራችን ትልቁ መሠረት የሆነው ከተፈጥሮ ጋር ያለን ትስስር ራሳችንን አሳልፈን ሳንሰጥ የማይፈርስ ትስስር መሆኑን ያመላክተናል ብለዋል።

ሁለት ቦታዎች ላይ የቀረቡ ሥራዎች
ገላጭ ባህሪ ያላቸው የሱተር ሥራዎች ከተፈጥሮ ጋር ያላትን ትስስር የሚያሳዩ ሲሆን፥ ይህም እሁድ ምሽት ላይ ባቀረበችው ሥራዎቿ ላይ በግልጽ እንደሚታይ የገለጹት በሮም የሳፒየንዛ ዩኒቨርሲቲ ዳይሬክተር የሆኑት አንቶኔላ ፖሊሜኒ ሲሆኑ፥ ከዚህም በተጨማሪ በሁለቱም ማለትም በግዙፉ ግሪን ሃውስ የእፅዋት ማዕከል እና በቪያ ዴላ ኮንሲሊያዚዮን-5 ውስጥ የታዩት አውደ ርዕዮቿ ይሄንኑ እንደሚመሰክሩ ገልጸዋል።

ተፈጥሮ የሥራዎቿ ረዳት ፈጣሪ ሆነዋል
ዳይሬክተሩ እንደተናገሩት የሳፒየንዛ ዩኒቨርሲቲ የሙዚየም ትስስር አንዱ አካል የሆነው ሮም ውስጥ የሚገኘው የእፅዋት ማዕከል የሥነ ተፈጥሮ፣ የብዝሃ ህይወት እና በልዩነት አብሮ የመኖር ተጨባጭ ምሳሌ እንደሆነ ገልጸው፥ ይህ በከተማው እምብርት ላይ ያለው የእፅዋት ማዕከል የሱተርን የሥዕል አውደ ርዕይ ለማስተናገድ ምቹ ቦታ እንደሆነ ገልጸዋል።

ሱተር የማዕከሉ ሃላፊ ከሆነችው ፔሬላ ጋር በነበራት ውይይት ስለ ተፈጥሮ ብቻ ሳይሆን ሥዕል መሳል እንዴት እንደጀመረች የገለጸች ሲሆን፥ ጓቲማላ በሚገኘው የሥዕል መሳያ ስቱዲዮ ውስጥ እየሰራች በነበረበት ወቅት ከዕለታት አንድ ቀን ኃይለኛ አውሎ ነፋስ አንዳንድ የሥዕል ሸራዎቿን በጭቃ ሸፍኖ እንደጣለው እና ጭቃው ሲደርቅ የተፈጠረው አሻራ አስደናቂ እንደነበር አስታውሳ፥ በዛው ይሄንን ሥራ እንደጀመረች ገልፃለች።

ክፍሉን ለቁሳቁሶች መልቀቅ
ይህ ክስተት የጥበብ አካሄዷን እንደቀየረው የተናገረችው ሱተር፥ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቀደም ሲል በቤት ውስጥ ስትሰራው የነበረውን የአሳሳል ዘይቤ በመተው የአየርን፣ የዝናብን፣ የአፈርን፣ የእርጥበትን፣ የውሻዎቿን አሻራዎች፣ የእፅዋት እና የእንስሳት ምልክቶች እና ድምጾች እንኳን ሳይቀሩ ከሸራዎቿ ጋር እንዲገናኙ መፍቀዷን ገልፃለች።

የማዕከሉ ሃላፊ ፔሬላ ለዚህ ምስክርነቷን ስትሰጥ “ሱተር በሥራዋ እና ለመኖር የመረጠችበት መንገድ የአካባቢያችን አካል መሆናችንን ያስታውሰናል” በማለት ገልፃለች።

እርስ በርሱ የሚገናኝ ዓለም
ሞቃታማውን መልክዓ ምድር ለምለም በሚያደርጉ መሳጭ አቀራረቦች የተዘጋጁት የሱተር ስራዎች የሰው ልጅ የሰፊው እና እርስ በርስ የተገናኘ ዓለም አካል መሆኑን ያረጋግጣሉ የተባለ ሲሆን፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ “የጋራ ቤታችንን እንንከባከብ” ብለው በላውዳቶ ሲ ላይ ያስተላለፉትን መልዕክት እንዲሁም “የአካባቢ እና የህብረተሰብ መጎዳት በተለይ በጣም ተጋላጭ የሆኑትን ይጎዳል” ተብሎ በኢዮቤልዩ ዓመት ላይ የተጠቀሰውን “የሥነ-ምህዳር ዕዳ” በቁም ነገር እንድንመለከተው በመጋበዝ ሥነ ምህዳራዊ ስሜትን ያንጸባርቃሉ ተብሏል።

ይህ መጀመሪያ ላይ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ሃዋሪያዊ ደብዳቤ ውስጥ የተገለጸው ሃሳብ፣ በኋላም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ‘ዳይሌክሲ ቴ’ በተባለው ሐዋርያዊ መልዕክታቸው ውስጥ ይሄንን ሃሳብ እንዳስተጋቡት ተገልጿል።

የሱተር ሥራዎች እስከ ታህሳስ 5 ቀን 2018 ዓ.ም. ለህዝብ ክፍት ሆኖ እንደሚቆይም ተነግሯል።

04 Nov 2025, 14:13