ብፁዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግሌ ህዳር 18 ቀን 2018 ዓ.ም. ታላቁ የተስፋ ነጋዲያን ዝግጅት በፔናንግ ከተማ ሲከፈት ለመርሃ ግብሩ የተዘጋጀውን ሻማ ሲያበሩ ብፁዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግሌ ህዳር 18 ቀን 2018 ዓ.ም. ታላቁ የተስፋ ነጋዲያን ዝግጅት በፔናንግ ከተማ ሲከፈት ለመርሃ ግብሩ የተዘጋጀውን ሻማ ሲያበሩ  

ብፁዕ ካርዲናል ታግሌ በፍርሃት ከሚመነጭ አመራር መጠንቀቅ እንደሚገባ አስጠነቀቁ

ብፁዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግሌ ታላቁ የተስፋ ነጋዲያን ዝግጅት በፔናንግ ከተማ ሲከፈት እንደተናገሩት የቤተክርስቲያን መሪዎችን በሄሮድሳዊ አመለካከት ከሚመነጨው የፍርሃት አስተሳሰቦች እንዲቆጠቡ በማስጠንቀቅ፥ የኢስያ ካቶሊኮች የሰብአ ሰገሎችን ትህትና እና ድፍረት መልሰው እንዲላበሱ ጥሪ አቅርበዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግሌ ህዳር 18 ቀን 2018 ዓ.ም. በማሌዥያ ፔናንግ ከተማ ታላቁን የተስፋ ነጋዲያን ዝግጅት ያስጀመሩ ሲሆን፥ ‘ሬዲዮ ቬሪታስ ኤዥያ’ በተባለው የዜና ማሰራጫ ተቋም በቀረበው ዘገባ መሰረት ብፁዕ ካርዲናሉ በክርስቲያናዊ ሕይወት ውስጥ ያሉትን ሁለት መንፈሳዊ ጎዳናዎች በማነፃፀር ከክልሉ የመጡ ልዑካንን ማነጋገራቸውን አመላክቷል።

“በአሁኑ ወቅት እንደ ሰብአ ሰገሎች የሚሹ፣ የሚያዳምጡ፣ የሚማሩ እና የሚሰግዱ በርካታ መንፈሳዊ ነጋዲያን ያስፈልጉናል” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ታግሌ፥ በአንፃሩ በፍርሃት፣ በስልጣን እና በተስፋ መቁረጥ የተጠመዱ ሄሮድሳዊ አመለካከት ያላቸውን ሰዎች መቀነስ ያስፈልጋል ያሉ ሲሆን፥ “ኑ እና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መንፈሳዊ ንግደት ተቀላቀሉ” ሲሉ ለተሳታፊዎች ተናግረዋል።

በሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ የኢስያ አቢያተ ክርስቲያናትን አንድ ላይ የሚያሰባስበው ታላቁ የተስፋው ነጋድያን ዝግጅት የተከፈተው የፔናንግ ጳጳስ በሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ሴባስቲያን ፍራንሲስ መሪነት በተካሄደው በመክፈቻ ስነ ስርዓት እና መስዋዕተ ቅዳሴ እንደሆነ ተነግሯል።

ብፁዕ ካርዲናል ታግሌ “በተለየ መንገድ የሚጓዙ፣ የታደሱ የተስፋ ነጋዲያን” በሚል ጭብጥ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፥ የኢስያ ቤተ ክርስቲያናት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ታሪክ ለመናገር እንዳይታክቱ በማሳሰብ፥ የክርስቲያን ተስፋ ከአዎንታዊ አስተሳሰብ ወይም ከማምለጥ የበለጠ ጥልቅ እንደሆነ አስረድተዋል።

“የክርስቲያን ተስፋ መነሻውን እና ግቡን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገ በእግዚአብሔር የተዋቀረ ሥነ-መለኮታዊ በጎነት ነው” ያሉት ብፁዕ ካርዲናሉ፥ እውነተኛ ተስፋ ጽናትን የሚያጠናክር እና ባልንጀራችንን እንደ እግዚአብሔር ፍቅር እንድንወድ ልባችንን የሚያፀዳ ነው በማለትም አክለዋል።

ብፁዕ ካርዲናሉ ለልዑካኑ ባስተላለፉት መልዕክት እውነተኛ ደስታ የሚሰጠን እና በጽናት እንድንሰራ የሚያደርገን መንገድ ዬትኛው እንደሆነ እና በጎ አድራጎት የሚመራው ለአምላክ መንግሥት ነው ወይስ የራስን ጥቅም ለማስቀደም ነው የሚለውን ጥያቄ እራሳቸውን በመጠየቅ ከመንፈሳዊ ሕይወታቸው በስተጀርባ ያለውን ተነሳሽነት እንዲመረምሩ ጋብዘዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ታግሌ በትህትና እና በፍርሃት መካከል ያለውን ምርጫ ለማሳየት የሰብአ ሰገሎቹን ታሪክ የሚናገረውን የወንጌል ክፍል በማስታወስ፥ ሰብአ ሰገሎች ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያደረጉት መንፈሳዊ ንግደት በትሕትና፣ በግልጽነት እና በብርሃን በመመራት እንደሆነ አስረድተው፥ በአንፃሩ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሌለበት መንፈሳዊ ንግደት በፍርሃት፣ በመቀዛቀዝ እና በዓመፅ የተሞላ ሄሮድሳዊ አካሄድ መሆኑን አብራርተዋል።

ብፁዕ ካርዲናሉ የንጉስ ሄሮድስን ታሪክ በመጥቀስ ስልጣንን ማሳደድ ተቋማትን እና ሰዎችን እንዴት እንደሚያደናቅፍ ያስጠነቀቁ ሲሆን፥ “ኃይል ካለህ ክብደት አለህ፣ ክብደት ካለህ ደግሞ መንቀሳቀስ ከባድ ነው” ካሉ በኋላ፥ የሄሮድስ ሽባነት በአካባቢው ባሉት ሰዎች ላይ ፍርሃትን በማስፋፋቱ “ተላላፊ” ሆኗል በማለት አክለዋል።

በአንጻሩ ደግሞ ሰብአ ሰገል ትሕትናን፣ ውስንነታቸውን እና አቅማቸውን ተቀብለው መመሪያ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን አስረድተው፥ ለመማር ያላቸው ዝግጁነት የሲኖዶሳዊነትን መንፈስ የሚያንፀባርቅ መሆኑን ብፁዕ ካርዲናል ታግሌ ተናግረዋል።

ሰብአ ሰገል እንዴት ለራዕይ ወዲያው ምላሽ እንደሰጡ እና ብዙ ጊዜ እንደ እየሩሳሌም ባሉ የሃይል ማዕከላት በተሸፈነችው ቤተልሔም እንዴት ደስታን እንዳገኙ በመግለጽ፥ “አንዳንድ ጊዜ ችላ ብለን በምናያቸው ትናንሽ ማህበረሰቦች ውስጥ ብዙ ጥበብ እና ደስታ አለ” ሲሉ ተናግረዋል።

ሄሮድስ በበኩሉ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መወለድ በረብሻ እና በዓመፅ ምላሽ በመስጠት የሌሎችን ደስታ መቀበል አለመቻሉን ያስታወሱት ብፁዕ ካርዲናል ታግሌ፥ “ተስፋ የሌላቸው ሰዎች ደስተኛ አይደሉም” ብለዋል።

በቅርቡ ባደረጉት የውጭ ሀገር ጉብኝት የጠፉበትን ታሪክ በማስታወስ፣ በወቅቱ የተከሰተው ስህተት ፀሎት እና ችግሮቻቸውን ለማካፈል ወደሚፈለጉ ሁለት የፊሊፒንስ ስደተኛ ሰራተኞችን እንዲያገኙ እንደመራቸው በመጥቀስ፥ ነገር ግን ከጊዜ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚያ መንገድ ሆን ብሎ እንደመራቸው እና እንዳልጠፉ መገንዘባቸውን ገልጸዋል።

የክርስትና ሕይወት ልብ ምንጊዜም በክርስቶስ የተቀረጸ ጉዞ እንደሆነ ልዑካኑን ያስታወሱት ብፁዕ ካርዲናል ታግሌ፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተለየ መንገድ እንደሚወስድ ጠቅሰው፥ በመጨረሻም “እርሱ መንገድ፣ እውነት እና ሕይወት ነው፥ እርሱ ኮከባችን፣ ግባችን፣ ተስፋችን ነው” በማለት አጠቃለዋል።

03 Dec 2025, 13:15