በአሲሲ በሚገኘው የቅዱስ ፍራንቺስኮ ገዳም እና ጳጳሳዊ ካቴድራል የታችኛው ክፍል ውስጥ የቅዱስ ፍራንቺስኮን ቅሪተ አካል ለመጎብኘት በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ መንፈሳዊ ነጋዲያን   በአሲሲ በሚገኘው የቅዱስ ፍራንቺስኮ ገዳም እና ጳጳሳዊ ካቴድራል የታችኛው ክፍል ውስጥ የቅዱስ ፍራንቺስኮን ቅሪተ አካል ለመጎብኘት በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ መንፈሳዊ ነጋዲያን   (ANSA)

በሺዎች የሚቆጠሩ መንፈሳዊ ነጋዲያን የቅዱስ ፍራንቺስኮስን ቅሪት ለማክበር ወደ አሲሲ መጓዛቸው ተነገረ

በሺዎች የሚቆጠሩ መንፈሳዊ ነጋዲያን ከ800 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለምዕመናን ክብር ይፋ የተደረጉትን የአሲሲውን የቅዱስ ፍራንቺስኮስን ዋና ቅሪተ አካል ለመጎብኘት ወደ ከተማዋ መግባታቸው ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

18,000 የሚጠጉ ከዓለም ዙሪያ የተውጣጡ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና ጎብኚዎች እሁድ የካቲት 15 ቀን 2018 ዓ.ም. የአሲሲውን የቅዱስ ፍራንቺስኮስን ቅሪተ አካል የጎበኙ ሲሆን፥ ጎብኚዎቹ በቤተክርስቲያኗ ታሪክ ውስጥ ካሉት እጅግ ተወዳጅ ቅዱሳን ውስጥ አንዱ የሆነውን የቅዱስ ፍራንቺስኮስን ዋና ቅሪት ለማክበር ከዚህ ቀደም ተደርጎ የማይታወቅ አጋጣሚ ማግኘታቸውም ተገልጿል።

የቅዱስ ፍራንቺስኮስ አጽም በትውልድ ከተማው ለእርሱ በተዘጋጀው ባዚሊካ ውስጥ ለአንድ ወር ያክል ለሕዝብ እንደሚታይ የተገለጸው፥ በ 8 ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሃገሬው ህዝብ ዘንድ “ፖቨሬሎ” ወይም ‘ትንሹ የአሲሲ ድሀ ሰው’ ተብሎ የሚታወቀውን የቅዱስ ፍራንቺስኮስ ሞት መታሰቢያ መርሃ ግብር አካል በማድረግ እንደሆነ ተነግሯል።

እ.አ.አ. በ 1230 የቅዱሱ አካል በባዚሊካው የውስጠኛው ክፍል ውስጥ ከገባ በኋላ ቅሪተ አካሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ እንደሚታይ የተገለጸ ሲሆን፥ ይህ መርሃግብር የሚከናወነው ከየካቲት 15 እስከ መጋቢት 13 ድረስ ለአንድ ወር ብቻ እንደሆነ ተገልጿል።

የማሰላሰል እና የደስታ ድባብ
የፍራንቺስካዊያን ካህን የሆኑት አባ ጁሊዮ ሴሳሪዮ ይሄንን ጉዳይ አስመልክተው እንደተናገሩት የቅዱስ ፍራንቺስኮስን ቅሪተ አካል ለማየት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አሲሲ የመጡት በሺዎች የሚቆጠሩ መንፈሳዊ ነጋዲያን የቅዱሱን አካል ለማክበር ወደ ስፍራው በደረሱበት ወቅት ልዩ የሆነ የማሰላሰል እና የደስታ ስሜት ውስጥ እንደሚገቡ አስታውሰው፥ ጎብኚዎቹ እድገትን የሚደግፍ እና የሚያበረታታ መልካም ቃላትን ቅዱሱ በልባቸው ሲያንሾካሹክ እንደሚሰሙ መናገራቸውን ገልጸዋል።

የአሲሲ ቅዱስ ገዳም የኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር የሆኑት አባ ሴሳሪዮ ፍራንቺስኮስን ለሚወዱ እና ይህ ዝግጅት እውነተኛ የወንድማማችነት ጊዜ እንዲሆን ከገዳሙ ጋር በመተባበር ለሰሩ በሙሉ ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

‘ከዓለም አመክንዮ’ ነፃ መውጣት
ቅሪተ አካሉ ለህዝብ ይፋ የተደረገበት የመጀመርያው ቀን በልዩ ሁኔታ የተከበረ ሲሆን፥ ዕለቱ በአሲሲ ጳጳሳዊ ቤተ ክርስቲያን የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል አንጄል ፈርናንዴዝ በተመራ መስዋዕተ ቅዳሴ መከበሩ ተነግሯል።

ብፁዕ ካርዲናሉ በመስዋዕተ ቅዳሴው ወቅት ባሰሙት ቃለ ምዕዳን የአሲሲው ቅዱስ ፍራንቺስኮ “ከዓለም አመክኖያዊ አስተሳሰብ” ነፃ የመውጣት መንፈስን የተላበሰ መሆኑን ገልጸው፣ ሀብትን የማይፈልግ ነገር ግን ራሱን ለእግዚአብሔር አደራ የሚሰጥ፣ ለማገልገል እንጂ የበላይነትን የማይፈልግ እንደነበረ ገልጸዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ፈርናንዴዝ አክለውም ይህንን መንፈስ መቀበል ማለት ያለፈውን መካድ ማለት ሳይሆን፥ ይልቁንም አሁን የሚገጥሙንን ፈተናዎች አጥብቆ መጋፈጥ ማለት እንደሆነ አስረድተዋል።

በቅድስት መንበር የገዳማዊያን ሕይወት እና ሐዋርያዊ ሕይወት ማኅበራት ጽህፈት ቤት ሃላፊው በሥርዓተ ቅዳሴው ወቅት ከተሰሙት የወንጌል ንባባት በመነሳት ባደረጉት አስተንትኖ በተያዘው የዐቢይ ጾም ወቅት ምዕመናን ራሳቸውን ከመጥፎ ነገር እንዲጠይቁ በመጋበዝ፥ ከዓለማዊ አመክንዮ ነፃ በመውጣት እግዚአብሔርን በመታዘዝ አመክንዮ መሠረት መኖር እንደሚገባ አሳስበዋል።

ፈተናን ድል ማድረግ
ብፁዕ ካርዲናል ፈርናንዴዝ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድረ በዳ በሴይጣን የተፈተነበትን የሚገልጽ የወንጌል ክፍል በማስታወስ ቅዱስ ፍራንቺስኮ ተመሳሳይ ፈተናዎች ገጥሞት እንደነበር ገልጸው፥ ነገር ግን በኩራት፣ በሀብት ክምችት እና እራስን በመቻል ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ትንሽነትን፣ ድህነትን እና ታዛዥነትን መምረጡን እንዲሁም፥ እግዚአብሔርን ብቻ ማምለክን እንደመረጠ አስረድተዋል።

“በፈተና ላይ የምንቀናጀው ድል ለሌሎች ሰዎች ክፍት እንድንሆን እንጂ በራሳችን ላይ እንድንዘጋ ፈጽሞ አያደርግም” ያሉት ብፁዕ ካርዲናሉ፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚያሔር መንግሥትን ለማወጅ በረሃ እንደወጣ እና ፍራንቺስኮ በበኩሉ የጌታን አምሳያ በመከተል ፈተናውን በማሸነፍ የሥጋ ደዌ በሽተኞችን እንዲሁም ሁሉንም ወንድሞቹን እና እህቶቹን መቀበሉን አመልክተዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ፈርናንዴዝ በመጨረሻም የቅዱሳት መጻሕፍት ምንባቦችን እና የቅዱስ ፍራንቺስኮን ቅሪተ አካል ማክበር መካከል ያለውን ትስስር ሲያብራሩ ይህ ድርጊት ዝም ብሎ የማስታወስ ተግባር ብቻ እንዳልሆነ ገልጸው፥ ከዚህም ይልቅ እራሳችንን “ደካማ ጎኔ የቱ ጋር ነው? በውስጤ ምን አይነት ፈተና ይኖራል? ጌታ በእምነት እንድኖር የሚጠይቀኝ የቱ ጋር ነው?” የሚሉትን ጥያቄዎች እንድንጠይቅ የተደረገልን ጠንካራ እና ተጨባጭ ግብዣ እንደሆነ በማስረዳት አጠቃለዋል።

24 Feb 2026, 13:30