የሊባኖስ የህይወት አድን ሰራተኞች መጋቢት 30 ቤይሩት በሚገኝ ህንፃ ላይ ያነጣጠረ የእስራኤል የአየር ጥቃት በደረሰበት ቦታ ላይ ያለውን ፍርስራሽ  ሲያፀዱ የሊባኖስ የህይወት አድን ሰራተኞች መጋቢት 30 ቤይሩት በሚገኝ ህንፃ ላይ ያነጣጠረ የእስራኤል የአየር ጥቃት በደረሰበት ቦታ ላይ ያለውን ፍርስራሽ ሲያፀዱ  (AFP or licensors)

በሊባኖስ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ተወካይ ‘ሊባኖስ ሰላም ይገባታል’ ማለታቸው ተነገረ

በሊባኖስ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ተወካይ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ፓኦሎ ቦርጊያ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እስራኤል በሀገሪቱ ላይ እየወሰደች ያለውን ጥቃት ተከትሎ በደረሰው ሞትና ውድመት እጅግ ማዘናቸውን ገልጸው፥ ሰላምን ለማስፈን ውይይት እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በሊባኖስ የሚገኙት ሊቀ ጳጳስ ፓኦሎ ቦርጂያ ረቡዕ መጋቢት 30 ቀን 2018 ዓ.ም. ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በዕለቱ በአስር ደቂቃ ውስጥ 10 የሚጠጉ ጥቃቶች በአንድ ጊዜ መደረጋቸውን በማስታወስ ‘እንዲህ ያለ ጥቃት ፈጽሞ ተደርጎ እንደማይታወቅ’ ጠቁመው፥ በዚህም ጥቃት በርካታ ቁጥር ያላቸው የእስራኤል የጦር አውሮፕላኖች ጥቅም ላይ መዋላቸውን ያስታወሱ ሲሆን፥ ከስፍራው የሚወጡ መረጃዎች 50 ያክል ሰዎች መሞታቸውን ቢዘግቡም ብፁዕነታቸው በርካታ ሰዎች አሁንም ድረስ በፍርስራሹ ውስጥ ሊሆኑ እንደሚችሉ በማስታወስ፥ በጥቃቱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከተገለጸው በላይ ሊሆን እንደሚችል አመላክተዋል።

ረቡዕ ዕለት እስራኤል በሊባኖስ ላይ ባደረሰችው የአየር ድብደባ ቢያንስ 182 ሰዎች መሞታቸው እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መቁሰላቸው የተነገረ ሲሆን፥ በዩናይትድ ስቴትስ፣ እስራኤል እና ኢራን መካከል ለሁለት ሳምንታት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት መደረጉ መጋቢት 26 ቀን 2018 ዓ.ም. ቢታወጅም፥ እስራኤል ግን በሊባኖስ ውስጥ በሚንቀሳቀሰው የሂዝቦላህ ታጣቂ ቡድን ላይ የምታደርገውን ጥቃት እንደማታቆም ገልፃለች።

ሊቀ ጳጳስ ቦርጂያ ከማሮናይት ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ቤቻራ ቡትሮስ ራኢ ጋር በመሆን ከ10 ሰዓታት በላይ በሃገሪቱ ደቡባዊ ምሥራቅ አካባቢዎች በመዞር ለሁሉም የሃይማኖት ተከታዮች የእርዳታ እና የአብሮነት ድጋፋቸውን ሲያደርጉ እንደነበር ተገልጿል።

ሊቀ ጳጳስ ቦርጂያ ከቫቲካን ዜና ጋር በስልክ ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት በእነዚህ አከባቢዎች ውስጥ ሲዞሩ በነበረበት ወቅት ተስፋን ለሌሎች ለማድረስ እና ህይወትን ለማስቀጠል የተደረገ ተልዕኮ ስለሆነ “ምንም እንዳልደከማቸው” በአጽንዖት ገልጸዋል።

ሊቀ ጳጳስ ቦርጂያ በጉብኝታቸው ወቅት ቀኑን ሙሉ በሂዝቦላህ እና በእስራኤል መካከል በተፈጠረው ግጭት ምክንያት በሞርታር ተኩስ ታጅበው እንደነበር አስታውሰው፥ እርሳቸው በስፍራው በነበሩበት ወቅት በቤይሩት ከተማ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ መኖሩን፣ ከተማዋ በሳይረን እና በአምቡላንስ ድምፆች መጨናነቋን እና ውዥንብር ውስጥ እንደነበረች ገልጸዋል።

የእስራኤል ወረራ አሁንም ድረስ ተጠናክሮ መቀጠሉን የጠቆሙት ሊቀ ጳጳሱ፥ እንደ እስራኤላውያን መገናኛ ብዙሃን ዘገባ ከሆነ በዚህ ሁኔታ ጥቃቱ ለ48 ሰዓታት ይቀጥላል ተብሎ እንደሚጠበቅ እና በዚህም ምክንያት ሁኔታው እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ አመላክተው ነበር።

ይህ ሁሉ የሆነው የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ማክሰኞ ዕለት በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ለሁለት ሳምንታት የሚቆየውን የእርቅ ስምምነት እንደሚደግፉ እና ሊባኖስን ግን እንደማያካትት ካስታወቁ በኋላ መሆኑ ይህ ምን እንደሚያመላክት የተጠየቁት ሊቀ ጳጳሱ፥ እነዚህ ነገሮች የሚያገናኛቸው ነገር ቢኖርም ሁለት የተለያዩ ሁኔታዎች መሆናቸውን እንደተረዱ ጠቅሰው፥ በአንድ በኩል ኢራን ከሂዝቦላህ ጋር ግንኙነት እንዳላት እና በሌላ በኩል ደግሞ ሂዝቦላህ በእስራኤል ዘንድ እንደጠላት እንደሚታይ ገልጸው፥ ይሁን እንጂ እዚህ የተኩስ አቁም ስምምነት መደረጉ እና ከእስራኤል ጋር በተያያዘ ሊባኖስን ለማረጋጋት ድርድር መጀመሩ በጣም ጥሩ ጅማሮ እንደሆነ አስረድተዋል።

የግጭቱ ሁኔታ ቀላል እንዳልሆነ እና መከፋፈልን፣ ሞትን እና ውድመትን እንደሚያስፋፋ የተናገሩት ሊቀ ጳጳሱ፥ እንደሚታወቀው እስራኤል ሂዝቦላን ትጥቅ ለማስፈታት እንደምትፈልግ እና ይህ ዓላማዋ ግን ሊሳካ እንዳልቻለ አስታውሰዋል።

እውነተኛ እርቅ የዲፕሎማሲን በር ዳግም እንደሚከፍት የገለጹት ሊቀ ጳጳሱ፥ ከዚህም በተጨማሪ የሊባኖስ ባለስልጣናት፥ በተለይ የሪፐብሊኩ ፕሬዝዳንት፥ ተጠናክሮ ለቀጠለው ጦርነት መፍትሄ ለመፈለግ ከእስራኤል ጋር ቀጥተኛ ድርድር እንዲደረግ ደጋግመው መጠየቃቸውን ገልጸዋል።

ያም ሆነ ይህ የሰላም መንገዱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ መጋቢት 6 ቀን 2018 ዓ.ም. በተደረገው የመልአከ ሰላም ጸሎት ወቅት የሀገሪቱ ባለስልጣናት ለመላው የሊባኖስ ህዝቦች የጋራ ጥቅም በአሁኑ ጊዜ እየተፈጠረ ላለው ከባድ ቀውስ ዘላቂ መፍትሄዎችን ተግባራዊ ለማድረግ የሀገሪቱን ባለስልጣናት ሊደግፉ የሚችሉ “የውይይት መንገዶችን” እንዲከተሉ ለተደራዳሪ ወገኖች ባቀረቡት ጥሪ ላይ እንደሚያርፍ ጠቁመዋል።

ለሃገሪቱ ምን ዓይነት መፍትሄ ሊኖር እንደሚችል የተጠየቁት ሊቀ ጳጳስ ፓውሎ፥ ጦርነት ውድመትን፣ ሞትን፣ በርካታ ተፈናቃዮችን እና ብዙ አሳዛኝ እና አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እንደሚያስከትል አስታውሰው፥ ምንም እንኳን በቀላሉ የማይገኙ በሚመስሉበት ጊዜም እንኳን ቢሆን ሰላምን ለማስፈን እና መፍትሄዎችን ለማግኘት ሁልጊዜ ተባብሮ መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ጦርነት ትክክለኛው መንገድ እንዳልሆነ ሁሉም ሰው ሊገነዘበው እንደሚገባ እና የተለየ አካሄድ መከተል እና ምክንያታዊ የሆነ መፍትሄ መፈለግ እንዳለበት አመላክተዋል።

ሊቀ ጳጳሱ ሊባኖስ በጣም ብዙ ጦርነቶችን እንዳስተናገደች አስታውሰው፥ ሆኖም የአሁኑ በጣም ጨለማው ጊዜ መሆኑን እርግጠኛ እንዳልሆኑ እና እያንዳንዱ ሰዓት አስቸጋሪ፣ የተለያዩ ሰዎችን እና ሁኔታዎችን እንዳካተተ የጠቆሙ ሲሆን፥ እያንዳንዱ ጦርነት በራሱ ልዩ ባህሪ እንዳለው፥ ነገር ግን ሁሉም ጦርነቶች ስቃይ እና ጥፋትን እንደሚያስፋፉ አስታውሰው፥ ሊባኖስ ከ 50 ዓመታት በላይ በጦርነት ውስጥ እንደኖረች የሚገነዘብ አንድ ሰው የአሁኑ ጦርነት የጨለማ ጊዜ ነው ወይም አይደለም ማለት የሚችል አይመስለኝም ብለዋል።

በቅርብ ቀናት ውስጥ ባደረጉት የሰብዓዊ ተልዕኮዎች ወቅት በሃገሪቱ ደቡባዊ ክፍል የሚገኙ በርካታ መንደሮችን እና ማህበረሰቦችን መጎብኘታቸውን ተከትሎ የአከባቢው ሰዎች ምን እንደነገሯቸው እና ምን ዓይነት ተስፋ እንደሚያደርጉ የተጠየቁት ሊቀ ጳጳሱ፥ በቤይሩት አካባቢ የተፈናቀሉ ወገኖች በተለይም የሺዓ ሙስሊሞች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ጠቁመው፥ ከዚህም በተጨማሪ በቤሩትም ሆነ በሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል በርካታ ክርስቲያኖች መፈናቀላቸውን ብሎም ትልቅ የኢኮኖሚ ችግር መኖሩን አስታውሰዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በህዝቡ ዘንድ የመረሳት ስሜት እንዲሁም ዘመዶቻቸው ወይም ጓደኞቻቸው ጋር የተጠለሉ ሰዎች የሚሰማቸው ጥልቅ የመረበሽ ስሜት መኖሩን ያመለከቱት ሊቀ ጳጳሱ፥ በደቡባዊ መንደሮች ውስጥ የቀሩት ሰዎች ከመሬታቸው እና ከአከባቢያቸው ጋር ጠንካራ ትስስር ስላላቸው ጥቃቱ ቢኖርም እዚያው ለመቆየት ቢወስኑም፥ ነገር ግን ስለመጪው ጊዜ እርግጠኛ እንዳልሆኑ እና እንደሚያስጨንቃቸው እንዲሁም ባጋጠማቸው የመገለል ሁኔታ የተነሳ የብቸኝነት ስሜት ስለሚሰማቸው የትም ለመሄድ እንዳልቻሉ ገልጸዋል።

“የአከባቢው ሰዎች ብቸኝነት ስለሚሰማቸው በተቻለን አቅም እነሱን ለመጎብኘት እንሞክራለን” ያሉት ሊቀ ጳጳሱ፥ የዓለም አቀፉ እና የሊባኖስ ቤተ ክርስቲያን አጋርነት በተለይም የቅዱስ አባታችን መገኘት እንዲሁም በእነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ የሚኖሩትን ሰዎች የሚያግዙ እና የሚደግፉ በርካታ በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች ከእነሱ መሆናቸው እንዲሰማቸው ዘወትር እንደሚጎበኟቸው አስረድተዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ለደበል ክርስቲያኖች የትንሳኤ በዓል መልዕክት ማስተላለፋቸውን እና ትንሳኤውን የተስፋ ምንጭ አድርገው እንዲመለከቱት እና ጥንካሬ እንዲኖራቸው ማሳሰባቸውን አስመልክቶ ያላቸውን ሃሳብ የተጠየቁት የቅድስት መንበር ተወካዩ፥ እነዚህ ቃላት ለክርስቲያኖች፣ በእውነት ትክክለኛ በሆነ መንገድ ጥልቅ የሆነ መልዕክት እንደሚያስተጋቡ ገልጸው፥ ሊባኖሳዊያን በጣም ሃይማኖተኛ በመሆናቸው መጠን በአሁኑ ወቅት ወደ ትንሳኤ መመልከት እንደሚገባ እና ፋሲካን ማክበር የክርስትና እምነታቸው እጅግ አስፈላጊው አካል መሆኑን ተናግረዋል።

“አሁንም በእነዚህ የህማማት ቀናት ውስጥ እየኖርን ያለ ቢመስልም፥ ነገር ግን ሁልጊዜ በትንሳኤው ላይ፣ እንዲሁም በሚያድነን እና አዲስ ህይወት በሚሰጠን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ዓይኖቻችንን እናተኩራለን” ያሉት ሊቀ ጳጳሱ፥ ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎችም የቅዱስ አባታችንን በተለይም ስለ ሰላም የተናገሩትን ቃላት በእጅጉ እንደሚያደንቁ እና በጦርነት ለተጎዱ ሰዎች ያላቸውን አሳቢነትም ጭምር እንደሚያደንቁ አስታውሰዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ማክሰኞ ዕለት በካስቴል ጋንዶልፎ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ዩናይትድ ስቴትስን አስመልክተው እንደተናገሩት ህዝቡ ሰላምን እንጂ ጦርነትን እንደማይፈልግ ለማስገንዘብ ከኮንግረሱ አባላት ወይም ከሌሎች ባለስልጣናት እና ፖለቲከኞች ጋር ተገናኝተው እንዲወያዩ ጥሪ ማቅረባቸውን በማስመልከት ያላቸውን ሃሳብ ተጠይቀው ሲመልሱ፥ በእርግጥ ይህ ጥሪ ሂዝቦላንም ሆነ እስራኤልን ጨምሮ ለሁሉም ሰው የሚጠቅም ግብዣ እንደሆነ ጠቅሰው፥ ችግሮችን ለመፍታት፣ መንገዶችን ለመፈለግ እና በሊባኖስ ውስጥ የሰላም እና አዲስ የሕይወት ጎዳና ለመክፈት ሀገሪቱ የምትፈልገው እና የሚገባት ነገር መሆኑን አመላክተዋል።

በአካል ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊ ሁኔታም ቢሆን ድካም ይሰማቸው እንደሆን የተጠየቁት ሊቀ ጳጳስ ፓውሎ፥ አንድ ሰውም ቢሆን በተስፋ እና በሕይወት መቆየት ስላለበት በፍጹም ድካም እንዳልተሰማቸው ገልጸው፥ ይሄንን ካላደረጉ የሌሎችን ተስፋ ማቆየት እንደማይቻል ተናግረዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አስራ አራተኛ ቀጣይነት ያለው የሰላም ጸሎት እንዲደረግ ማሳሰባቸውን አስመልክቶ ሃሳባቸውን ያካፈሉት ሊቀ ጳጳሱ፥ ሊባኖስ ብዝሃነት ያለባት እና በንፅፅር የተሞላች ሃገር ስለሆነች ሁሌም ፈታኝ የሆነ ነገር እንደማይጠፋባት አስታውሰው፥ ሰላም እንዲሰፍን፣ ሰዎችም ተረጋግተው እና በሰላም እንዲኖሩ የብፁዕነታቸው ጥሪ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን የጠቀሱ ሲሆን፥ ተግዳሮቱ የዚህች ሀገር መልካም ገጽታ እንዲገለጥ ሁሉንም ነገር በአንድ ላይ ማሰባሰብ እንደሆነ አመላክተዋል።

“ሁሉም ሰው የሰላምን አስፈላጊነት ይገነዘባል” ያሉት ሊቀ ጳጳስ ፓውሎ፥ በመጨረሻም፥ ሰላም መሸነፍ ሳይሆን፣ ከዚህም ይልቅ ከእግዚአብሔር የሆነ መልካም ነገር መሆኑን አስረድተው፥ ሰላምን መፈለግ በሁኔታዎች ፊት እጅ መስጠት ሳይሆን፥ ፍትሃዊነትን ለማስፈን በእርቅ መንገድ ራስን ለቀጣይ ሕይወት ክፍት ለማድረግ እድል የሚሰጥ ነገር መሆኑን በማስረዳት አጠቃለዋል።

15 Apr 2026, 14:31