ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን   (© Archdiocese of Malta)

ካርዲናል ፓሮሊን፥ ለሰላም የሚወተውቱ ተጨማሪ ድምጾች ያስፈልጉናል ሲሉ ተናገሩ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን 'ዲያሎጊ' ከተሰኘ የጣሊያን መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ የዲፕሎማሲ ደካማነት፣ የገናና መንግሥት መነሳሳት አመክኖ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስፈላጊነት እና የኑክሌር ጦር መሣሪያዎች ማስቀረት አስፈላጊነት በማስመልከት በተነሱ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ሰላም በዓለም አቀፍ ስምምነቶች ሳይሆን በከባድ የጦር መሣሪያ ትጥቅ እና በኃይል ሚዛን መብለጥ ይረጋገጣል ብሎ ማሰብ ፍጹማዊነት ነው” ሲሉ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን “ዲያሎጊ” ከተሰኘ የጣሊያን “ካቶሊክ አክሽን” መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረው፥ የጦር መሣሪያ መልሶ ግንባታን በጥብቅ አውግዘዋል።

“ከኑክሌር የጦር መሣሪያዎች ጀምሮ የጦር መሣሪያዎች በሙሉ መወገድ እንዳለባቸው አጥብቀን እናምናለን” ሲሉ በአፅንዖት የተናገሩት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ የአቶሚክ ጦር መሣሪያዎችን ቀስ በቀስ ለመቀነስ በሚል የተደረጉ ስምምነቶችን ማደስ አለመቻሉን አስታውሰው፥ “ይህም በምድር ላይ ሕይወትን ለማጥፋት የሚችሉ ገዳይ የጦር መሣሪያዎችን ለመገንባት የበለጠ ነፃነት ሰጥቷል” ብለዋል።

“ለሰላም የሚወተውቱ የተጨማሪ ድምጾች ፍላጎት አለ” ያሉት ብጹዕነታቸው፥ የጦር መሣሪያ ውድድርን የሚቃወሙ ተጨማሪ ድምጾች ያስፈልጋሉ” ሲሉ አጥብቀው አሳስበው፥ “ለድሆች ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን የሚጮሁ ተጨማሪ ድምጾች እና ሃሳቦች፥ ለምሳሌ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲዎች እና በፍትህ እና ለአቅመ ደካሞች በሚደረግ እንክብካቤ የተነሳሱ አዳዲስ የኢኮኖሚ ሞዴሎች እንዲኖሩ እንፈልጋለን” ብለዋል።

የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት የፈጠረው “ቁስል”

“በሁሉም ሰው ዘንድ የሰብዓዊነት እና የኃላፊነት መጨመር ፍላጎት አለ” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ቀጥለውም፥ “በብዙ አጋጣሚዎች እንደታየው፥ ለዚህ ብቸኛው ምላሽ የጦር መሣሪያ ግንባታን መልሶ ማሳደግ መሆኑ ያሳዝናል” ብለዋል።

የተባበሩት የአውሮፓ አገራትን ለማየት ሕልም የነበራቸው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ተስፋን በማስታወስ፥ “ዓለም ነፃ እና የበለጠ አንድነት ያለው ከመሆን ይልቅ ወደ ሌላ አቅጣጫ ሄዷል” ያሉት ካርዲናል ፓሮሊን፥ “በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብ፣ በጥማት፣ በአነስተኛ የጤና አጠባበቅ እጦት እና በሚያዋርዱ የሥራ ሁኔታዎች እንዲሰቃዩ የሚያደርጉ አስከፊ እና ኢ-ፍትሃዊ ድርጊቶች ብቅ ማለታቸውን አይተናል” ብለዋል።

የክርስትና አኅጉር እንደሆነች በምትታመን የአውሮፓ እምብርት ላይ የተከሰተውን የዩክሬን ጦርነት ያስታወሱት ብጹዕነታቸው፥ ከፍተኛ የሰው ሕይወት መጥፋት፣ የከተሞች እና የመሠረተ ልማት ውድመት የታየበት የዩክሬን ጦርነት በአገሪቱ ላይ ያስከተለው አደጋ በበቂ ሁኔታ ግንዛቤን እንዳላገኘ ይሰማኛል” ብለዋል።

የስልጣን የበላይነት

የዩክሬን እና የጋዛን ጦርነት ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ ብዙ መንግሥታት የሩስያ ሚሳኤሎች እና ድሮኖች በዩክሬን ሲቪሎች ላይ በፈጸሙት ጥቃቶች ቁጣቸውን እንደገለጹ ማዕቀብም እንደጣሉ ገልጸው ነገር ግን በጋዛ ውድመት አሳዛኝ ሁኔታ ተመሳሳይ ነገር የተደረገ አይመስልም” ብለዋል።

ከስልጣን የበላይነት ጋር የተያያዘ የሁለት ደረጃዎች አጠቃቀም ዘዴ፥ በሌሎች ላይ የበላይነትን ማሳየት፣ በዓለም አቀፍ ሕግ የተረጋገጠ እና ምቹ በሚሆንበት ጊዜ ብቻ የሚሰራ ካልሆነ ግን በሌሎች ብዙ ጉዳዮች ችላ የተባለለት ይመስላል” ብለዋል።

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊው እንደሚሉት፥ ዝምታን የመረጠው እና ሌሎች አማራጭ መንገዶችን መጠቀም የማይችል የሚመስል ዲፕሎማሲ “በኃይል ሚዛን መብለጥ” በሚለው አመክንዮ የተተካ እና የሰላምን ዋጋ፣ የጦርነት አሳዛኝ ሁኔታ እና የጋራ ሕጎችን አስፈላጊነት እና እነርሱን ማክበር ግንዛቤን ያጣ ይመስላል” ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት እና የሰላም ቦርድ

“ዲፕሎማሲ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ጥበብ ነው” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ “ከላይ በተቀመጡት ወይም ረቂቅ አስተምህሮዎች ላይ በተመሠረቱ ቀድሞ በተቋቋሙ እቅዶች መሠረት ፈጽሞ ሊሠራ አይችልም” ሲሉ አስረድተው፥ አንዳንድ ጊዜ አስፈሪ ቢሆንም ከእውነታው መጀመር እንዳለበት እና ሊደረስባቸው ለሚችሉ ውጤቶች ትዕግስት እና ትኩረት እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን በተመለከተ፥ “ቅድስት መንበር በአስፈላጊነቱ ማመንዋን ቀጥላለች” ብለው፥ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች “በኃይል ሚዛን የሚበልጥ” የሚለውን አመክንዮ ለመግታት አስፈላጊ እንደሆኑ ገልጸው፥ “ከሕግ ኃይል ወደ የኃይል ሕግ” መሄድ አስፈላጊ እንዳልሆነ አክለው ገልጸዋል።

ቅድስት መንበር የሰላም ቦርዱን እንዳልተቀላቀለች የገለጹት ብጹዕነታቸው፥ ከተሳታፊ አገሮች ጋር የሚደረገውን ውይይት ክፍት ማድረጉን እና ከቅድስት ምድር ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጋር በቅርበት በመተባበር ለሰላም እና ለመልሶ ግንባታ የሚቻለውን ሁሉ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆኑን አስረድተዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ድምፅ መደገፍ

በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ድምፅ ላይ ያሰላሰሉት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ በችግር ወቅት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ድምጽ ድጋፍ ካላገኘ፥ ሰሚ የሌለው የበረሃ ውስጥ ድምፅ ይሆናል” ብለዋል።

የትራምፕ አስተዳደር ሃይማኖታዊ እሴቶችን በማስመልከት ያቀረበው ጥሪ የተወሰኑ አለመጣጣሞች እንዳሉት ጠቁመው፥ የክርስትና እምነት ገዢው ሊመርጣቸው የሚችላቸው የተለያዩ ምርቶች ማሳያ ዓይነት እንዳልሆኑ ገልጸው፥ “በባሕር ላይ የሚሞቱ ስደተኞች ሕይወትም ሕይወት መሆኑን ሳናውቅ ስለ ፅንስ ብቻ እያሰብን ሕይወትን እንደምንወድ እና እንደምንከላከል መናገር አንችልም” ብለዋል።

በቬነዙዌላ ላይ የተከሰተውን ያስታወሱት ብጹዕነታቸው፥ ቅድስት መንበር ደም መፋሰስን የሚያስወግድ መፍትሄ ለማግኘት ቀደም ሲል ያደረገችውን ጥረት አስታውሰው፥ “የተከሰተው ነገር ምንም ይሁን ምን፣ እንዴት እንደተከሰተ፣ ነገር ግን ሰላማዊ መፍትሄን መደገፋችንን እንቀጥላለን፣ የአገሪቱ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብትን እና የቬንዙዌላ ሕዝብ ጥቅም እንዲከበር እንጠይቃለን” ብለዋል።

ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ግሪንላንድን ለመጠቅለል ካስፈራሩ በኋላ የዴንማርክ መንግሥት እና የግሪንላንድ ራስ ገዝ መንግሥት ከአሜሪካ መንግሥት ጋር ለመግባባት ያደረጉትን የጋራ ጥረት አድንቀው፥ “የተከሰተው ነገር የግሪንላንድ ሕዝብ ስለ ማንነቱ አዲስ ግንዛቤ እንዲያገኝ አድርጓል” ብለዋል።

ኢራንን በተመለከተ የሰብአዊ መብቶችን እና የሕዝቡን ጥያቄዎች ማክበር አስፈላጊ መሆኑን በድጋሚ ተናግረው፥ “ውይይትን እና ሰላምን በትዕግስት ማሳደግ ይገባል” ብለዋል።

ስለ ቻይና የተጠየቁት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ “ችግሮቹ ቢኖሩም ውይይቱ ይቀጥላል” ብለው፥ እንደገና “እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በመስከረም ወር 2018 ዓ. ም. የተፈረመው ጊዜያዊ ስምምነት የፖለቲካ ወይም የዲፕሎማሲ ስምምነት ሳይሆን ነገር ግን ጳጳሳትን የመሾም ሂደትን ብቻ ይመለከታል” ሲሉ መልሰዋል። “ዛሬ ቻይና ውስጥ የሚገኙ ሁሉም ብጹዓን ጳጳሳት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ኅብረት አላቸው፤ ይህም መሠረታዊ ጉዳይ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

በሆንግ ኮንግ ውስጥ የሃይማኖት ነፃነትን ለማረጋገጥ ቤተ ክርስቲያን ከባለስልጣናት ጋር የምታደርገውን ውይይት  ቀጥላለች” ብለዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በመጨረሻም፥ ሌላውን ሰው አለመርሳት” ባሉት አስተያየታቸው፥ በቴክኖሎጂ ውስጥ ያለውን ከፍተኛ እድገት እና ገደቦች በማክበር አስፈላጊነት ላይ በማሰላሰል፥ “ሰብዓዊነትን መከላከል አለብን” ሲሉ ካርዲናል ፓሮሊን ተናግረው፥ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ለሌሎች አክብሮት የሌለውን የጥላቻ እና የንቀት ቋንቋ መጠቀምን አውግዘው፥ ይህም ፍርሃትን የሚፈጥር እና የተጠረጠሩ ጠላቶችን ለይቶ ለማወቅ ያስችላል” ብለዋል።

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በመደምደሚያቸው፥ “እንደ ክርስቲያኖች ይህንን ዕለታዊ ምስክርነታችንን መጠቀም አለብን” ብለው፥ ጥላቻ፣ ጦርነት እና ዓመፅ የሚጀምሩት ሌላውን ሰው ስንረሳ ነው” ብለዋል።

 

09 Apr 2026, 16:47