ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በኬፕ ቨርዴ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በኬፕ ቨርዴ  

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጋላገር፥ የቫቲካን ዲፕሎማሲ ለዘመናት ሰላምን እያገለገለ እንደሚገኝ አስታወቁ

በቫቲካን የመንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ክፍል ዋና ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር፥ ኬፕ ቨርዴ ከቅድስት መንበር ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የመሠረተችበት 50ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ ተገኝተዋል። አቡነ ጋላገር በመታሰቢያው በዓል ላይ ተገኝተው የቅድስት መንበር ዲፕሎማሲ የሥራ ዘዴዎችን የሚዳስስ ንግግር አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሊቀ ጳጳስ ጋላገር በንግግራቸው፥ ቅድስት መንበር እና ኬፕ ቨርዴ የሚጋሩት መሠረታዊ እሴቶች፥ የሕይወት ጥበቃ፣ ቤተሰብ፣ የሃይማኖት ነፃነት፣ ሰብዓዊ መብት፣ ዲሞክራሲ፣ የብዙ አገራት ግንኙነት እና ዓለም አቀፍ ሕግ ያካተቱ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ከእነዚህ ጎን ለጎን ግጭቶች፣ የአየር ንብረት ቀውስ፣ የሰዎች ኑሮ አለመመጣጠን፣ ስደት፣ የቴክኖሎጂ ዕድገት፣ የዕፅ ዝውውር፣ የእሴቶች ቀውስ፣ ግለኝነት እና የእውነት ስሜት ማጣት ያሉ ዋና ዋና ዓለም አቀፍ ተግዳሮቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።

እነዚህ ርዕሦች በቫቲካን የመንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ክፍል ዋና ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር፥ ሰኞ ግንቦት 3/2018 ዓ. ም. በኬፕ ቨርዴ በተካሄደው ጉባኤ ላይ የገለጿቸው እንደሆኑ ታውቋል።

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር እስከ ግንቦት 6/2018 ዓ. ም. ድረስ በአፍሪካ ደሴት ኬፕ ቨርዴ ሐዋርያዊ ጉብኝት በሚያደርጉበት ወቅት፥ በቅድስት መንበር እና በአገሪቱ መካከል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተመሠረተበት 50ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።

የሰላም ዋና ዓላማ

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር፥ የቫቲካን ዲፕሎማሲ ለዘመናት ከዘለቁ የዓለም ጥንታዊ የዲፕሎማሲ ተቋማት አንዱ መሆኑን ገልጸው፥ ከኬፕ ቨርዴ ጋር በመሠረተው የግማሽ ምዕተ ዓመት ግንኙነት ውይይትን፣ ትብብርን እና እውነተኛ ወዳጅነትን ማጎልበቱን ገልጸዋል።

ጳጳሳዊ ዲፕሎማሲ በረጅም ታሪካዊ ባሕል የተጠናከረ መሆኑን የገለጹት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጋላገር፥ የሰላም ማዕከላዊ ዓላማ የሆነውን የሰውን ልጅ ክብር መጠበቅ እና ማስተዋወቅ እንደሆነ አፅንዖት ሰጥተው፥ በዚህ ረገድ በ11ኛው ክፍለ ዘመን በተካሄደው የጎርጎሮሳዊያኑ ተሃድሶ ወቅት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ “የመሪነት መብት” በሚል የተመሠረተ ጳጳሳዊ የዲፕሎማሲ ተቋም አመጣጥን አስታውሰዋል።

ከዚያም በ15ኛው ክፍለ ዘመን የተገኘውን ተቋማዊ መረጋጋት ያስታወሱት ሊቀ ጳጳሱ፥ ከጊዜ በኋላ በሽግግር በሌሎች መንግሥታት መሻሻሉን ጠቅሰው፥ በጊዜዊነት ከሚደረጉ ተልዕኮዎች ወደ ቋሚ ተልዕኮዎች በማደግ የዘመናዊ ዲፕሎማሲ ማዕከላዊ ገጽታ ማግኘቱን አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጋላገር በመጨረሻም፥ በ16ኛው እና በ17ኛው ክፍለ ዘመን በታየው የጳጳሳዊ ዲፕሎማሲ ውህደት ላይ በማትኮር፥ በቅድስት መንበር ዲፕሎማሲያዊ ተወካይ፣ መልዕክተኛነት እና ብዙውን ጊዜ በሲቪል መንግሥት ውስጥ በውክልና ደረጃ በሚያገለግሉ ጳጳሳዊ ዲፕሎማሲዎች መካከል ያለውን ልዩነት አስረድተዋል።

የቅድስት መንበር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት

በአሁኑ ወቅት ቅድስት መንበር ከአውሮፓ ኅብረት እና ከማልታ ሉዓላዊ ወታደራዊ ማኅበር በተጨማሪ ከ184 አገሮች ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላት ሊቀ ጳጳስ ጋላገር ገልጸው፥ እንዲሁም በቅድስት መንበር እውቅና የተሰጣቸው 93 የዲፕሎማሲ ተልዕኮዎች በሮም እንደሚገኙ ሊቀ ጳጳስ ጋላገር አስረድተዋል።

አክለውም ጳጳሳዊ ዲፕሎማሲ የሥራ ዘዴዎችን እና በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት አገልግሎት ውስጥ የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት ተግባርን አብራርተዋል።

የቅድስት መንበር ዲፕሎማሲ ሰላምን፣ ፍትህን እና የሰው ልጅ ክብርን በመጠበቅ እና በማስፋፋት በዘመናት ውስጥ ልምዱን እንዳዳበረ ተናግረው፥ ከኬፕ ቨርዴ ጋር ግንኙነት የተጀመረው አገሪቱ ነፃነቷን ከማወጇ ማለትን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ 1975 ዓ. ም. በፊትም ጭምር መሆኑን ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ሐምሌ 1/1970 ዓ. ም. በቫቲካን ከተገኙት አጎስቲኖ ኔቶ፣ ማርቼሊኖ ዶስ ሳንቶስ እና አሚልካር ካባልን ጨምሮ ከአፍሪካ የነፃነት ንቅናቄ መሪዎች ጋር ያደረጉትን ስብሰባ አስታውሰዋል።

ቅዱስነታቸው ከነጻነት ንቅናቄ መሪዎች ጋር ያደረጉት ውይይት ኬፕ ቨርዴ ከፖርቱጋል ጋር ያላት ግንኙነት ለጊዜው እንዲቋረጥ ምክንያት መሆኑን አስረድተው፥ ይህም ቤተ ክርስቲያኗ የአፍሪካን ዓላማ ለመደገፍ ያላትን ድፍረት የተሞላበት ቁርጠኝነት እና ለሕዝቦች ያላትን ክብር ማሳየቱን ገልጸዋል።

በኬፕ ቨርዴ የምትገጘኝ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን

ይህ በእንዲህ እንዳለ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያኑ በኬፕ ቨርዴ ሪፐብሊክ መገኘት በታሪክ ላይ የተመሠረተ የማንነቷ አካል እንደሆነ የገለጹት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጋላገር፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1462 ዓ. ም. የአፍሪካ ደሴት በሆነች ኬፕ ቨርዴ የኖሩት የመጀመሪያዎቹ ካቶሊካዊ ሚስዮናውያን በባሕሏ፣ በሥነ ጥበቧ፣ በሙዚቃዋ እና በልማዶቿ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደራቸውን ገልጸዋል።

የሳንቲያጎ ደ ካቦ ቨርዴ ሀገረ ስብከት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1533 ዓ. ም. መቋቋሙን ያስታወሱት ሊቀ ጳጳሱ፥ ይህም ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች የመጀመሪያው እንደሆነ እና አገሪቱን ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች እና ትምህርት ተቋማት ያሏት የወንጌል እና የማኅበራዊ ድርጅቶች ማዕከል ማድረጉን ተናግረዋል።

ቤተ ክርስቲያኗ በአገሪቱ ውስጥ ፖለቲካዊ ወይም ኢኮኖሚያዊ ሥርዓቶችን ከመዘርጋት ይልቅ፥ የሰው ልጅ ክብር የሚጠበቅበት እና ተልዕኮዋን መወጣት እንድትችል ነፃነት እንዲረጋገጥላት መጠየቋን ሊቀ ጳጳስ ጋላገር አብራርተው፥ በዚህ አውድ በተለይም በጤና እና በትምህርት ዘርፎች ዕርዳታን ለማድረግ የታለመውን የቅድስት መንበር እና የኬፕ ቨርዴ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የ2013 ዓ. ም. ስምምነት ጠቅሰዋል።

በፍቅርና በእውነት ላይ የተመሠረተ ግንኙነት

በፍቅርና በእውነት ላይ የተመሠረተ ግንኙነት በማድረግ የመሣሪያ ትጥቅን የሚያስፈታ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የሰላም ጥሪን ተግባራዊ በማድረግ የተስፋ እና የእሴቶች ዲፕሎማሲ እንዲስፋፋ በማበረታታት፥በመጨረሻም የኬፕ ቨርዴ መሪዎችና ሕዝቦች በጋራ ጥቅም፣ በፍትህ፣ በአንድነትን እና በመረዳዳት ፍላጎት እንዲጸኑ አሳስበዋል።

ሰኞ ግንቦት 3/2018 ዓ. ም. ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በተገኙበት የ2013 ዓ. ም. የሁለትዮሽ ስምምነትን ተግባራዊ ለማድረግ ከአገሪቱ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጋር የፕሮቶኮል ስምምነት ተፈርሟል።

 

13 May 2026, 15:42