የቅድስት መንበር እና ጣሊያን የታዳሽ ኃይል ስምምነት ሥራ ላይ መዋል መጀመሩ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ሐሙስ ግንቦት 20 ቀን 2018 ዓ.ም. በተለቀቀው መግለጫ መሰረት ከሮም ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው በቫቲካን ሳንታ ማሪያ ዲ ጋሌሪያ አካባቢ በጣሊያን እና በቅድስት መንበር የተፈረመው የአግሪቮልታይክ ስምምነት ማለትም ለግብርናም ሆነ የፀሀይ ሃይል ማመንጨት የሚያስችል የተወሰነ የመሬት ክፍልን በአንድ ጊዜ መጠቀም የሚያስችል ስምምነትን ባለፈው ዓመት ሃምሌ ወር ላይ የተፈራረሙት ስምምነት ተግባራዊ መሆን መጀመሩን አስታውቋል።
ይህ ተነሳሽነት የመሬቱን የእርሻ አጠቃቀምን በመጠበቅ ለቫቲካን ከተማ ግዛት ታዳሽ ኃይል ለማቅረብ ያለመ ሲሆን፥ ከቫቲካን ድንበር ውጭ ነገር ግን የቫቲካን ግዛት የሆነው የሳንታ ማሪያ ዲ ጋለሪያ አካባቢ እ.አ.አ. ከ 1957 ዓ.ም. ጀምሮ የቫቲካን ሬዲዮ ስርጭት ማዕከል ሆኖ መቆየቱ በመግለጫው ተገልጿል።
የፕሮጀክቱ ተነሳሽነት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ሃዋሪያዊ መልዕክት በሆነው ‘ላውዳቶ ሲ’ ላይ እንደተገለጸው በተለይም “ንጹህ እና ታዳሽ ኃይልን የማግኘት አነስተኛ ተደራሽነት” ባለበት በአሁኑ ዓለም ውስጥ “በቂ የኃይል ማከማቻ ቴክኖሎጂዎችን ማዳበር እንደሚያስፈልግ” ከግንዛቤ ላይ በመደረሱ አማራጮችን ለማስፋት የታለመ መሆኑ ተመላክቷል።
የፕሮጀክቱ ደረጃዎች
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ሰኔ 19 ቀን 2016 ዓ.ም. ‘ፍራቴሎ ሶሌ’ በሚል የጀመሩት ተነሳሽነት ይሄንን ሥርዓት ለመገንባት ለጠቅላይ ግዛት ፕሬዝዳንቶች እና የሐዋርያዊ መንበረ ፓትርያሪክ አስተዳደር አስፈላጊውን ተግባር እንዲፈጽሙ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው የሚታወስ ሲሆን፥ በመቀጠልም ሃምሌ 24 ቀን 2017 ዓ.ም. በቅድስት መንበር የጣሊያን ኤምባሲ ውስጥ በቫቲካን የመንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ክፍል ዋና ጸሐፊ ከሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር እና እና የጣሊያን አምባሳደር ፍራንቸስኮ ዲኒቶ ስምምነቱን መፈራረማቸው ይታወሳል።
ስምምነቱ ግንቦት 27 ረቡዕ ዕለት በይፋ ሥራ ላይ መዋል የጀመረ ሲሆን፥ በዚህም መሰረት የቅድስት መንበር መግለጫ የወጣው በስምምነቱ አንቀጽ 5 ላይ የተደነገገው ሥርዓት መጠናቀቁን ተከትሎ እንደሆነ ተገልጿል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ማዕከሉ ለዓለም ምሳሌ መሆኑን መግለፃቸው
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ስምምነቱ ከተፈረመ ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሰኔ 12 ቀን 2017 ዓ.ም. የሳንታ ማሪያ ዲ ጋለሪያ አካባቢን በጎበኙበት ወቅት ለፋብሪካው የተመደበውን ቦታ የማየት እድልን ያገኙ ሲሆን፥ በዚህም ወቅት እንደተናገሩት ይህ “አስደናቂ ዕድል” እንደሆነ እና ግልጽ የሆነ “የቤተክርስቲያንን ቃል ኪዳን” እንደሚወክል በመግለጽ ይህ ማዕከል “ለተቀረው ዓለም ምሳሌ” የሆነ በጣም አስፈላጊ ፕሮጄክት መሆኑን አመላክተዋል።
ብፁዕነታቸው በማከልም የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ውጤት ሁሉም ሰው እንደሚረዳ እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በግልጽ እንደሚያስተምሩት ለመላው ዓለም፣ ለፍጥረታት ሁሉ እንክብካቤ ልንሰጥ እንደሚገባ በአጽንዖት ተናግረዋል።
“ለመሬቱ ታላቅ አክብሮት መስጠት”
ባለፈው ዓመት ሃምሌ ወር ላይ የተለቀቀው መግለጫ እንደሚያስረዳው የታዳሽ ሃይል ማመንጫ ፋብሪካው ከቴክኒካል እና ከመዋቅር አንፃር ተግባራዊ ለማድረግ ያለመ መሆኑን አፅንዖት በመስጠት፥ አሁን ባለው የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሁኔታ መሰረት ለመሬቱ ታላቅ ክብርን የሚያረጋግጡ መፍትሄዎችን በመተግበር የአፈርን የእርሻ ምርታማነት የመጠበቅ ዓላማዎችን በተሻለ ሁኔታ በማሻሻል እንዲሁም የአካባቢን የተፈጥሮ ሃይድሮጂኦሎጂካል ሚዛን ለመጠበቅ እና በተቻለ መጠን የአካባቢ ጥበቃን ለማረጋገጥ እንዲሁም የባህል፣ የአርኪዮሎጂ እና የመሬት ገጽታ ቅርስ ጥበቃን ማረጋገጥ እንደሆነ ተገልጿል።